ተማሪዎች በአገራዊ አስተዋጽኦ እንዲሳተፉ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለአንድ ሳምንት ሊዘጉ ነው

ተማሪዎች

የፎቶው ባለመብት, EDUARDO SOTERAS

ትምህርት ሚኒስቴር በመላው አገሪቱ የሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለአንድ ሳምንት ዝግ ሆነው ለአገራዊ ዘመቻ የተለያዩ ተግባራት እንዲያከናወኑ ወሰነ።

የሁለተኛ ደራጃ ትምህርት ቤቶቹ ከሚቀጥለው ሰኞ ኅዳር 27 እስከ ታኅሣሥ 3/2014 ዓ.ም. ዝግ እንደሚሆኑና ተማሪዎች፣ መምህራንና ሠራተኞች እንደየአካባቢያቸው ተጨባጭ ሁኔታ "ለአገራዊ ትግል አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ" መወሰኑ ተገልጿል።

ይህ ውሳኔ የተላለፈው የትምህርት ሚኒስቴር ባለሥልጣናት፣ የክልሎችና የከተማ አስተዳደር የትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች ውይይት ካደረጉ በኋላ መሆኑ ውሳኔው ይፋ በተደረገበት ጊዜ ተነግሯል።

የአገሪቱ የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ "አገር ከሌለች መኖር ስለማይቻል፣ ሁሉም አገሩን የመጠበቅ ኃፊነት አለበት" በማለት የትምህርቱ ዘርፍ ከወቅታዊው ሁኔታ አንጻር የሚጠበቅበትን አገራዊ ኃላፊነት እንዲወጣ ውሳኔው መተላለፉን አመልክተዋል።

በመላው አገሪቱ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሚዘጉበት ጊዜ ተማሪዎች፣ መምህራንና ሌሎች የዘርፉ ሠራተኞች በአካባቢያቸው የሚገኙ የዘማቾች ሰብል መሰብሰብና ቤተሰባቸውን የመርዳትን ጨምሮ የተለያዩ ተግባራት እንደሚከናወኑ ተገልጿል።

ተማሪዎች ከሚሳተፉባቸው ተግባራት መካከል ሰብል መሰብሰብ ይገኘበታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ተማሪዎች ከሚሳተፉባቸው ተግባራት መካከል ሰብል መሰብሰብ ይገኘበታል።

በተጨማሪም በመላው አገሪቱ በሚገኙ በትምህርት ዘርፉ ውስጥ ያሉ አካላት ለአገራዊ አገልግሎት የሚውሉ የተለያዩ አስተዋጽኦዎችን እንዲያበረክቱ ይደረጋል ተብሏል። በዚህም መሠረት የገንዘብ መዋጮ፣ ደም ልገሳ፣ የስንቅ ዝግጅትና ሌሎችም ተግባራት እንደሚከናወኑ ተነግሯል።

የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በሚሳተፉበትና ለአንድ ሳምንት በሚቆየው የአገራዊ ዘመቻ መረሃ ግብር ወቅት የሚስተጓጎለውን የትምህርት ሂደት ትምህርት ቤቶች በሚያወጡት የማካካሻ መርሃ ግብር አማካይነት እንዲካካስ ይደረጋል ተብሏል።

ለአንድ ሳምንት የሚዘጉት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ያሉ ተማሪዎች፣ መምህራንና ሠራተኞች የሚያከናውኑት ተግባር ለአገር የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ በመሆኑ ሁሉም አገራዊ ግዴታቸውን በመወጣት በአገር ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቧል።