"በተገጠመልኝ የዓይን ብሌን፣ መጀመሪያ እናቴን አይቼ አለቀስኩ"

ቤዛዊት ጥላሁን

የፎቶው ባለመብት, Bezawit Tilahun

ቤዛዊት ጥላሁን እስከ 12 ዓመቷ ከእኩዮቿ ጋር የምትቦርቅ፣ ትምህርቷን የምትከታተል እና የጎላ የጤና እክል እንኳን ገጥሟት የማያውቅ ታዳጊ ነበረች።

ዓይኖቿም የለምንም ችግር የሚያዩ እንደነበር ስትገልጽ "ቀልቶ እንኳን" አያውቅም ትላለች። ሆኖም በ2006 ዓ.ም ቤዛዊት የ12 ዓመት ልጅ እና የ7ኛ ክፍል ተማሪ እያለች ዕይታዋ መቀነስ ጀመረ።

በከፍተኛ ፍጥነት እያሽቆለቆለ የሄደው ዕይታዋ ሙሉ በሙሉ ማየት ወደማትችልበት ደረጃም ደርሶ ነበር። አመጣጡ በግልጽ ባይታወቅም የዓይን ብሌኗ ላይ በተፈጠረው ጠበሳ ምክንያት በሳምንታት ውስጥ ያለ ሰው እርዳታ መንቀሳቀስ የማትችል ሆነች። በዚህም ሳቢያ ለአእምሮ ጤና እክል ተዳርጋም ነበር።

"በአንዴ ትምህርቱንም ማቆም፤ ወጥቶ መጫወቱንም ማቆም ልጅ ሆኜ የማሳልፋቸውን ነገር አቁሜ ቤት መቀመጥ ከፍተኛ የሥነልቦና ጫና አለው" የምትለው ቤዛዊት "ከዚህ በኋላ አላይም የሚለው ነገር በጣም ስለሚሰማኝ ጭንቀት ውስጥ ገብቼ ሌላ ህክምና ጀምሬ የጭንቀት መድኃኒት የምወስድባቸው ጊዜያት ነበሩ" ስትል ታስረዳለች።

የዓይኖቿ ገጽታ ላይ ምንም ለውጥ ባለመኖሩ "ሰዎች አያምኑኝም። እየቀለድኩ ነው የሚመስላቸው" ስትል የምትገልጸው ቤዛዊት በዓይኖቿ አለማየት ምክንያት ያሳለፈችው ውጣ ውረድ ከእሷ አልፎ ለቤተሰቦቿም የተረፈ ነበር።

ለሦስት ዓመታት በአስቸጋሪ ሁኔታ የቆየችው ቤዛዊት በ2009 ዓ.ም ብርሃኗን ብቻ ሳይሆን የአእምሮ ጤንነቷን ሊመልስ የሚችል አጋጣሚ አገኘች።

ዳግማዊ ሚኒሊክ ሆስፒታል ውስጥ ከሚገኘው የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ ከለጋሽ የተገኘ እና ለእሷ የሚሆን አንድ የአይን ብሌን መኖሩ ተነገራት። ይህ የዓይን ብሌን 2 ሰዓታትን በፈጀ የንቅለ ተከትላ ሂደት ከተገጠመላት በኋላ ደስታዋ ወስን አልነበረውም።

"መጀመሪያ ያየሁት እናቴን ነበር። በጣም ከባድ ነው ስሜቱ [ሳግ እየተናነቃት] አዲስ ነው የሆነችብኝ። ያሳደገችኝ እናቴ አልመሰለችኝም። በጣም ነው የሚያስደስተው። እናቴን እንዳየኋት ወዲያውኑ አለቀስኩ።...በህይወት ያጣሁትን ሰው መልሶ እንደማግኘት ነው - ስሜቱ" ስትል ታብራራለች።

"ቤተሰቦቼም ታያለች እኔም ከዚህ በኋላ አያለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም።...ደስተኛ ያደርጋል ተስፋ ይሰጣል።"

ቤዛዊት በተገጠመላት ብሌን ዕይታዋ ከተመለሰ በኋላ ከሦስት ዓመት በፊት ወዳቋረጠችው ትምህርት ተመለሰች። አንድ ዓይኗ ቢያስቸግራትም እስከ 10ኛ ክፍል ትምህርቷን ቀጥላለች።

በንቅለ ተከላው ዕይታዋ ባይመለስ ኖሮ ያጋጠማት ጭንቀትና መረበሽ ተባብሶ ወደ ሌላ ደረጃ ሊደርስ ይችል እንደነበር የምትናገረው ቤዛዊት፣ ሁለተኛውን ዓይን ለማግኘት ግን አምስት ዓመታትን መጠበቅ ነበረባት።

ፍሬው ሺበሺ

የፎቶው ባለመብት, Firewu Shibeshi

"በቃላት የማይገለጽ ብርሃን ነው ያገኘሁት"

በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን ነዋሪ የሆነው ፍሬው ሺበሺም በግራ ዓይን ብሌኑ ላይ የነበረው ጠባሳ ቀስ በቀስ እየሰፋ ዕይታው በከፍተኛ ደረጃ ቀንሶ ለተለያዩ ችግሮች ተዳርጎ ነበር። የጠባሳው መነሻ ምን እንደሆነ በትክክል ባይታወቅም የቴክኒክ እና ሙያ ተማሪ በነበረበት ወቅት ብየዳ ይለማመድ ስለነበረ መነሻው ያ ሊሆን እንደሚችል ይገምታል።

በባሌ ዞን ጊኒር በተባለ ቦታ ሞተር ሳይክል በማሽከርከር ገቢ ያገኝ የነበረው ፍሬው ዕይታው እጅግ ዝቅተኛ ሆኖ ነገሮችን መለየት እስኪያቅተው ድረስ ሥራውን አላቋረጠም ነበር።

"ያው ግዴታ መስራት ስለነበረብኝ። ካልሰራሁ መኖር ሰለማልችል በሥራዬ ቀጥዬ ነበረ።...በእግዚያብሔር ጥበቃ ስር ሆኜ ነው እንጂ የተለያየ አደጋ ደርሶብኛል። በፍጥነት ሞተርን ሳሽከረክር በጣም በቅርበት ካልሆነ ማየት ሰለማልችል ከፊት ለፊቴ ካለው ነገር ጋር እጋጭ ነበር" ሲል ያስታውሳል።

ፍሬው ዕይታው በዚህ ደረጃ መቀነሱ የእለተ'ለት ህይወቱን አሰቸጋሪ እንዲሆን ከማድረጉ ባሻገር ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ ከቶት ነበር።

"ወጣት ሆኖ ዕይታን በቅጽበት ማጣት ይከብዳል። ወደ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ይከታል። ለምንድን ነው የምኖረው? የሚለው ነገር ይፈጥርና ህይወትን ዝም ብሎ መኖር ይጀመራል። መኪና በገጨኝ ጊዜ ይገጨኝ የሚል አይነት ኑሮ ሁሉ ጀምሬ ነበር።...መንገድ ሳቋርጥ ሰዎች 'አታይም እንዴ?!' ምናምን እያሉ ህሊና የሚነካ ስድብ ይሳደባሉ።"

ከ10 ዓመታት በላይ በዚህ ሁኔታ ሲቸገር የቆየው ፍሬው በህይወት ከሌለ ሰው የወሰደው የዓይን ብሌን ህይወቱን ባልጠበቀው አቅጣጫ ቀየረለት።

በሰዎች ጥቆማ ወደ ዓይን ባንክ በማምራት ተመዘገበ። ከብዙ ጥበቃ በኋላ ባለፈው ዓመት የካቲት ላይ ለእሱ የሚሆን የዓይን ብሌን ተገኝቶ ሦስት ሰዓታት በፈጀ የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ ሂደት ዕይታው ተመለሰለት "በቃላት የማይገለጽ ብርሃን ነበር ያገኘሁት" ሲል ያስረዳል።

"ከንቅለ ተከላው በኋላ በዓይኑ ላይ የነበረው መሸፈኛ ሲነሳ ዕይታዬ የሚገርም ነበር። በቃ የሚገርም ብርሃን ነው ያገኘሁት። ከጨለማ ወደ ብርሃን ነው የመጣሁት። 'እንደዚህ አያለሁ እንዴ?' እስክል ነው የተገረምኩት። ብርሃን የሚያክል ነገር ሲገኝ [ደስታውን] እንዴት ተብሎ እንደሚገለጽ ከባድ ነው።"

የ33 ዓመቱ ፍሬው ከለጋሽ የተገኘው የዓይን ብሌን ከማግኘቱ በፊት አጥርቶ ማየት የሚችለው ከአንድ ሜትር የነሰ ርቀት ላይ ሲሆን አሁን እስከ አምስት ሜትር ድረስ መመልከት እንደሚችል እና የልቡ እንደደረሰለት ይናገራል።

"መጽሐፎችን ማንበብ እፈልግ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስም ማንበብ እፈልግ ነበር። ከዚያ በኋላ ማንበብ ችያለሁ። በግሌ መስራት የማልችላቸው ነገሮች ነበሩ። አሁን ላይ ግን በዓይኔ በኩል ምንም የሚቸግረኝ ነገር የለም። በቃ የልቤ ደርሶልኛል ማንበብ ችያለሁ።"

አይን ጠብታ እየተደረገ

የፎቶው ባለመብት, Eye Bank of Ethiopia

ቤዛዊት እና ፍሬው የሚሳተፉበት አዲስ እንቅስቃሴ

ቤዛዊት ከአምስት ዓመታት ጥበቃ በኋላ ከአንድ ወር በፊት ሁለኛውን የዓይን ብሌን አግኝታለች። "ያኔ በአንዱ ብቻ ስለነበር የማያው፣ ይህቺ እንኳን የሆነ ነገር ብትሆን ብዬ አስብ ነበር" ስትል የነበራትን ስጋት ትገልጻለች።

ሆኖም አሁን ሁለት የዓይን ብሌን በማግኘቷ ወደ ኋላ የሚያሰጋትና ካሰበችው ወደ ኋላ የሚያስቀራት ነገር የለም ትላለች። ይህን 'በምንም ቃል የማይገለጽ ደስታ' እሷ ባለፈችበት መንገድ ያለፉ ሰዎች እንዲጋሩ ለመርዳት ጥረት ማደረግ ላይ ነች።

እሷና ፍሬውን ጨምሮ ከዓይን ባንኩ ብሌን አግኝተው ብርሃናቸው የተመለሰላችው ሰዎች በማኅበራዊ ሚዲያ አማካኝነት በጉዳዩ ዙሪያ ግንዛቤ እንዲስፋፋ እንቅስቃሴ ጀምረዋል።

ቤዛዊት የዚህ እንቅስቃሴ ንቁ ታሳታፊ ስትሆን እስካሁን ወንድም እና እህቶቿን ጨምሮ 17 ሰዎች ከህልፈታቸው በኋላ የአይን ብሌናቸውን እንዲለግሱ አሳምና እንዲፈርሙ አድርጋለች።

"ዋናው ዓላማችን ምንድን ነው፤ እኛ ማየት ችለናልና ለማኅበረሰባችን ግንዛቤ መፍጠር ለዶክተሮቻችን ምስጋና መሰጠት ባህል እንዲሆን ነው የምንፈልገው። ብርሃን ያጡ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ አሉና እነሱን ወደ ህክምና ማምጣት ነው።"

የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ ዳይሬክተር ወይዘሮ ለምለም አየለ ባንኩ ካሉበት ችግሮች መካከል ዋነኛው በሰዎች ዘንድ ስለ ዓይን ብሌን ንቀለ ተከላ ያለው የተሳሳተ ግንዛቤ ስለመሆኑ ይናገራሉ።

እናም እነቤዛዊት የጀመሩትን እንቅስቃሴ ጉዳዩን በስፋት ለማስተዋወቅ እና የዓይን ብሌን ለጋሾችን ቁጥር ከፍ ለማድረግ እንደሚረዳ ይታመናል።

"ሩቅ ሳንሄድ በእኔ ማየት ይቻላል። እኔ ከዚህ በፊት መስራት የማልችለውን ነገር መስራት ችያለሁ። አንድ በበጎ ፍቃደኝነት በለገሰ ሰው እኔ ማየት ችያለሁ። ብርሃንን ከምንቀብር ብርሃን ብንለግስ፤ ለምን ብርሃንን እንቀብራለን?" ሲል የሚጠይቀው ፍሬው ይህንን እሳቤ በሰዎች ዘንድ ማስረጽ የእንቅስቃሴያቸው ዓቢይ ተግባር እንደሆነ ጠቁሟል።

"በኢትዮጵያ ከ300 ሺህ በላይ ሰዎች የዓይን ብሌን ጠበሳ ችግር አለባቸው"

በ1995 ዓ.ም የተመሠረተው የዓይን ባንኩ ባለፉት 18 ዓመታት እንደቤዛዊት እና ፍሬው ላሉ በዓይን ብሌን ጠበሳና ተያያዥ ችግሮች ምክንያት ለዓይነ ስውርነት ለተዳረጉ ወይም ዕይታቸው በእጅጉ ለቀነሱ ከ2500 በላይ ሰዎች የዓይን ብሌን በማቅረብ ዕይታቸውን መልሷል።

የዓይን ባንኩ ዳይሬክተር ወይዘሮ ለምለም ይህ ቁጥር በየዓመታት ውስጥ እያደገ ቢሄድም፣ ዝቅተኛ መሆኑን ከ17 ዓመታት በፊት የተደረገ አገራዊ ጥናትን ዋቢ አድርገው ይናገራሉ።

"ከ300 ሺህ በላይ ሰዎች በዓይን ብሌን ጠባሳ ምክንያት ተጎድተው ይገኛሉ። ይሄ ቁጥር ደግሞ አሁን ካለን አጠቃላይ የሕዝብ ቁጥር አንጻር ብዙ አድጓል ብለን ነው የምንገምተው። ስለዚህ አስካሁን የሠራናቸው ንቅለ ተከላዎች እጅግ በጣም ትንሽ ናቸው።"

በዓይን ብሌን ጠባሳ እና መሰል ችግሮች የሚመጣ ዓይነ ስውርነት ሙሉ በሙሉ ሊድን የሚችል እንደሆነ የሚናገሩት ዳይሬክተሯ፣ ይሄ የሚሆነው ግን ለጋሾች ከህልፈታቸው በኋላ የዓይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል ሲገቡ ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል።

ለጋሾች ከህልፈታቸው በኋላ የዓይን ብሌን ለመስጠት ቃል ሲገቡ የሚወሰደው የዓይናቸው ሙሉ ክፍል ሳይሆን ከ12 እስከ 14 ሚሊሜትር የሚሆነው የዓይን አካል [ብሌን] ነው።

"ከዓይን ብሌን የፊት ክፍል ያለው እና የአውራ ጣት ጥፍር የምታክል መስታወት መሰል ብርሃን አሳላፊ ክፍል ብቻ ናት ለኢትዮጵያ የዓይን ባንክ የሚለገሰው። ስለዚህ ከህልፈቱም በኋላ ሂደቱ በለጋሽ ዓይን ላይ የሚያመጣው የገጽታ ለወጥ የለም" ሲሉ ያስረዳሉ።

ሂደቱም ከ30 እስከ 40 ደቂቃ የሚፈጅ ሲሆን የለጋሹ ህይወት ካለፈ በኋላ ባሉት ስምንት ሰዓታት ውስጥ መከናወን ይኖርበታል።

በሌላ በኩል ባንኩ ከመንግሥት እና ከዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ተቋማት በተለያየ ወቅት ገንዘብ የሚቀርብለት ቢሆንም ለሥራው የሚያስፈልገው የገንዘብ እጥረት ዋና ፈተናው መሆኑን ጠቅሰዋል።

"ይህ የሚሟላበት ሁኔታ ቢኖር ተቋሙ ባሰበው ልክ የተለያዩ ክልሎች ላይም ቅርንጫፍ የመሰብሰቢያ ጣቢያዎችን በመክፈት አገልግሎቱን ተደረሽ ማድረግ ይችላል። ለዚህ ደግሞ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር እየሰራን ነው የምንገኘው።"

በ1995 በአዲስ አበባ የተጀመረው የዓይን ባንኩ አገልግሎት አሁን በጎንደር፣ በጅማ እና በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች ውስጥ እንዲሁም በትግራይ ኩያ ሆስፒታል በመስፋት የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህም ባሻገር የለጋሾች ቁጥር ለማሳደግ በአዲስ አበባ እና በሌሎች አካባቢዎች የባንኩን ቅርንጫፎች ለመጨመር ከጤና ሚኒስቴር ጋር እየሰራ ይገኛል።

ዜጎች የዓይን ብሌንናቸውን የመለገስ ፈቃደኝነታቸው ቢዳብር እና ባንኩ ያለበት የፋይናንስ ችግር ቢቃለል የብዙዎችን ህይወት መቀየር እንደሚችል ቤዛዊት በጽኑ ታምናለች።

"ብርሃናችሁን ለግሱ ስንል ማድረግ ሰለሚቻል ነው" የምትለው ቤዛዊት "እኔ ማየት ስለቻልኩ ነው ከቤት የወጣሁት። ማየት ስለቻልኩ ነው ትምህርቴን የቀጠልኩት። እርግጠኛ ነኝ የሆነ አሻራ እንደማሳርፍ አውቃለሁ። አሻራዬን የማሳርፈው ደግሞ ስለ ተደረገልኝ ነው።"