ተራኪ፡ የሩጫ ዘመን የወለደው የመጻሕፍት ትረካ መተግበሪያ

ናሆም ጸጋዬ እና አቤል እንግዳ

የፎቶው ባለመብት, Nahom

የምስሉ መግለጫ, ናሆም ጸጋዬ እና አቤል እንግዳ

ሁላችንም ሩጫ ላይ ነን። የሥራ፣ የኑሮ ሩጫ።

ሩጫውን ገታ አድርገን ዘለግ ያለ ጽሑፍ የምናነብ ስንቶቻችን እንሆን?

ቴክኖሎጂም በአማራጮች ያጨናንቀናል። ቲክቶኩ፣ ኢንስታግራሙ፣ ትዊተሩ፣ ፌስቡኩ፣ ፒንትረስቱ. . .

ለእያንዳንዱ ማኅበራዊ ሚዲያ በቂ ጊዜ እንስጥ ብንል፤ ሁሉንም ለማዳረስ ሙሉ ዕድሜያችንስ ይበቃናል?

ከአንዱ ወደ ሌላው በሩጫ እንሻገራለን። ዜና ርዕሱን ብቻ አንብበን እናልፋለን። ሙሉ ቪድዮ አይቶ መጨረስ የማይታሰብ ነው። ስለዚህ ላይክ፣ ኮሜንት፣ ሼር አድርገን ቶሎ ማለፍ።

ያለንበት የሩጫ እና የቴክኖሎጂ ዘመን ካስረሳን መካከል መጻሕፍት ዋነኛ ተጠቃሽ ናቸው። ለመሆኑ ለመጨረሻ ጊዜ መጽሐፍ አንብበው የጨረሱት መቼ ነበር?

ጓደኛሞቹ ናሆም ፀጋዬ እና አቤል እንግዳም እንደ አብዛኞቻችን ይሮጣሉ። ከስልካቸው በቀላሉ አይላቀቁም።

አምና የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሰውን ሁሉ ቤቱ እንዲውል ሲያደርገው ግን ነገሮች ተለወጡ። ጓደኛሞቹ ለምን መጻሕፍት አናነብም? ብለው ተነሱ።

መጻሕፍትን እንደ ቀደሞው በጥራዝ ማንበብ አልነበረም ውጥናቸው። ዘመኑ በደረሰበት ቴክኖሎጂ መጻሕፍትን በመተግበሪያ ማዳመጥ እንጂ።

እናም ወጣቶቹ ተራኪ የተባለ የመጻሕፍት ትረካ መተግበሪያ ፈጠሩ።

ናሆም የኮምፒውተር ኢንጂነሪንግ ምሩቅ ነው። አቤል ደግሞ የአርክቴክቸር።

የተራኪ ትረካዎች

ተራኪ መተግበሪያን ወደ 9 ሺህ ገደማ ተጠቃሚዎች በስልካቸው ጭነውታል።

በአማርኛ፣ በኦሮምኛ እና በእንግሊዘኛ የተጻፉ መጻሕፍት ትረካዎች አሉት።

ልብ ወለድ፣ እውነተኛ ታሪክ፣ ፍልስፍና፣ ፖለቲካ፣ የልጆች ተረት እና ሌሎችም መጻሕፍትን ይዟል።

በሩዋንዳዊቷ ኢማኪዩሌ ኢሊባጊዛ የተጻፈው 'ሌፍት ቱ ቴል' ውርስ ትርጉም የሆነው የመዘምር ግርማ 'ሁቱትሲ'፣ የቆንጂት ብርሐን 'ምርኮኛ'፣ የካሕሳይ አብርሃ 'የአሲምባ ፍቅር' እና የፈቀደ አግዋር 'የልብ ጠጋኙ ማስታወሻ' ይጠቀሳሉ።

በተራኪ መተግበሪያ ፖድካስቶችም ተካተዋል።

የመዝናኛ፣ የራስ አገዝ፣ የቴክኖሎጂ፣ የሳይንስ እና የሐይማኖት ይዘት ካላቸው ፖድካስቶች መካከል ዘማች ኤፍኤም፣ ሐበሻ ኢን ቴክ፣ ጉርሻ እና ኩኩሉ ይገኙበታል።

በአፍሪካ ትልቁ የንግድ ትስስር መድረክ በሆነው ኢንተር-አፍሪካ ትሬድ ፌር የዘንድሮው አሸናፊ ከሆኑት አንዱ ተራኪ ነው።

ከሰሞኑ በደርባን፣ ደቡብ አፍሪካ በተካሄደው የንግድ ዐውደ ርዕይ፣ በጀማሪ ነጋዴዎች ዘርፍ እውቅና ማግኘታቸውን ናሆም ለቢቢሲ ገልጿል።

"የንባብ ባህል እየደከመ በመምጣቱ መፍትሔ ልናበጅ ይገባል ብለን የፈጠርነው መተግበሪያ ነው" ይላል፣ ስለ ተራኪ ሲያስረዳ።

ንግድ፣ ንግግር፣ ንባብ እና ሌሎችም ክንውኖች ወደ ስልክ ተሻግረዋል። ከዘመኑ ጋር ለመራመድ መጻሕፍትንም የዚህ አካል ማድረግ የግድ እንደሆነ ያምናል።

ተራኪ መጻሕፍትን በድምጽ ሲያቀርብ ዓይነ ስውራንንም ታሳቢ በማድረግ ነው። ከዓይነ ስውራን ማኅበራት ጋር በመጣመርም ይሠራሉ።

"በእንግሊዘኛ የተጻፉ የኢትዮጵያውያን መጻሕፍት አሉን። በቅርቡ የትግርኛ ትረካዎች እንጀምራለን። በሂደት አብዛኛውን የኢትዮጵያ ቋንቋ ሽፋን ለመስጠት እናቅዳለን" ይላል።

ፖድካስቶች፣ ጭውውቶች፣ ወጎች፣ ግጥሞች እንደ ስፖቲፋይ ባሉ ማኅበራዊ የትስስር ገጾች ሲወጡ፤ በየጊዜው በሚለቀቁ አዳዲስ ይዘቶችን ስለሚሸፈኑ ተራኪ ቋሚ መድረክ ይሰጣቸዋል።

ናሆም "በኢትዮጵያ ፖድካስት እየተለመደ ስለመጣ በየቀኑ ብዙ አድማጭ እያገኘን ነው" ይላል።

ከዓመት በፊት ናሆም እና አቤል የጀመሩት መተግበሪያ አሁን ላይ አድጎ የቴክኖሎጂ እና የመጽሐፍ ትረካ ክንፍ አለው።

የትረካ ክፍሉ የተለያዩ መጻሕፍትን ስቱድዮ ውስጥ በድምጽ ይቀርጻል።

ቅጂ መት (ኮፒራይት) ጉዳይ

በተራኪ የሚቀርቡ የኢትዮጵያ መጻሕፍት ከደራሲያን ጋር የቅጂ መብት (ኮፒራይት) ስምምነት እንደሚደረግባቸው ናሆም ይናገራል።

አንድ መጽሐፍ ለህትመት የበቃበትን ዓመት እና ሌሎችም መስፈርቶችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ደራሲያን ከ30 በመቶ እስከ 65 በመቶ ድርሻ እንደሚወስዱ ያስረዳል።

ተራኪ ወደ ደራሲያን የሚሄድበት እንዲሁም ደራሲያን ወደ ተራኪ የሚመጡበትንም አሠራር ዘርግተዋል።

በመተግበሪያው ለሽያጭ የሚቀርቡ መጻሕፍት ሲኖሩ የሚገኘውን ትርፍ ይካፈላሉ። አንዳንድ መጻሕፍት መተግበሪያው ላይ በነጻ ሲወጡ እንደ ማስታወቂያ ስለሚቆጠር ክፍያ አይፈጸምም።

"በነጻ ለሕዝብ ከሚቀርብ መጽሐፍ ውጪ ያለው ለሽያጭ ነው የሚሆነው። ደራሲያን ገቢ ማግኘት አለባቸው። አሁን ላይ የኢትዮጵያ ደራሲያን የሚገባቸውን ጥቅም እያገኙ አይደለም" ይላል ናሆም።

ተራኪ የሥራ ማስኬጃ ወጪውን የሚሸፍነው ከሌሎች ገቢዎች ነው። ለወደፊት በሰብስክሪብሽን ክፍያ እና በሌሎችም መንገዶች መተግበሪያው እራሱን የቻለ ትርፍ እንደሚያገኝ ናሆም ያምናል።

"በቀጣይ የግል ባለ ሀብቶች ኢንቨስት እንዲያደርጉ እንጠይቃለን። በተለይም በኢንተር-አፍሪካ ትሬድ ፌር ላይ ኢትዮጵያን ወክለን ማሸነፋችን ያግዘናል" ሲል ያስረዳል።

ተራኪ

የፎቶው ባለመብት, Nahom

"በየቀኑ ለአንድ ሰዓት ኦዮቡክ አዳምጣለሁ"

በተራኪ አዳዲስ እና የቆዩ መጻሕፍትም ይገኛሉ።

ለትረካ የተመቸ ነው ብሎ የሚያስበውን መጽሐፍ የሚመርጥ ቡድን አለ። ከዚያ ከደራሲያን ፈቃድ ይጠየቃል። ተራኪ ላይ ይቅረብልን ብለው የሚጠይቁ ደራሲያንም አሉ።

ገበያ ላይ የሌሉ ወይም ተጽፈው ሳይታተሙ የቀሩ መጻሕፍትን የማካተት ዕቅድ አላቸው።

መተግበሪያውን የጫኑ ሰዎች በቀጥታ ኦንላይን ማድመጥ ይችላሉ። መጻሕፍቱን ጭኖ ኦፍላይን መስማትም ይቻላል።

መተግበሪያውን የዓይነ ስውራን ማኅበራት እንዲገለገሉበት ማስቻል ሌላው ዕቅዳቸው ነው።

"ዓይነ ስውራን ሰው ከሚያነብላቸው ይልቅ በእራሳቸው ስልክ፣ በፈለጉት ጊዜ መጻሕፍትን እንዲሰሙ ያስችላል። በተለይም በቅርብ ጊዜ የወጡ መጻሕፍትን ያገኛሉ" ይላል ናሆም።

ናሆም በየቀኑ ለአንድ ሰዓት ኦዲዮቡክ የማዳመጥ ልማድ አዳብሯል።

"ጠዋት 30 ደቂቃ፣ ማታ 30 ደቂቃ እሰማለሁ። መተግበሪያውን ሳልጀምር በፊትም የነበረኝ ልማድ ነው። ተራኪን የሠራነው መተግበሪያው ከእኛ ልማድ ጋር ስለሚጣጣም ነው።"

የንባብ ባህል የቀጨጨው ያለ ምክንያት አይደለም። ወደ 70 በመቶ የሚጠጉት ወጣት የኢትዮጵያ ዜጎች አብዛኛውን ጊዜ የሚያጠፉት ስልካቸው ላይ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ ጉዳዮች ጥድፊያ ውስጥ ናቸው።

"ንባብ ሲጎዳ ደራሲያን እና መጻሕፍት ሻጮች ብቻ ሳይሆን መላው አገሪቱ ትጎዳለች" የሚለው ናሆም፤ ተራኪ ይህንን ክፍተት ለመሙላት እንዳለመ ይገልጻል።

የኢትዮጵያ ቴሌኮም ዘርፍ ለውጭ የቴሌኮም ተቋሞች ክፍት ከመሆኑ ጋር በተያያዘ የኢንተርኔት ተደራሽነት እየሰፋ ሲሄድ፤ የመጻሕፍት ትረካ መተግበሪያ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከፍ እንደሚል ያምናል።

"በትራንስፖርት ውስጥ ረዥም ሰዓት ነው የምናሳልፈው። ሩጫ ላይ ነን። ብዙዎቻችን በመሰላቸት እና ጊዜ በማጣትም ረዥም ጽሑፍ አናነብም። አጭር ነገር በስልካችን ማየት እየለመድን ነው። ስለዚህ ኦዲዮቡክ የተሻለ አማራጭ ነው።"