በኢትዮጵያ የኤችአይቪ ቫይረስ ስርጭት መቀነሱ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኢትዮጵያ በየዓመቱ በኤችአይቪ ቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መቀነሱ ተገለጸ።
በፌደራል ኤችአይቪ ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት የሕዝብ ግነኙነት እና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዳንኤል በስረ በኢትዮጵያ የኤችአይቪ ቫይረስ ስርጭት መቀነሱን ጥናቶች ያመላክታሉ ብለዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ አጠቃላይ የቫይረሱ የስርጭት ምጣኔ 0.86 በመቶ መሆኑን አቶ ዳንኤል ያስረዳሉ።
"ይሄ ማለት በመላው አገሪቱ፤ በሁሉም ማሕበረሰብ ክፍል ተመሳሳይ ነው ማለት አይደለም። በገጠር እና በከተማ የስርጭት ምጣኔው የተለያየ ነው" የሚሉት ዳንኤል፤ በጋምቤላ ክልል እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስርጭት ምጣኔው ከፍተኛ መሆኑን ይናገራሉ።
ዳንኤል የቫይረሱ ስርጭት በጋምቤላ 4.1 በመቶ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከ3 በመቶ በላይ መሆኑን ያስረዳሉ።
3 በመቶ ምጣኔ ምን ማለት እንደሆን ሲያስረዱ፤ በቀላል ቋንቋ ከመቶ ሰዎች ሦስት ሰዎች ቫይረሱ በደማቸው አለ ማለት ነው ይላሉ።
በሶማሌ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች፣ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የስርጭት ምጣኔው ከ1 በመቶ በታች መሆኑን ይናገራሉ።
የሶማሌ ክልል 0.01 በመቶ አነስተኛ የቫይረሱ ስርጭት የሚገኘበት ክልል መሆኑን ይናገራሉ።
በአገሪቱ ክልሎች መካከል ከፍተኛ የሆነ የቫይረሱ ስርጭት ልዩነት እንዴት ሊፈጠረ ቻለ? ተብለው የተጠየቁት አቶ ዳንኤል፤ ለዚህ ጥያቄ ቁርጥ ያለ ምላሽ ለመስጠት በዝርዝር ጥናት ላይ መመርኮዝ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የተሰራ ሥራ ልዩነት ፈጥሮ ሳይሆን ዋናው ምክንያት ከባህል እና ሃይማኖታዊ ጉዳይ ጋር ሊያያዝ ይችላል ይላሉ።
አቶ ዳንኤል ከዓመታት በፊት በኢትዮጵያ አጠቃላይ የቫይረሱ ስርጭት ምጣኔ ከ6 በመቶ በላይ ደርሶ የሚያውቅበት አጋጣሚ እንዳለ ይናገራሉ።
በከተሞች አካባቢ ደግሞ የስርጭት ምጣኔው እስከ 10 በመቶ ስለመድረሱ ተመዝግቦ ነበር ይላሉ።
"በአንድ አገር አጠቃላይ የስርጭት ምጣኔው ከ1 በመቶ እና ከዚያ በላይ ከሆነ የቫይረሱ ስርጭት ወረርሽኝ ነው የሚባለው" የሚሉት አቶ ዳንኤል፤ ምንም እንኳ በአገር ደረጃ የስርጭት ምጣኔው ከ1 በመቶ በታች ቢሆንም የስርጭት መጠኑ ከ1 በመቶ በላይ የሆነባቸው ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች መኖራቸውን ይናገራሉ።
የቫይረሱ ስርጭት በጾታ ተከፍሎ ሲታይ ደግሞ፤ ሴቶች ከወንዶች በላይ ተጋላጭ መሆናቸውን ይናገራሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሽታውን በመከላከል ረገድ የሚሰሩ ሥራዎች መቀነሳቸውን ዳንኤል አስረድተዋል።
መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንዲሁም የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ቀደም ሲል ሲሰሩ በነበሩበት ልክ ቫይረሱን የመከላከል ሥራ እየሰሩ አይደለም ይላሉ።
ለዚህም ምክንያቱ የስርጭቱ መጠን በየዓመቱ መቀነስ በማሳየቱ እና በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ከመከላከሉ ይልቅ ሕክምናው ላይ ትኩረት በመሰጠቱ ነው ይላሉ።
በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች
በአሁኑ ወቅት ከ622 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች በኢትዮጵያ የኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ይገኛል። ከእነዚህ መካከል ወደ 500 ሺህ የሚሆኑ ጸረ-ኤችአይቪ መድሃኒት እየወሰዱ እንደሚገኙ ጥናቶች ያሳያሉ ብለዋል ዳንኤል።
በየዓመቱ ከ11 ሺህ በላይ አዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች አሉ። "ይህን የከፋ የሚያደርገው ከእነዚህ ውስጥ 67 በመቶ ድርሻ የሚይዙት እድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶች መሆናቸው ነው" ይላሉ ዳንኤል።
የቫይረሱን ስርጭት መከላከል አስፈላጊነትን ከሚያረጋግጡት መካከል አንዱ በበሽታው የሚያዙት አብዛኛዎቹ ወጣቶች መሆናቸው ነው ይላሉ።
"አምራች ኃይል ነው። እንደ ሀገር ተስፋ የሚጣልበት ነው። በዚህ እድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ወጣቶች ላይ የስርጭት ምጣኔው ከፍ ብሎ መታየቱ እንደ አገር አደጋ ውስጥ እንዳለን የሚያሳይ ነው" ብለዋል።
ዳንኤል፤ ሴተኛ አዳሪዎች፣ ባሎቻቸውን በሞት ያጡ እና ትዳራቸውን የፈቱ ሴቶች ዘንድ የቫይረሱ ስርጭት መጠን ከፍተኛ ነው ይላሉ።
"በሴተኛ አዳሪዎች የስርጭት ምጣኔው 18 በመቶ ነው። ባሎቻቸውን በሞት ያጡ እና ትዳራቸውን የፈቱ ሴቶች አካባቢ የስርጭት ምጣኔው ወደ 20 በመቶ ሆኖ እናያለን" ይላሉ።
ሕይወታቸው የሚያልፍ ሰዎች
ከ12 ሺህ ባለይ ሰዎች ደግሞ በየዓመቱ በኤድስ እና ተያያዥ በሽታዎች ሕይወታቸው እያለፈ ነው።
በአገሪቱ ቫይረሱ በደማቸው ይገኘባቸዋል ከተባለው ከ622 ሺህ ባለይ ሰዎች 61 በመቶውን የሚይዙት ሴቶች ናቸው ይላሉ።
በአሁኑ ሰዓት የስርጭት ምጣኔው ከ1 በታች መሆኑ የስርጭት መጠኑ አነስተኛ እንደሆነ ነው የሚያሳየን የሚሉት አቶ ዳንኤል፤ የስርጭት መጠኑ ግን ሊያዘናጋን አይገባም ይላሉ።
"መዘናጋቱ እና ቸልተኝነቱ በዚህ መንግድ የሚቀጥል ከሆነ፤ እንደ አገር ያልተገባ ዋጋ ሊያስከፍለን ይችላል" የሚሉት አቶ ዳንኤል፤ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ የልሆኑ ተቋማት እንዲሁም የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የድርሻቸውን መወጣት አለባቸው ይላሉ።
ኮቪድ እና ኤችአይቪ
የኮሮናቫይረስ መከሰት ኤችአይቪ በደማቸው በሚገኝባቸው እና መድሃኒት በሚወስዱ ሰዎች ላይ ተጽእኖ ፈጥሯል ይላሉ።
"ትልቁ ችግር የነበረው ስነ-ልቦናዊ ተጽእኖ ነው" የሚሉት አቶ ዳንኤል፤ ኮቪድ-19 ተጓዳኝ በሽታ ያለባቸውን ሰዎችን ይጎዳል በሚል በስጋት ወደ ጤና ተቋም ያለመምጣት ሁኔታዎች እንደነበሩ ይናገራሉ።
ከዚህ በተጨማሪም የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በማሰብ በመንግሥት የእንቅስቃሴ ገደብ መጣሉን ተከትሎ ከሚኖሩበት ርቀው መድሃኒት ይወስዱ የነበሩ ሰዎች የትራንስፖርት አማራጭ ባለማግኘት መድሃኒታቸውን መውሰድ የማይችሉት ሁኔታ ነበር።
"ለምሳሌ አዲስ አበባ ላይ ያለ ሰው አዳማ ሄዶ የሚወስድ ከሆነ . . . መንቀሳቀሱ ሲቆም መድሃኒቱን በትክክል ለመወሰድ መቸገር ነበር" ብለዋል።












