'የሰላም ድርድር የእኔ ጉዳይ አይደለም፤ ሥራዬ መዋጋት ነው' ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ

የፎቶው ባለመብት, FDRE Defense Force/fb
ቢቢሲ በአሁኑ ወቅት ወቅት እየተካሄደ ያለውን ጦርነት በተመለከተ በአገር መከላከያ ሚኒስቴር የሠራዊት ግንባታ ሥራዎች ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ ጋር ቆይታ አድርጓል።
ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ ሠራዊቱ እያካሄደ ስላለው ዘመቻ፣ ስለዘመቻ የመድረሻ ግብ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ በጦር ግንባር መገኘት፣ ጦርነቱን ለማብቃት የሚኖር ድርድርን እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ምላሽ ሰጥተውናል።

ቢቢሲ፡ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል እየተደረገ ባለው ጦርነት ዙሪያ ለውጦች መኖራቸው ይታወቃል። አሁን እስከምንነጋገርበት ሰዓት ድረስ ያሉ አዳዲስ ለውጦችን እስቲ ይንገሩን።
ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ፡ ወያኔ ያደራጀው ሰራዊት አዲስ አበባ ገብቼ ኢትዮጵያን እበትናለሁ በሚል ሂሳብ እስከ ሰሜን ሸዋ የተወሰኑ አካባቢዎች ድረስ ገብቶ እንደነበር ይታወቃል። በመከላከል ማዳከም ከዚያም በማጥቃት ለመደምሰስ በሚለው መርህ መሰረት። ይህንን ኃይል ለተከታታይ አንድ ወር መከላከል አድርገናል።
ለማጥቃት የሚያስችለንን ተገቢ የሆነውን ዝግጅት በመከላከል ውስጥ ሆነን አድርገናል። ሰሞኑን የማጥቃት እርምጃ ወስደናል። በዚህ እርምጃ ሰሜን ሸዋ የነበረውን የጠላት ኃይል አባረናል። በጋሸና፣ በደቡብ ወሎ፣ በወረ ኢሉ እንዲሁም በምሥራቅ ከጭፍራ አልፈን በዋናው መስመር በባቲ በኩል የነበረውም እንደዚሁ። ነገ (አርብ) ባቲ፣ ደሴ፣ ኮምቦልቻም አንድ ላይ ይያዛሉ የሚል ግምት አለ። ይሄ ነው ሰሞኑን ያለው። ይህም በዕቅድ የተደረገ ነው።
ቢቢሲ፡ ይህ አሁን እየታየ ያለው ውጤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሲቪል ኃላፊነታቸውን ትተው ወደ ጦር ግንባር ከመሄዳቸው ጋር ይያያዛል?
ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ፡ አዎ። ይያያዛል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደዚያ መሄድ የሠራዊቱን የመስራት አቅም በከፍተኛ ደረጃ ነው የጨመረው። አንደኛ የአገሪቱ መሪ ናቸው። እንዲሁም በጣም ተወዳጅ እና የተከበሩ ናቸው። ታታሪ ሠራተኛ፣ ሕዝብን የሚያፈቅሩ እና ትንሽ ትልቁንም በእኩል የሚያከብሩ በመሆናቸው መቼም ከህሊናው ጋር የሚኖር የማይወዳቸው የለም።
በሠራዊታችንም በጣም የተወደዱ እና የተከበሩ ናቸው። እንዲህ አይነት ሰው አይደለም ጦር ሜዳ የሆነ ትንሽ ነገርም እሱ ቀድሞ ልስራ ሲል፣ ሁሉም ተሻምቶ ነው የሚሰራው። በጦር ሜዳ ደግሞ እንዲህ የምናከብረው እና የምንወደወው ሰው ሲመጣ እንሳሳለታለን።
ሁለተኛ ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የኃላፊነት ስሜት እንዲሁም የሥራ ሞራልን ጨምሯል። ተጽዕኖ የመፍጠር ብቃት እና የአመራር ብቃቱ ታክሎበት እነዚህን የሰማናቸውን ድሎች አምጥተዋል።
ቢቢሲ፡ 'ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀድሞውንም የጦሩ አዛዥ አይደሉም ወይ? አሁን ወደ ውጊያ መሄዳቸው አዲሱ ነገር ምንድነው?' የሚሉ ሃሳቦች ይነሳሉ። የእርስዎ ምላሽ ምንድነው?
ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ፡ ቢሮ ሆኖ መምራት እና ግንባር ላይ መስመር ገብቶ ተኩስ ያለበት ቦታ ላይ ከሠራዊቱ ጋር ቆሞ መምራት የሰማይ እና የምድር ያህል ልዩነት አለው።
አይደለም ጠቅላይ ሚኒስትር በእኛ ደረጃ እና ከእኔ በታችም ዝቅ ብሎ ከአባላት ጋር ስንገናኝ እና ሥራውን አብረን ስንሰራ ሰዉ በብዙ እጥፍ ነው ሥራውን የሚያከናውነው። ይህ በሥራ አመራር ንድፈ ሃሳብም የታወቀ ነው።
ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጦርሜዳ ነው የገቡት ቢሮ አይደለም የተቀመጡት። ቢሮ ተቀምጠውም መርተው ድል አድርገዋል። ያው የምታውቁት ነው ወያኔ በ15 ቀን ድባቅ ተመቷል። በእርግጥ ያን ጊዜ ቢሮ ሆነው መሩ ይባላል እንጂ ያኔም ቢሆን በቀጥታ እያዩ ነበር የሚመሩት። በድሮኖች የሚሆነውን እያዩ ነበር ትዕዛዝ ሲሰጡ የነበረው።
ቢቢሲ፡ በቀጥታ ማለት የአየር ጥቃቶች ሲደረጉ ይከታተሉ ነበር ማለት ነው? ምን ማለት ነው?
ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ፡ ውጊያ ሲደረግ በስክሪን ሲቺዌሽን ሩም ሆነው ይከታተላሉ። በየትም አገር ይደረጋል። ውጊያዎች ትራንስሚት ይደረጋሉ (ይተላለፋሉ) ወደ ቢሮዎች፤ ከዚያም ይታያል ውጊያው።
ስለዚህ በዚያ አይነት መንገድ ነው ባለፈው ሲመሩ የነበረው። አሁን ደግሞ ልዩነቱ በአካል ነው የሄዱት። በአካል ሲሆን ደግሞ እያንዳንዱን ነገር ያያሉ፣ እያንዳንዱን የሠራዊት አባል እየሄዱ ያገኛሉ፣ ያናግራሉ፣ የሚሰሩትን ይነግሯቸዋል።
ይሄ የሥራ ሞራልን ያስነሳል። ስለዚህ ድሮም አዛዥ ናቸው አሁንም አዛዥ ናቸው የሚሉ ሰዎች፣ ውጊያ ያለበት ቦታ መሄድ እና ቢሮ ሆኖ መምራትን ያለመገንዘብ ይመስለኛል።
ቢቢሲ፡ ትላንት ከትግራይ አማጺያን ዘንድ የተሰጠ መግለጫ አለ። ይህም በአማራ ክልል ተይዘው ከነበሩ ቦታዎች በታክቲካዊ ውሳኔ ሠራዊቱ ለቆ ወጥቷል የሚል ነው። እናንተ ደግሞ በውጊያ ነው ያስለቀቅነው እያላችሁ ነው።
ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ፡ ታዲያ ምን እንዲሉ ነው የሚጠበቀው። በአቅማቸው በጉልበታቸው አይደለም እዚህ የደረሱት። በላኳቸው ሰዎች ጉልበት እና አቅም ነው እዚህ የደረሱት። ስለዚህ ጌቶቻቸው ለማስደሰት ምን ይበሉ?
ሁለተኛ ነገር እነሱ እኮ አዲስ አበባ ለመግባት በቀናት ሳይሆን ሰዓታት ነበር ሲቆጥሩ የነበሩት። አንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን እኮ አዲስ አበባ ተከባለች፣ ሊገቡ ነው የሚል ዘገባ ሲያስተላልፉ ነው የነበሩት። እነዚህ ሰዎች ተሸነፍን ሊሉ አይችሉም።
ስለድርድር ሲነሳ እኮ "መንግስት የለም ጦርነቱ አልቋል፣ ከማን ጋር ነው የምንደራደረው" ብሏል። አሁን እነሱ ባልጠበቁት መንገድ የማጥቃት ጎርፍ ሲወስዳቸው ሊሉ የሚችሉት ይህንን ነው። ታዲያ ለምን በጽሁፍ መግለጫ አወጡ። ለምን እንደድሮው ጻድቃን የሚባለው ወይም የእነሱ ሰዎች ወጥተው መግለጫ አይሰጡም?
ስለመኖራቸውም እጠራጠራለሁ፤ ሁለተኛ ደግሞ ያንን ለማድረግ ሐፍረት ይዟቸዋል። ሐፍረት የያዛቸው ስለጌቶቻቸው ነው። በዚህ ጉዳይ ትልልቆቹ ምዕራባዊያን ናቸው የሚያፍሩበት። ሊሉ የሚችሉት አልተሸነፍንም ለቀቅን ነው። መልሰን እናጠቃለን የሚል ቃል ለመግባት የተደረገ ነው።
ነገር ግን በሳተላይት ይከታተሉናል ሲሉ ነበር። ስለዚህ ከየት ቦታ እንደወጡ በደንብ ያያሉ። ስለዚህ ተመትተው እንደወጡ እነሱ ቢክዱም ጌቶቻቸው ያውቃሉ። ከአማራ ክልል ለቀን ወጣን ካሉ ከአፋር ክልልስ ይህንን ሁሉ መሬት እንዴት አድርገው ለቀቁ? ጭፍራ፣ ቡርቃ፣ ጪፍቱ አፋር ናቸው። ይሄንን ሁሉ መሬት እንዴት አድርገው ነው የለቀቁት። አመኑም አላመኑም የሆነው ይሄ ነው።
ቢቢሲ፡ ሌላው በሠራዊቱ ዙሪያ በተለያዩ መንገድ ሲነሱ የነበሩ ነገሮች አሉ። የመጀመሪያው በሠራዊቱ ውስጥ ክፍፍል አለ የሚል ነው። በርግጥም ክፍፍሎች ታይተዋል?
ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ፡ የተከፋፈለ ሠራዊት እንደዚህ አይነት ድል አያመጣም። ቢከፋፈል ኖሮ አዲስ አበባ ለመድረስ 200 ኪሎ ሜትር አካባቢ የራቀ እና ዛሬ ነገ እገባለሁ ያለ እሱን በመከላከል በቂ ዝግጅት አድርጎ ባዘጋጀው ኃይል ጠራርጎ ያወጣው ይሄ ተከፋፈለ የሚባለው ሠራዊት ነው።
ስለዚህ አንደኛው ነጥብ በሰራዊቱ ውስጥ መከፋፈል ሃሳቡም የለም የሚለው ነው። ድሮ መከፋፈል ነበር። ወያኔ ነው የሚከፋፍለው። የበኩር ልጅ እና የጉዲፈቻ ልጅ ነው የነበርነው በሠራዊቱ ውስጥ። የበኩር ልጅ እንደፈለገ የሚሆን የጉዲፈቻ ልጅ ደግሞ ቁራሽ እንጀራ የሚወረወርለት አይነት ማለት ነው። ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች እንደዚያ ነበሩ። ያኔ ነው መከፋፈል፤ አሁን አይታሰብም።
ቢቢሲ፡ በሠራዊቱ ውስጥ ባሉ ሰዎች የመፈንቅለ መንግሥት እንቅስቃሴ ነበረ የሚለ ነገር ነበረ። ይህ በእርግጥም ተፈጥሯል?
ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ፡ ይህ በፍጹም የማይቻል ነው። እኔ እስከማውቀው ድረስ መፈንቅለ መንግሥት የሚያስብ እና ለዚህ የሚነሳ ጭንቅላት ያለው ሰው የለም በእኛ ውስጥ። ማሰብ ሳይሆን በዚህ ጉዳይ ላይ ተነስቶ የሚነጋገር ሰው የለም። እያንዳንዳችን አብረን ያደግን የምንተዋወቅ ሰዎች ነን።
የመፈንቅለ መንግሥቱ ውጤት ምንድነው የሚሆነው? ከዚያስ በኋላ? የሚለውን እናውቃለን። በእምነት ደረጃ መፈንቅለ መንግሥት አንድን አገር አይለውጥም የሚል በጣም የጸና እምነት ያለው ሰው ነው ሠራዊቱን የሚመራው።
በመፈንቅለ መንግሥት ሳይሆን ሕዝብ ራሱ የፈለገውን ሰው ያስቀምጥ፤ ጉዳያችን አይደለም። የእኛ ሥራ አገርን መጠበቅ ነው።
ስለዚህ ይህ የሚቻል አይደለም፣ አይታሰብምም፣ አልተደረገም፣ ውሸት ነው። በዙ ነገር ሰምቻለሁ እኔም። በዚህ መንገድ ምን ሲባል እንደነበረ። እነ እገሌ እንደዚህ አደረጉ፣ እንደዚህ ናቸው፣ ከወያኔ ብር የተቀበሉ እና የተለያዩ ነገሮች ሲባሉ ሰምቻለሁ።
እንደዚህ አይነት ሃሳብ በሠራዊቱ ውስጥ እንዲገባ፣ ያላሰበም እንዲያስብ ለማድረግ በቀጥታ የሚመጣ ሃሳብ ነው። የእኛ ሰው ደግሞ የጠላትን ሃሳብ አስተጋብቶ ይኼው አንቺ በፊት ለፊት እንድትጠይቂኝ አደረገ።
ቢቢሲ፡ በቀጣይ ቀናት ወደ ደሴ እንደምታመሩ ገልጸውልኛል። ወደ መቀሌ የማምራት እቅድ አላችሁ?
ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ፡ ይህ ወታደራዊ ጉዳይ ነው። እኛ እዚህ ጋር እንቆማለን አንልም። ወታደራዊ ሁኔታው ነው የሚወስነው። ጦርነት በእርግጠኝነት የሚነገር ነገር አይደለም። አንሰርቴይኒቲ (የማይገመቱ ነገሮች) የሞላበት ነው። ስለዚህ በቀጣይ የሚፈጠረው ነገር ነው የሚወስነው። ነገር ግን እኛ አንቆምም።
ያው ደረጃ በደረጃ ወያኔ የያዛችውን ቦታዎች እያስለቀቅን እና እየደመሰስን እንቀጥላለን። መቀሌ ነው የምንቆመው? የት ነው የምንቆመው? ለሚለው፤ የምንቆም አይደለንም። አሁን ግን እቅዳችን እዚህ ድረስ ነው የሚል ነገር የለንም። ወያኔን የገባበት ገብተን እስከምናጠፋ ድረስ እንቀጥላለን።
ቢቢሲ፡ ወታደራዊ አመራር ነዎት። ነገር ግን ቅድምም ግጭቱ በሰላም ለመጨረስ የሚደረጉ ጥረቶች እንዲቀጥሉ እና ይህ ጦርነት በሰላም እንዲፈታ በእናንተ በኩል ቁርጠኝነቱ አለ?
ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ፡ እኔ ስለሰላም ድርድር ጉዳዬ አይደለም። መዋጋት ነው ሥራዬ። ከፈለጉ በሰላም ይጨርሱ ከፈለጉ ይደራደሩ። ይህንን ፖለቲከኛ ነው የሚያውቀው። በእኔ በኩል ግን ፊት ለፊቴ ያለ ጠላት አለ፣ እሱን ደምስስ ተብያለሁ፣ የገባበት ገብቼ አጠፋዋለሁ።
በቃ አቁም በሰላማዊ መንገድ እንጨርሳለን፣ ድርድር ጀምረናል እና አቁም ሲባል አቆማለሁ። ይኼው ነው። ቢደራደሩ ጥሩ ነው አይደለም የሚል አስተያየት መስጠት የእኔ ኃላፊነት አይደለም። ሥራዬም አይደለም መርሁም አይደለም።















