በመንግሥት ቁጥጥር ስር በገቡ አካባቢዎች የሰዓት እላፊ ገደብ ተጣለ

የመንግሥት ኃይሎች

የፎቶው ባለመብት, Government Communication/fb

እየተካሄደ ባለው ጦርነት በኢትዮጵያ መንግሥት ኃይሎች ቁጥጥር ስር በዋሉ አካባቢዎች ላይ የሰዓት እላፊ ገደብ መጣሉን በመላው አገሪቱ የተጣለውን የአስችኳይ ጊዜ አዋጅ የሚቆጣጠረው ዕዝ አስታወቀ።

ዕዙ እንዳለው በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ስር ቆይተው በመንግሥት ቁጥጥር ስር በገቡ በአካባቢዎች ሰላምንና ፀጥታን ለማስፈን እንዲሁም የሕዝብን ደኅንነትና ንብረት ለመጠበቅ ሲባል ላልተወሰነ ጊዜ የሰዓት እላፊ ገደብ ተጥሏል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚቆጣጠረው ዕዝ በርካታ ቦታዎች በመንግሥት ኃይሎች ቁጥጥር ስር መግባታቸው መገለጹን ተከትሎ ረቡዕ ምሽት ኅዳር 22/2014 ዓ.ም እንዳሳወቀው፤ በአካባቢዎቹ ከምሽት 12 ሰዓት አስከ ንጋት 12 ሰዓት ድረስ የሚቆይ የሰዓት እላፊ ተጥሏል።

በዚህም መሠረት ስለተጣለው የሰዓት እላፊ ገደብ በየአካባቢዎቹ ያሉ የመንግሥት የፀጥታ አካላት ለሕብረተሰቡ እንዲያሳውቁና ተፈጻሚነቱን እንዲከታተሉ ኃላፊነቱ ተሰጥቷቸዋል።

ዕዙ ጨምሮም በመንግሥት ቁጥጥር ስር በገቡት አካባቢዎች ከፀጥታ ኃይሎችና በክልሉ መንግሥት የሚመደብ ሲቪል አስተዳደር ጥምር ኮሚቴ በአስቸኳይ እንዲቋቋም ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ይህ ኮሚቴም በህወሓት ኃይሎች በመንግሥት ተቋማት፣ በግለሰብ ንብረቶች፣ በማኅበራዊ ተቋማትና በመሠረተ ልማቶች ላይ የደረሱ "ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመቶችን የሚያሳዩ ማስረጃዎች እንዳይጠፉ እንዲጠበቅ፣ በተገቢው መንገድ እንዲመዘግብ፣ ማስረጃዎችንም እንዲሰንድ" እንዲሁም የፍትሕ አካላት ማስረጃዎቹን በማደራጀት ለሚመለከተው አካል እንዲያስረክቡ ታዘዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም የወጣው ዝርዝር መመሪያ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በመላው አገሪቱ ወይም በተወሰኑ የአገሪቱ ክፍሎች ላይ የሰዓት እላፊ ገደብ የመጣል ሥልጣንን ይሰጣል።

በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ጦርነት መባባሱን ተከትሎ ከጥቅምት 23/2014 ዓ.ም ጀምሮ በመላው ኢትዮጵያ ተፈጻሚ እንዲሆን በሚኒስትሮች ምክር ቤት የደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለስድስት ወራት የሚቆይ ነው።

ይህንን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚከታተለውና የሚያስፈጽመው 'የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ' የተባለው አካል ነው። ዕዙ በአገሪቱ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም የሚመራ ሲሆን የተለያዩ አካላትን በማካተት ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መሆኑ ተገልጿል።

አንድ ዓመት ያለፈውና ከትግራይ ባሻገር ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተስፋፋው ጦርነት አሁንም የቀጠለ ሲሆን ካለፈው ሳምንት ጀምሮ መንግሥት በህወሓት አማጺያን የተያዙ አካባቢዎችን ለማስለቀቅ የተጠናቀረ ዘመቻ እያካሄደ ይገኛል።

በዚህም ታሪካዊቷን የላሊበላ ከተማን እንዲሁም ቁልፍ ናቸው የሚባሉትን በአፋርና በአማራ ክልል የሚገኙትን ጭፍራንና ጋሸናን ጨምሮ በርካታ ስፍራዎችን የመንግሥት ኃይሎች መቆጣጠራቸውን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ማስታወቁ ይታወሳል።