የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የጣላቸው ክልከላዎችና ግዴታዎች ምንድን ናቸው?

አዲስ አበባ ከተማ

የፎቶው ባለመብት, Adugent

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በመላው ኢትዮጵያ ከጥቅምት 23/2014 ዓ.ም ጀምሮ ተፈጻሚ እንደሚሆን የደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለስድስት ወራት የሚቆይ ነው።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚከታተለውና የሚያስፈጽመው 'የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ' ሲሆን ዕዙ በአገሪቱ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም የሚመራ ሲሆን የተለያዩ አካላትን በማካተት ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሆናል ተብሏል።

ይህ "በአገር ህልውና እና ሉዓላዊነት ላይ የተደቀነን አደጋ ለመከላከል የወጣ አዋጅ ቁጥር 5/2014" የባለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በውስጡ ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያዎችን ይዟል።

አዋጁ እንዲከናወኑ የሚጠበቁ ተግባራት ምንድን ናቸው፣ ምን ግዴታዎችን ጥሏል፣ ምን ይከለክላል?. . .

በአስቸኳይ ጊዜ የሚወሰዱ እርምጃዎች

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ የአገርን ህልውና እና ሉዓላዊነት እንዲሁም የሰላማዊ ዜጎችን ደኅነንት ለመጠበቅ አስፈላጊ ነው ብሎ ሲያምን፡

1. በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል መከላከያ ኃይልን ወይም የትኛውንም ሌላ የፀጥታ አካል በማሰማራት ሰላምና ፀጥታ እንዲያስክብሩ ትዕዛዝ ሊሰጥ ይችላል፤

2. እድሜያቸው ለወታደራዊ አገልግሎት የደረሱ እና የጦር መሳርያ የታጠቁ ዜጎች ወታደራዊ ስልጠና እንዲወስዱ፣ ወታደራዊ ግዳጅ እንዲቀበሉ ወይም ይህን ማድረግ የማይችሉ ሲሆን በአማራጭ ትጥቃቸውን ለመንግሥት እንዲያስረክቡ ሊያዝ ይችላል፤

3. የሰዓት ዕላፊ ገደብ ሊወሰን ይችላል፤

4. ማናቸውም የሕዝብ የመገናኛ እና የሕዝብ መጓጓዣ ዘዴ እንዲዘጋ ወይም እንዲቋረጥ ሊያዝ ይችላል፤

5. ከሽብር ቡድኖች ጋር ይተባበራል ብሎ ምክንያታዊ በሆነ መልኩ የተጠረጠረ ማንኛውንም ሰው ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ በቁጥጥር ሥር ለማድረግ፣ ይህ አዋጅ ተፈጻሚ ሆኖ ባለበት ጊዜ ድረስ ይዞ ለማቆየት ወይም በመደበኛ ሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማድረግ ይችላል፤

6. ከሽብር ቡድኖች ጋር ይተባበራል ብሎ ምክንያታዊ በሆነ መልኩ የተጠረጠረ ማንኛውንም ሰው ወይም ድርጅት ንብረት የሆነን ማንኛውንም ቤት፣ ህንጻ፣ ቦታ፣ መጓጓዣ ለመበርበርና እንዲሁም ማንኛውንም ሰው ለማስቆም፣ ማንነቱን ለመጠየቅ፣ ለመፈተሽ ይችላል፤ በብርበራ ወይም በፍተሻ የተያዙ የጦር መሳሪያዎችን መውረስ ይችላል፤

7. ለተወሰነ ጊዜ መንገዶችን፣ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ለመዝጋት እንዲሁም ሰዎች ለጊዜው በተወሰነ ቦታ እንዲቆዩ፣ ወደ ተወሰነ አካባቢ እንዳይገቡ ወይም ከተወሰነ ቦታ እንዲለቀቁ ለማዘዝ ይችላል፣

8. ከፍተኛ የፀጥት ችግር እና ስጋት በተፈጠረባቸው የአገሪቱ ክፍሎች የአካባቢ አመራር መዋቅርን በከፊልም ሆነ በሙሉ፣ ማገድ፣ መለወጥ እና በሲቪልም ሆነ በወታደራዊ አመራር መተካት ይችላል፤

9. በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለሽብር ቡድኖች የሞራልም ሆነ የቁስ ድጋፍ ያደርጋል ብሎ የሚጠረጥረውን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት እንቅስቃሴ በሚመለከተው ባለሥልጣን በኩል እንዲታገድ ወይም ፍቃዱ እንዲሰረዝ ሊያዝ ይችላል፤

10. በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለሽብር ቡድኖች የሞራል ድጋፍ ያደርጋል ብሎ የሚያምነውን የመገናኛ ብዙኃንን ወይም ጋዜጠኛ በሚመለከተው ባለሥልጣን በኩል እንዲታገድ ወይም ፍቃዱ እንዲሰረዝ ሊያዝ ይችላል፤

የተከለከሉ ተግባራት እና ግዴታዎች

1. ሁሉም ሰው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ በአዋጁ መሰረት የሚያወጣቸውን መመሪያዎች እና የሚሰጣቸውን ትዕዛዞች የመቀበል ግዴታ አለበት።

2. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዙን እንቅስቃሴ እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አላማ የሚቃረን፣ የሚቃወም እና ለሽብር ቡድኖች አላማ መሳካት አስተዋፅኦ የሚያደርግ፣ የሽብር ቡድኖችን የሚያበረታታ፣ ሰላማዊ ዜጎችን የሚያሸብር ንግግር በማንኛውም መንገድ ማድረግ ወይም ማሰራጭት የተከለከለ ነው።

3. በየትኛውም መንገድ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለሽብር ቡድኖች የገንዝብ፣ የመረጃ፣ የቁስም ሆነ የሞራል ድጋፍ ማድረግ የተከለከለ ነው።

4. አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዙ በተዋረድ ውክልና ከሰጣቸው አካላት ፈቃድ ውጪ ማንኛውንም የአደባባይ ስብሰባ ወይም ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ የተከለከለ ነው።

5. ከመከላከያ፣ ከፌዴራል ፖሊስ ወይም ሌሎች ፈቃድ ከሚሰጣቸው የፀጥታ አካላት ወይም ከእነዚህ አካላት እውቅና እና ፈቃድ ውጭ ማናቸውንም የጦር መሳርያ ይዞ መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው።

6. በከተሞች አካባቢ የነዋሪ መታወቂያ የመንጃ ፈቃድ፣ የሠራተኛ መታወቂያ፣ ፓስርፖርት ወይም ከእነዚህ ተመጣጣኝ የሆነ መታወቂያ ሳይዙ መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው። [ዜጎች እነዚህን ሰነዶች የሚያገኙበት መንገድ ተመቻችቷል]

7. ማንኛውንም ወሳኝ በሆነ የአገልግሎት ዘርፍም ሆነ በምርት ሂደት ላይ የሥራ ማስተጓጎል ወይም የኢኮኖሚ አሻጥር መፈፀም የተከለከለ ነው።

8. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈፃፀም ሰበብ በማድረግ የግል ጥቅም ለማግኘት ስልጣንን አላግባብ መጠቀም፣ ምክንያታዊ የሆነ ጥርጣሬ ሳይኖር ሆን ብሎ ዜጎችን ማሰር ወይም መሰል እርምጃ መውሰድ የተከለከለ ነው።

ተፈፃሚነታቸው የታገዱ ሕጎች

1. በዚህ አዋጅ በተሸፈኑ ጉዳዮች ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እሲኪጠናቀቅ ድረስ የትኛውም የዳኝነት አካል ስልጣን አይኖረውም።

2. በቪዬና ኮንቬንሽን የተመለከተው የዲፕሎማቲክ መብት እንደተጠበቀ ሆኖ ከዚህ አዋጅ ጋር የሚቃረኑ የፍሬ ነገርና የሥነ ሥርዓት ሕጎች ይህ አዋጅ በሥራ ላይ በሚውልበት ጊዜ ተፈፃሚነታቸው ታግዶ ይቆያል::

የወንጀል ተጠያቂነት

1. የዚህን አዋጅ ድንጋጌዎች እና በአዋጁ መሰረት የወጡ መመሪያዎችን ተላልፎ የተገኘ ማንኛውም ሰው እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት ወይም እንደጥፋቱ ክብደት እስከ አስር ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል።

2. የዚህን አዋጅ ድንጋጌዎች እና በአዋጁ መሰረት የወጡ መመሪያዎችን በመተላለፍ የተፈፀመው ወንጀል በሌሎች ሕጎች ከዚህ ከፍ ያለ ቅጣት የሚያስከትል ከሆነ የከበደው ቅጣት ተፈጻሚ ይሆናል።

3. በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት የተፈፀሙ የአዋጁ እና በአውጁ ማዕቀፍ የወጡ መመሪያዎች ጥሰቶች የአዋጁ ተፈጻሚነት ጊዜ ቢያበቃም፣ የሚያስከትሉት የወንጀል ተጠያቂነት በመደበኛው የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ መሰረት ይቀጥላል።