በትግራይ ያለው የረሃብ አደጋ እና የመድኃኒት እጥረት

እርዳታ የሚጠብቁ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ህይወት በርኸ ባለትዳርና የሦስት ልጆች እናት ነች። ሁለቱን ልጆቿን ስታሳድግ ምንም ዓይነት የጤና እክል ገጥሟቸው አያውቅም።

አንድ ዓመት ከአራት ወር የሆናት ሦስተኛ ልጇ ኤደን ገብረጻዲቅ ግን አይደር ሆስፒታል ተኝታ ሕክምና እየተከታተለች ነው።

ህይወት፣ መቀለ በሚገኘው አይደር ሆስፒታል ተኝታ እየታከመች የምትገኘውን ልጇን፣ ዓይን ዓይን እያየች በህይወት እንድትተርፍላት ፈጣሪዋን ትማጸናለች።

መድህን ወደ ሆስፒታሉ የመጣችው በከፍተኛ ሁኔታ በረሃብ ተጎድታ ነው።

አቶ ግደይ መረሳ፣ በቆላ ተምቤን፡ ወረዳ ቀይሕ ተኽሊ፡ እንዳባና የገጠር ጣቢያ ነዋሪ ናቸው።

አካባቢው ከፍተኛ ጦርነት ከተደገባቸው የትግራይ አካባቢዎች መካከል አንዱ ነው።

ብዙዎቹ የገጠር ነዋሪዎች ለወራት ያህል ቤታቸውንና ንብረታቸውን ጥለው ኑሯቸውን በየተራራውና ጫካ አድርገው ነበር።

አቶ ግደይ በሰኔ ወር መጨረሻ ወደ ቤታቸው ቢመለሱም፡ የስድስተኛ ክፍል ተማሪ የሆነች ልጃቸውን በጽኑ ታመመችባቸው።

"በየበርሃው ቆይተን ሰኔ ወር ላይ ስንመለስ እዚህ ችግር ውስጥ ወደቅን። ልጄ ታመመችብኝ። በፊት ጤነኛ ነበረች" ይላሉ።

መጀመርያ በአቅራቢያ ወደ ሚገኘው ጤና ጣቢያ ቢወስዷትም መድኃኒት ማግኘት አልተቻለም።

ልጃቸው የታመመችው በዋናነት የምግብ ዕጥረት የተነሳ ቢሆንም፣ በተጨማሪ የልብ ችግር እንዳለባት ተነግሯቸዋል።

የምግብ እና የመድኃኒት ዕጥረት የሚፈትናቸው ነዋሪዎች

ህይወት ልጇ ኤደን ለሳምንታት የሕክምና እርዳታ ሲደርግላት የቆየች ሲሆን "በምግብ ዕጥረት የመጣ በሽታ እንደሆነ ነግረውኛል። እኔ እንጃ፤ እነሱ ግን ባለቸው አቅም ሁሉ እየረዱን ነው" ትላለች።

አክላም "በጥሩ ሁኔታ ነበር ልጆቻችን የምናሳድገው። ኑሯችን ከሞላ ጎደል ጥሩ ነበር። አሁን ግን የምንበላው የለንም። ልጃችንም በዚህ ምክንያት ነው ለዚህ የተዳረገችው" ብላለች።

"አሁንም ግን መድኃኒት ማግኘት አልተቻለም፤ ከሆስፒታሉ ውጪ እያፈላለግን ነው" የሚሉት አቶ ግደይ መድኃኒት ቢገኝ እንኳ የመግዛት አቅም እንደሌላቸው ይናገራሉ።

የመቀለ ከተማ ነዋሪዋ ህይወት በበኩሏ "ሰርተን እንዳንበላ ሥራ የለም። ሁሉም ተዘግቷል። እኔ ቁጭ ብዬ ነው ምውለው፤ ባለቤቴም እንደዚሁ ቤት ቁጭ ብሎ ነው የሚውለው፤ ምን እናብላቸው?" በማለት የችግሯን ተደራራቢነት ታስረዳለች።

አንድ ዓመት ሊሞላው የቀናት እድሜ ብቻ በቀረው የትግራይ ጦርነት ምክንያት በክልሉ በርካታ ሰብዓዊ ጉዳቶች ደርሰዋል።

ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት ሰዎች በጅምላ ተገድለዋል፤ ነፍሰ ጡር ሴቶች ሳይቀሩ በጅምላ ተደፍረዋል፣ አብያተ ክርስትያናት እና ታሪካዊ ስፍራዎች ወድመዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለው ከሆነ በክልሉ ከ5.2 ሚልዮን በላይ ሕዝብ አስቸኳይ እርዳታ የሚጠባበቅ ሲሆን ግማሽ ሚልዮን ያህሉ የክልሉ ሕዝብ ደግሞ ለከፍተኛ ረሃብ ተጋልጧል።

የኢትዮጵያ መንግሥትም 'ረሃብን እንደ የጦር መሳርያ እየተጠቀመበት ነው' ተብሎ ይወነጀላል።

በትግራይ ያለች እናት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የመድኃኒት እጥረት እና ረሃብ

ህይወት፣ ልጇ በሚደረግላት የህክምና እርዳታ ትድናለች የሚል ተስፋ አላት።

ይሁን እንጂ ሆስፒታሉ በተለይ ባለፉት አራት ቀናት የመድኃኒት ዕጥረት እንዳጋጠመው ተነግሯታል።

ልጇን በሆስፒታሉ በማስታመም ላይ የምትገኘው ህይወት፣ አሁን እጅግ ያስጨነቃት ይሄው ነው።

"መድኃኒት የለንም፤ ከውጪ ግዙ ብለውናል። ነገር ግን አቅም የለንም። ከየት አምጥተን እንገዘዋለን?" ትላለች።

ህይወት ልጇ ኤደን፣ አንድ ቀን መድኃኒት እየወሰደች ሌላ ቀን ደግሞ እየዘለለች እስከ አሁን ድረስ በህይወት መቆየቷን ትናገራለች።

አይደር ሆስፒታል በትግራይ ክልል ከሚገኙ ሆስፒታሎች መካከል ትልቁ ሲሆን፣ ሠራተኞቹ ላለፉት አራት ወራት ደመወዝ ሳይከፈላቸው እንደሚሰሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሆስፒታሉ ከክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ለሚመጡ ሕክምና ሲሰጥ ቢቆይም በአሁኑ ወቅት የተለያዩ መሰረታዊ የመድኃኒት ቁሳቁሶችም እንዳለቀባቸው፤ የሆስፒታሉ ሠራተኞች ይገልጻሉ።

በቅርቡ የክልሉ ቴሌቪዥን ጣቢያ እንደዘገበው ከሆነ በሆስፒታሉ በብቸኝነት ሲሰጥ የነበረው የኩላሊት እጥበት በመድኃኒት እጥረት ምክንያት በመስተጓጎሉ ህክምና ሲከታተሉ የቆዩት 32 የኩላሊት ህሙማን ህይወታቸው ለአደጋ ተጋልጧል።

ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) የተሰኘው በሕክምና ላይ የተሰማራው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በትግራይ ክልል በሚገኙ የሕክምና ተቋማት ሦስት አራተኛዎቹ ላይ ሆን ተብሎ ዘረፋ እና ጥቃት ተፈጽሟል ሲል መጋቢት ወር ላይ ባወጣው ሪፖርት መግለፁ ይታወሳል።

'ቁርስ መብላት ቅንጦት ሆኖብናል'

ቀደም ሲል በግል ኮሌጅ መምህር የነበረው ገብረመድህን ባለፈው አንድ ዓመት ሥራ በመፍታቱ እናቱን፣ እህትና ወንድሙን ጨምሮ ከአራት የቤተሰቡ አባላት ጋር ለችግር መጋለጣቸውን ይናገራል።

በመቀለ ስላለው የኑሮ ውድነት ሲያስረዳም "እንጨት እንኳ በውድ ነው የሚገዛው" ይላል።

ባንክ የነበረውን ተቀማጭ ገንዘብ በማውጣት እንዳይጠቀም ባንኮች አገልግሎት በማቋረጣቸው ተቸግሯል።

በአንድ የፌደራል መሥሪያ ቤት ውስጥ ትሰራ የነበረችው እህቱ ደመወዝ ከተከፈላት ስድስት ወር እንደሆናት ጨምሮ ተናግሯል።

"እናቴም ቤት ታከራይ ነበር፤ አሁን ተከራዮቹ መክፈል ስለማይችሉ ቤት ኪራይ ተቀብላቸው አታውቅም" የሚለው ገብረመድህን፡ ለመኖር መሰረታዊ የሚባሉ ነገሮች ዋጋቸውን ሰማይ መድረስ ብቻ ሳይሆን አይገኙም ይላል።

"ያለ ዘይትና በርበሬ በተሰራ ወጥ መብላት ከጀመርን ከሁለት ወር በላይ ሆኖናል። ቁርስ መብላት እንደቅነጦት ነው የምናየው" ይላል።

ብዙ ጊዜ በቀን አንዴ እንደሚመገቡም ይናገራል።

በተጨማሪ እናቱ እና ወንድሙ ላለባቸው ቋሚ የጤና ችግር ሲወስዱት የነበረው መድኃኒት ስላቆሙ ከፍተኛ የጤና ችግር ላይ መውደቃቸው ያሳስበዋል።

"ይህንን የእኛ ኑሮ የተሻለ የሚባለው ነው፤ የብዙ ሰው ኑሮ ከዚህ በባሰ ነው። ብዙ ሰው መንገድ ላይ እጁ ለልመና ሲዘረጋ ታገኘዋለህ። ሁኔታው በዚሁ ከቀጠለ፤ በርካቶች በረሃብና በመድኃኒት እጦት ሊሞቱ ይችላሉ" ብሏል።

ከጦርነቱ እና ተያያዥ ጉዳዮች በአገሪቱ የዋጋ ንረት ከፍተኛ ቢሆንም፣ በትግራይ ክልል ግን አምስትና ስድስት ዕጥፍ መሆኑ ይነገራል።

የአንድ ኪሎ በርበሬ ዋጋ 800 ብር፣ የአንድ ኪሎ ሽሮ 180 ብር፣ የአንድ ኩንታል ጤፍ እስከ ሰባት ሺ ይደርሳል፤ እንዲሁም የአንድ ሊትር ዘይት ዋጋ 250 ብር መድረሱን ቢቢሲ ከአካባቢው ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

ፍትሃዊ ሕሩይ፣ በአሜሪካ አገር የሚኖር ወጣት ነው። ቀደም ሲል በተለያየ ምክንያት ለተቸገሩት በ'ጎ ፈንድሚ' ከውጭ እርዳታ በማሰባሰብ በመርዳት ይታወቅ ነበር።

አሁንም ይህንኑ በጎ ተግባር ለማድረግ ቢፈልግም ከዚህ ቀደም ሲረዳቸው የነበሩት ግለሰቦች፣ እንዲሁም በአክሱም ከተማ የሚገኙት ቤተሰቡ እና ዘመድ አዝማዶቹ ከሰኔ ወር ጀምሮ ያሉበትን ሁኔታም ማወቅ አልቻለም።

በክልሉ የስልክ እና የባንክ አገልግሎት ከተቋረጠጠ ወራት በመቆጠራቸው "በተለይ ተከታተይ መድኃኒት የሚያስፈልጋቸው ዘመዶቼ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ አላውቅም፤ በህይወት ይኑሩ አይኑሩም እርግጠኛ አይደለሁም" ብሏል ለቢቢሲ።

ህሙማን ሆስፒታል ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, Filmon

ወደ ጎረቤት ክልሎች የተስፋፋው ግጭት

ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የተጀመረው የትግራይ ጦርነት መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም አውጆ ክልሉን ለቅቆ ከወጣ በኋላ መልኩ ተቀይሯል።

የፌደራል መንግሥት ክልሉን ለቅቆ ሲወጣ ወቅቱ የግብርና መሆኑን በመጥቀስ ገበሬዎች ተረጋግተው እንዲያርሱ የሚል ምክንያት ሰጥቶ ነበር።

ሆኖም ግን የትግራይ አማፂያን ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ተዋጊዎቻቸውን በማንቀሳቀስ ጦርነቱን አስፋፍተውታል።

ይህንን ተከትሎ በአጠቃላይ በሰሜን ኢትዮጵያ እስከ 7 ሚልዮን ሰዎች አስቸኳይ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አሳውቋል።

በተጨማሪም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች እንደ አዲስ ተፈናቅለዋል።

በትግራይ ብቻ ከግማሽ ሚልዮን ሕዝብ በላይ ለረሃብ የተጋለጠ ሲሆን በአስቸኳይ እርዳታ ካልደረሰ የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ ሊያጋጥም እንደሚችል የተባበሩት መንግሥታት ለፀጥታው ምክር ቤት ገልጿል።

አንዳንድ ድርጅቶች ጦርነቱ ከተከሰተ ጥቂት ወራት ጀምሮ ትግራይ ላይ የ1977 ዓ.ም ዓይነት ረሃብ ሊከሰት ይችላል በማለት ስጋታቸውን ሲገልፁ ነበር።

በቤልጂየም የሚገኘው ገንት ዩኒቨርሲቲ ከመቀለ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባለፈው ሰኔ ወር ላይ በቴክኖሎጂ ታግዞ በሰራው ጥናት፣ ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ያልታረሰ መሬት ይታይ ነበር ብሏል።

አብዛኞቹ አርሶ አደሮች ንብረታቸውንና ሰብላቸውን መቃጠሉን እንዲሁም በሬዎቻቸው መታረዳቸውን ባዶ እጃቸውን መቅረታቸው የዚሁ ተቋም ጥናት ያመላክታል።

ሰኔ ወር ላይ አብዛኞቹ አርሶ አደሮች ወደ ማሳቸውን መሄድና ማረስ የሚጠበቅባቸው ወቅት ነበር። የህይወት ዋጋ የሚያስከፍል ቢሆንም፣ የሚቀጥለው ዓመት ሊገጥማቸው የሚችል ረሃብ ለመቋቋም ህይወታቸው መስዋዕት እያደረጉ አንዳንዴም በሌሊት [ወታደሮቹ ሳይነሱ] ለማረስ ተገድደዋል ይላል ጥናቱ።

በተለይ መንግሥትን ደግፈው በጦርነቱ የተሳተፉት የኤርትራ ወታደሮች እንዳያርሱ ይከለክሉ እንደነበር ቀደም ሲል ቢቢሲ ያነጋገራቸው አርሶ አደሮችን ገልጸው ነበር።

የኤርትራ መንግሥት ግን ክሱን ማስተባበሉ ይታወሳል።

በጥናቱ የተሳተፈው በዩኒቨርሲቲው የሦስተኛ ዲግሪውን እየሰራ የሚገኘው እምነት ነጋሽ፣ ገበሬዎቹ የተለያዩ ችግሮች ቢገጥሟቸውም፣ በራሳቸው ባህላዊ እውቀትና መላ ተጠቅመው የዝናቡ ወቅት እንዳያመልጣቸው ለማረስ ሞክረዋል ይላል።

በእርግጥ እንደ ከዚህ ቀደሙ ምርጥ ዘርና ማዳበርያ አለማግኘታቸው ለቢቢሲ ገልጿል።

አብዛኛው የክልሉ ወጣት ግጭቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ ጦርነቱን ተቀላቅሏል የሚለው እምነት፣ በዚህም ምክንያት ከ20 እስከ 30 በመቶ የክልሉ እርሻ የዘር ወቅት አልፎበታል ሲል ያስረዳል።

ጥናቱንም ጠቅሶ በአጠቃላይ ዘንድሮ በክልሉ ከ20 አስከ 50 በመቶ የእርሻ መጠን ብቻ ነው ምርት ሊሰጥ የሚችለው ይላል።

እንደ ጥናቱ ከሆነ በአብዛኛው ያልታረሰው በምዕራብ ትግራይ ላይ ያለው ሰፊ የእርሻ መሬት ሲሆን በተለይ በተከዜ ወንዝ ዳር የነበረው የመስኖ ሥራ ከሞላ ጎደል መቋረጡን ገልጿል።

በአሁኑ ወቅት የምዕራብ ትግራይ አካባቢ በአማራ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻዎች እና በኢትዮጵያ ወታደር ቁጥጥር ስር ይገኛል።

የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ምላሽ

የተለያዩ መንግሥታት፣ መንግሥት ለእርዳታ አቅርቦት መንገዱን ሙሉ ለሙሉ እንዲከፈት በተደጋጋሚ ሲወተውቱ ይደመጣል።

እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ ከሆነ ከሐምሌ ወር ጀምሮ ወደ ትግራይ በየቀኑ 100 የጭነት መኪኖች እንዲገቡ ወስኖ የነበር ቢሆንም እስከ አሁን ግን አስር በመቶ የሚሆነው ብቻ ማለፍ ችሏል።

የአሜሪካ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን በትግራይ ያለው ሁኔታ ካልተሻሻለ በሁሉም ተፋላሚ ወገኖች ላይ ማዕቀብ እንዲጣል የሚያስችል ትዕዛዝ ፈርመዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ መንግሥት ሰባት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ ኃላፊዎችን ከአገር እንዲወጡ አድርጓል።

የተመድ ዋና ጸሐፊው አንቶኒ ጉተሬዝ እንደሚሉት፤ ሰባቱ የተመድ ሠራተኞች በኢትዮጵያ መንግሥት 'ጣልቃ በመግባት' በሚል መባረራቸው የእርዳታ መስጠት ሂደቱን ያደናቅፋል።

ጉታሬዝ እንዳስጠነቀቁትም የእርዳታ ድጋፍና የረድኤት አቅርቦት ካልተሻሻለ በክልሉ ያለው ሁኔታ "የበለጠ እየተባባሰ ሊሄድ ይችላል።"

አክለውም "ችግሩን ለመቅረፍ አሁን የምንወስደው እርምጃ በበርካታ ሰዎች ሕይወት ላይ ትልቅ ልዩነትን ይፈጥራል" ብለዋል።

የዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር ኃላፊ ፒተር ሞውረር በቅርቡ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል እየተደረገ ያለው ጦርነት የሰብአዊ እርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር በየቀኑ እንዲጨምር እያደረገ ነው።

"በጦርነቱ ተሳታፊ ለሆኑ አካላት መልዕክቱ ሁሌም ተመሳሳይ ነው። ለችግሩ አስቸኳይ ፖለቲካዊ መፍትሔ መስጠት ከግጭት ያወጣናል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የአሜሪካ የተራድኦ ተቋም (ዩኤስኤድ) ኃላፊ ረዳት የሆኑት ሳራ ቻርልስ የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲሁም የትግራይ ኃይሎች እርዳታ ሰጪ ተቋማት ተረጂዎች ጋር እንዲደርሱ ገደብ እንዲያነሱ ጠይቀዋል።

ሰብአዊ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ያለ ምንም ገደብ እንዲያልፉ እና የሰብአዊ እርዳታ በረራ ቁጥር እንዲጨምርም ጠይቀዋል። በረራው በቅርቡ መቋረጡን ይታወሳል።

"ለወራት ያህል ነዳጅ፣ ገንዘብ እና የመድኃኒት አቅርቦት በኢትዮጵያ መንግሥት በመታገዱ ምክንያት ሰብአዊ እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች የሚሰጡትን ድጋፍ ለመቀነስ ተገደዋል። ሆስፒታሎች እና የጤና ተቋማት መድኃኒት አልቆባቸዋል" ብለዋል።