የኢትዮጵያ ሠራዊት ድል እያስመዘገበ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከጦር ግንባር ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian state media
የኢትዮጵያ ሠራዊት በአማጺያኑ ተይዘው የነበሩ ቦታዎችን በማስለቀቅ ከፍተኛ ድል እያስመዘገበ መሆኑን በጦር ግንባር የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ።
ጦርነቱን ለመምራት ባለፈው ማክሰኞ ወደ ጦር ግንባር ያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከቀናት በኋላ የአገሪቱ ቴሌቪዥኖች በሰበር ዜና ባስተላለፉት አጭር መግለጫቸው ላይ ሠራዊታቸው በአሁኑ ጊዜ እያካሄደ ስላለው ዘመቻ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ጊዜው ሀገርን በመስዋዕትነት መምራት የሚያስፈልግበት ነው" በማለት እራሳቸው የአገሪቱ ሠራዊት በተሰለፈበት ግንባር በመገኘት ለመምራት "ወደ ትግሉ ሜዳ እዘምታለሁ" በማለት ነበር ባለፈው ማክሰኞ ወደ ጦር ግንባር ማምራታቸው የተነገረው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ጦር ግንባር ከተጓዙ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በቴሌቪዥን ቀርበው በአማርኛ እና በኦሮምኛ በሰጡት አጭር መግለጫ ሠራዊቱ በአፋር ክልል ካሳጊታ የተባለውን ስፍራ መቆጣጠሩን ገልፀው ቡርቃ እና ጭፍራን ደግሞ እንደሚቆጣጠሩ ተናግረዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በኋላ አርብ ምሽት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት እንዳስታወቀው የመንግሥት ኃይሎች ቡርቃን እና በባቲ ከተማ ዙሪያ ያሉ ተራሮችን መቆጣጠራቸውን እንዲሁም በአፋር በኩል ጪፍቱን፣ የጭፍራ ከተማንና አካባቢውን መያዙን አመልክቷል።
ከአንድ ዓመት በፊት ትግራይ ውስጥ ተቀስቅሶ ወደ አማራና የአፋር ክልሎች የተስፋፋው ጦርነት ሰፊ ቦታዎችን እየሸፈነ የህወሓት ኃይሎች ከሰሜን ወሎና ደቡብ ወሎ ባሻገር ወደ ሰሜን ሸዋ አካባቢዎች መንቀሳቀሳቸውን ተከትሎ ነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ጦር ግንባር ያቀኑት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጦር ግንባር እንደተናገሩት ሠራዊቱ በአማጺያኑ ተይዘው የነበሩ ቦታዎችን እያስለቀቀ መሆኑን አመልክተው "ጠላት ከእኛ ጋር ሊፎካከር የሚያስችለው ቁመና የለውም" ብለዋል።
የሠራዊታቸው ፍላጎት የአገሪቱን አንድነትና ነጻነት ማስጠበቅ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ "ይህ መስዋዕትነት እየተከፈለ ያለውም ይህንን ለማምጣት ነው" ብለዋል።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት 24/2013 ትግራይ ውስጥ የተቀሰቀሰው ጦርነት ለስምንት ወራት ተካሂዶ የአገሪቱ ሠራዊት የተናጠል የተኩስ አቁም አውጆ ከክልሉ መውጣቱን ካሳወቀ በኋላ ወደ አፋርና አማራ ክልሎች ተስፋፍቶ ቀጥሏል።
ጦርነቱ ለማስቆም በተለያዩ ወገኖች በኩል ጥረት እተደረገ ባለበት ጊዜ የህወሓት ኃይሎች ተጨማሪ አካባቢዎችን ለመያዝ ዘመቻቸውን ማጠናከራቸውን ተከትሎ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሠራዊቱን ለመምራት ወደ ጦር ግንባር ለመዝመት መወሰናቸውን ያስታወቁት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በጦር ግንባር በመገኘት ዘመቻውን ለመምራት መወሰናቸውን ተከትሎ የመንግሥት መደበኛ ሥራዎች በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እየተመሩ መሆናቸው ተገልጿል።
የህወሓት አመራሮች ተዋጊዎቻቸው ወደ አፋርና አማራ ክልሎች በመግባት ጥቃቱን የቀጠሉት መንግሥት በትግራይ ላይ ጥሎታል ያሉትን የእርዳታና ሌሎች አገልግሎቶች ዕገዳ እንዲነሳ ለማስገደድ ነው ቢሉም ጦርነቱ አድማሱን አስፍቶ ሰብአዊ ቀውሱም የበለጠ ተስፋፍቷል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለው ጦርነቱ በሚካሄድባቸው የሰሜን ኢትዮጵያ ክልሎች ውስጥ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ሰዎች እርዳታ እንደሚጠብቁና ግማሽ ሚሊዮን የሚደርሱት ደግሞ በረሃብ አፋፍ ላይ ይገኛሉ።
ይህንን ከባድ ሰብአዊ ቀውስ ያስከተለውን ጦርነት ለማብቃት የአፍሪካ ሕብረት እና አሜሪካ ልዩ መልዕክተኞችን ወደ ኢትዮጵያ በመላክ ጥረት ቢያደርጉም ውጤት ሳይገኝ ጦርነቱ ተባብሶ ቀጥሏል።













