የጠቅላይ ሚንስትሩን ውሳኔ ተከትሎ ታዋቂ ግሰለቦች ወደ ጦር ግንባር ለመዝመት እንደሚፈልጉ እየገለጹ ነው

ከግራ ወደ ቀኝ፡ አትሌት ኃይሌ፣ አትሌት ፈይሳ እና ክርስቲያ ታደለ

የፎቶው ባለመብት, BBC/AFP/Christian Tadele FB

የምስሉ መግለጫ, ከግራ ወደ ቀኝ፡ አትሌት ኃይሌ፣ አትሌት ፈይሳ እና ክርስቲያ ታደለ

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ጦር ግንባር እንደሚሄዱ መግለጻቸውን ተከትሎ ተዋቂ ግለሰቦች በተመሳሳይ ወደ ጦር ሜዳ እንደሚዘምቱ እየገለጹ ነው።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ከትናንት በስቲያ ባወጡት መግለጫ ወደ ጦር ግንባር በመሄድ የመከላከያ ሠራዊቱ ከህወሓት አማጺያን ጋር የሚያደርገውን ጦርነት እንደሚመሩ መግለጻቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ታሪክ ከሚያደንቃቸው የኢትዮጵያ ልጆች አንዱ ለመሆን የምታስቡ ሁሉ ለሀገራችሁ ስትሉ ዛሬውኑ ተነሡ፤ ግንባር ላይ እንገናኝ" በማለት ሌሎችም የእሳቸውን አርአያ እንዲከተሉ ጥሪ አቅርበዋል።

አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ተክትሎ ወደ አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ቃል ከገቡ ታዋቂ ሰዎች ዝርዝርን ተቀላቅሏል።

ኃይሌ ለብሔራዊው የቴሌቪዥን ጣቢያ ወደ ግንባር መሰለፍን ጨምሮ የሚጠበቅበትን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።

በዓለም የአትሌቲክስ ታሪክ ውስጥ ከታዩ ከዋክብት መካከል ከፊት የሚሰለፈው ኃይሌ ገብረሥላሴ በተለያዩ ርቀቶች በርካታ ክብረ ወሰኖችን ያሻሻለና የኦሊምፒክ ሜዳሊያዎች ባለቤት ነው።

ኃይሌ ከውድድር ስፖርት ከራቀ በኋላ በተለያዩ የምርትና የአገልግሎት ዘርፎች የተሰማራ ስኬታማ ሥራ ፈጣሪና የንግድ ሰው ለመሆን ችሏል።

በተመሳሳይም ሪዮ ኦሊምፒክ በማራቶን ውድድር ሁለተኛ በወጣበት ጊዜ በወቅቱ በነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት ላይ የተቃውሞ ምልክት ካሳየ በኋላ በስደት የቆው አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ በቅድሚያ በፌስቡክ ገጹ ቀጥሎም ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ በመቅረብ ወደ ጦር ሜዳ እሄዳለሁ ሲል ተናግሯል።

"እንደ ትልቅ እድል ነው የምቆጥረው። ከዚህ በፊት ሲጨፈጭፈን የነበረውን ህወሓትን ፊት ለፊት ተገናኝተ ለመዋጋት መቻል እንደ እድል ነው የምቆጥረው። ሰው ሁለት እናት አለው። አገር እና ወላጅ እናት። አገር ሲደፈር ቆሜ የማይመበት ምክንያት የለም" ሲል ሌሊሳ ለኢቢሲ ተናግሯል።

የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችም በተመሳሳይ የጠቅላይ ሚንስትሩን ውሳኔ ተከትሎ ወደ ጦር ግንባር እንደሚዘምቱ እየገለጹ ነው።

ከእነዚህም መካከል የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አመራር እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ክርስቲያን ታደለ እንዲሁም የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ የሴቶች ጉዳይ ዋና ተጠሪ ገነት አራጌ ወደ ጦር ሜዳ ለመዝመት ከወሰኑት ፖለቲከኞች መካከል ይገኙበታል።

"ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጦር ሜዳ ወርጄ ጦሩን እመራለሁ ሲል ቤቱ የሚቀመጥ ጤናማ ኢትዮጵያዊ ይኖራል ብዬ አላስብም። በእርግጥ እኛ በሥራ አስፈጻሚ ደረጃ ሁሉም የስራ አስፈጻሚ አባላት ለሃገር አንድነት እና ለህዝብ ደህንነት መዝመት አለበት የሚል ውሳኔ አሳልፈን ነበር" ሲሉ ክርስቲያን ታደለ ለኢቢሲ ተናግረዋል።

ከአርቲስቶችም ደመረ ለገሰ እና ቴዎድሮስ ታደሰ ወደ ጦር ሜዳ በመሄድ ለመሰፍ ስለመወሰናቸው በተመሳሳይ ተዘግቧል።

ብልጽግና ፓርቲ በፌስቡክ ገጹ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ፈለግ በመከተል ወደ ጦር ሜዳ ለመሄድ ወስነዋል ያላቸውን ተጨማሪ ሰዎች ይፋ አድርጓል። ከእነዚህም መካከል የፓርቲው ከፍተኛ አመራር የሆኑት አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ይጠቀሳሉ።

በብልጽግና ፓርቲ ይፋዊ የፌስቡክ ገጽ ላይ በተጋራው መልክት አለሙ ስሜ (ዶ/ር) መሪዎቹ ወደ ጦር ሜዳ መዝመታቸውን ተናግረዋል።

"የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት አመራሩ በግንባር ተገኝቶ መከላከያ ሠራዊቱንና የፀጥታ አካላትን የመደገፍ ቁርጠኝነቱን በተግባር እያሳየ ነው" ብለዋል።