ፌልትማን የጠቅላይ ሚንስትሩ አላማ የትግራይ አማጺያንን ከአማራ እና አፋር ማስወጣት ነው አሉ

የፎቶው ባለመብት, AFP/Getty Images
የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ጄፈሪ ፌልትማን የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አላማ የህወሓት አማጺያንን ከአማራ እና ከአፋር ክልሎች ማስወጣት ነው አሉ።
አምባሳደር ፌልትማን ይህን ያሉት የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ትናንት ምሽት በኢትዮጵያ ጉዳይ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው።
አምባሳደሩ በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላትን ልዩነቶቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ የሚያስችል ተስፋ የሚሰጥ ጀምር አለ ብለዋል።
ይሁን እንጂ አምባሳደሩ ሁለቱን አካላት በዲፕሎማሲያዊ ጥረት ወደ ውይይት እንዲገቡ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት በፍጥነት በሚቀያየሩ ሁኔታዎች ይደናቀፋል የሚል ስጋት እንዳላቸው ተናግረዋል።
"ግልጽ መሆን እፈልጋለሁ። ግጭት ቆሞ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ የሚያስችል ውይይት አለ" ካሉ በኋላ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ እሁድ ዕለት (ህዳር 12) ዋና አላማቸው የህወሓት አማጺያን ተቆጣጠረው ከሚገኙባቸው የአማራ እና አፋር ክልሎች ማስወጣት መሆኑን ነግረውኛል ሲሉ አምባሳደር ፌልትማን ተናግረዋል።
"ይህን ዓላማ እንጋራለን" ያሉ ፌልትማን፤ "በሌላ በኩል ያነጋገርናቸው የትግራይ መከላከያ ኃይል እና የህወሓት መሪዎች የኢትዮጵያ መንግሥት ከሐምሌ (2013) ጀምሮ ይፋዊ ባልሆነ መንገድ ትግራይ ላይ የጣለውን የሰብዓዊ እርዳታ እቀባን ማስነሳት ዓላማችን ነው ብለዋል። ይህንም እንጋራለን" ብለዋል አምባሳደሩ።
አምባሳደር ፌልትማን እንደሚሉት የፌደራሉ መንግሥት እና የህወሓት ኃይሎች ለአፍሪካ ሕብረት ልዩ መልዕክተኛ ኦሌሴጉን ኦባሳንጆ እና ለሌሎች ዲፕሎማት እና መሪዎች ተመሳሳይ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ፌልትማን ትናንት በሰጡት ማብራሪያቸው መሠረታዊው ጉዳይ ሁለቱም ዓላማዎች ሊሳኩ ይችላሉ ይላሉ። "ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ካላ፤ ሁለቱንም ማሳካት ይቻላል። አለመታደል ሆኖ ግን፤ ሁለቱም አካላት አላማቸውን በወታደራዊ ኃይል ለማስፈጸም እየጣሩ ነው። ሁለቱም እያሸነፉ እንደሆነ ነው የሚያምኑት" ብለዋል።
አምባሳደሩ አንድ ዓመት ያስቆጠረው ጦርነት ከፍተኛ ሰብዓዊ እና የንብረት ውድመት ማስከተሉን በማስታወስ፤ ለዚህ ጦርነት ወታደራዊ አማራጭ መፍትሄ እንደማይሆን ተናግረዋል።
ፌልትማን መንግሥት የሰብዓዊ አቅርቦት ሥራዎች ላይ እንቀፋት መሆን እና የመልሶ ማጥቃት ወታደራዊ እምጃዎችን መግታት አለበት፤ እንዲሁም የትግራይ ኃይሎች ወደ አዲስ አበባ የሚያደርጉትን ጉዞ ማቆም አለባቸው ብለዋል።
"ለግጭቱ መፍትሄ ለመስጠት የመጀመሪያም የመጨረሻም እንዲሁም ብቸኛው አላማችን ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ መስጠት ነው። የትኛውንም ቡድን አንደግፍም። ለአንዱ ወገንተኛ ናቸው የሚለው አሉባልታ ሐሰት ነው።"
የኢትዮጵያ ጎረቤት አገራት፣ የአፍሪካ ሕብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ዓለም አቀፉ ማኅብረሰብ ልዩነቶቹን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት የሚባክን ጊዜ የለም በሚለው ይስማማሉ ብለዋል ፌልትማን።
አምባሳደር ፌልትማን ከጠቅላይ ሚንሰትር ዐቢይ ጋር በነበራቸው ውይይት ከወታደራዊ አማራጭ ይልቅ በድርድር አላማቸውን ሊያሳኩ እንደሚችሉ ማስረዳታቸውን ተናግረዋል።
"የትግራይ መከላከያ ኃይልን ወደ ሰሜን ገፍቶ ወደ ትግራይ መመለስ እንደሚቻል ተማምነዋል። በዚህ መተማመን ላይ ግን ጥያቄ አለኝ። ሰኔ መጨረሻ ላይ የአገር መከላከያ ሠራዊት ትግራይን ለቅቆ ከወጣ በኋላ ስላለው ሁኔታ ካርታ ስመለከት በዚህ ዙሪያ ጥርጣሬ ያሳድርብኛል" ብለዋል።
አምባሳደር ፌልትማን የትግራይ ኃይሎችን በወታደራዊ አማራጭ ወደ ትግራይ ለመመስ ለሚደረገው ጥረት መስዕዋትነቱ ከፍተኛ መሆኑን ማስረዳታቸውንና ዲፕሎማሲያዊው ሂደት ምን ሊመስል እንደሚችል ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር በዝርዝር ማወራታቸው አበረታች መሆኑን ጠቅሰዋል ፌልትማን።
ፌልትማን በአፍሪካ ቀንድ ቆይታቸው ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት በተጨማሪ የህወሓት አመራሮችን ኬንያ ውስጥ አግኝተው ማነጋገራቸውን ገልጸዋል።
አምባሳደሩ ከተለያዩ የህወሓት አመራሮች ጋር በነበሯቸው ወይይቶች፤ አዲስ አበባ መግባት ለህወሓት እና ለአገሪቱ በጠቅላላው አደጋ መሆኑን በመረዳት ወደ አዲስ አበባ መግባት ፍላጎት እንደሌላቸው እንደነገሯቸው አመልክተዋል።
ይሁን እንጂ መንግሥት ትግራይ ላይ ጥሏል የሚሉት የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እግድ እንዲነሳ ፍላጎት እንዳላቸው ፌልትማን አስታውሰዋል።















