አሜሪካ በአፍሪካ ከምታራምደው አዲስ ፖሊሲ የተማርናቸው ጉዳዮች

አንቶኒ ብሊንከን በኬንያ ጉብኝታቸው ወቅት

የፎቶው ባለመብት, AFP

በቅርቡ የመጀመሪያ የአፍሪካ ጉብኝታቸውን ያደረጉት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከንን ለሰማ አሜሪካ አፍሪካን የምትመለከትበትና ስለ አህጉሪቱም የምትናገርበት መንገድ ትልቅ ለውጥ አለ።

በተለይም አህጉሪቷን በማንቋሸሽ ከሚታወቁት ዶናልድ ትራምፕም ለየት ባለ መልኩ አስተደዳራቸው አህጉሪቷን እንደሚያዩት አስረድተዋል።

ከዚህ ቀደም አፍሪካ ምን ማድረግ እንዳለባት የበላይነቷን በሚያንፀባርቅ መልኩ ማስተማር የሚቃጣት አሜሪካ በአሁኑ ወቅት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል የንግድ ሸርክናና አጋርነት ላይ አተኩራለች።

የአሜሪካው ዋና ዲፕሎማት "አፍሪካ የወደፊቷ መዳረሻ ናት" ማለታቸው አህጉሪቱ ከዚህ በኋላ ችላ ልትባል እንደማትችል ማሳያ ነው።

አፍሪካ የዓለማችን ወጣቶች የሚኖሩባት አህጉር ናት በአውሮፓውያኑ 2050 ግምቶች ከዓለም ከአራት ሰዎች አንዱ አፍሪካዊ ይሆናል።

ይህ የህዝብ መጠን ለሚመጡት አሥርት ዓመታት ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን ይቀርጻል ነገር ግን ብዙ ፈተናዎች ተጋርጠዋል።

የባይደንን አስተደዳር የአፍሪካ ፖሊሲ የተናገሩት ብሊንከን አገራቸው በአምስት ቁልፍ ጉዳዮች ላይ እንደምታተኩር ተናግረዋል እነዚህም ንግድን ማሳለጥ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን መቋቋም፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ዲሞክራሲ፣ እና ሰላምን እና ደህንነት ናቸው።

1 ንግድ

አሜሪካ አፍሪካ ውስጥ ካሉ 54 አገሮች ጋር ያላት የንግድ ልውውጥ ከጠቅላላው ወጪ ንግዷ 2 በመቶ ያነሰ ነው።

ይህም በዋነኝነት ናይጄሪያን ጀምሮ በነዳጅ የወጪ ንግድ ላይ ያተኮረ ነው። በዚህ ወቅትም ብሊንከን የአሜሪካ አስተዳደር ለአህጉሪቱ ያለውን ፖሊሲ አስታውቀዋል።

በቀድሞው የአሜሪካ አስተዳደር የተጀመረውን "የሁለትዮሽ ንግድ እና ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ ያለመው" የብልጽግና አፍሪካ ፕሮግራምን (ፕሮስፐር አፍሪካ ፕሮግራምን) ጠቅሰዋል።

በክሊንተን ዘመንም ይህንን ለማሳካት ከቀረጥ ነፃ ንግድ ተጠቃሚነት እድል 'አጎዋ' ፕሮግራም ተጀመረ።

አጎዋ ለብዙ ታዳጊ አገሮች የአሜሪካ ገበያን ክፍት የማድረግን ቅድሚያ ይሰጣል።

ያደገ ምጣኔ ኃብት ያላቸው አገራት አትራፊ በሆኑባት አሜሪካ ዕድል ያላገኙ አገሮች ኢኮኖሚን ለማሳደግ ታስቦ ነበር። ነገር ግን በአብዛኛው የወጠነውን ዕቅድ ማሳካት እንዳልቻለም ይነገራል።

የጨርቃጨርቅ ምርት በኬንያ

የፎቶው ባለመብት, AFP

በጨርቃጨርቁ ዘርፍ ረገድ እንደ ኢትዮጵያና ኬንያ ባሉ የአፍሪካ አገሮች በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የአገሬዎቹ ተወላጆች በልብስ ሰፊነት ተቀጥረው የሚሰሩባቸው ኢንዱስትሪዎች ቢከፈቱም አብዛኛው ጨርቃ ጨርቅ የሚመጣው ከቻይና በርካሽ ተመርቶ ነው።

ስለዚህ በጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪው ወይም በግብርናው ዘርፍ ጥሬ ዕቃዎች በሚመረቱበት ሁኔታ ትንሽ ወይም ምንም ተፅእኖ ማምጣት አልቻለም።

የአፍሪካ ገበያ ትልቅ ቢሆንም ከአገር ወደ አገር ወጥ የሆነ ሰንሰለት ወይም ቅርፅ የለውም፤ እንዲሁም ከፍተኛ የመሠረተ ልማት፣ የሎጂስቲክስና የታሪፍ ችግሮች ያሉበት ነው።

እነዚህን መሰናክሎች ለመፍታት በሚል በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ተቋቁሟል።

ብሊንከን አገራቸው ከአህጉሪቷ ጋር ያለውን የንግድ ሸሪክነት በደስታ እንደምትቀበል እና የአፍሪካ ሀገራትም ከስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየሰራች ነው ብለዋል።

"በአለም ላይ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኃያል እድገትን ማየት እንፈልጋለን" ብለዋል።

በተጨማሪም አሜሪካ 'ቢዩልድ ባክ ቤተር' በተባለ ንቅናቄ "የዓለም አቀፉን የመሰረተ ልማት ክፍተት ለማጥበብ" አላማ እንዳላት አስታውቀዋል።

ቻይና ቀድሞውንም በአፍሪካ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ዋና ተዋናይ ስትሆን የትራምፕ አስተዳደር በበኩሉ የአፍሪካ ፖሊሲያቸው ቻይና የምታደርሰውን ተፅእኖ በመቃወም ላይ ያተኮረ ነበር።

ብሊንከን በበኩላቸው ከትራምፕ አስተዳደር ለየት ያለ እይታ ነው ያላቸው

"የእኛ አፍሪካ ፖሊሲ አፍሪካን ያማከለ ነው፤ ስለ ቻይና አይደለም" ብለዋል ብሊንከን ለቢቢሲ

ነገር ግን በንግግራቸው ቻይናን ሸንቆጥ ባደረገ መልኩ ተናግረዋል "ብዙውን ጊዜ አለም አቀፍ የመሠረተ ልማት ስምምነቶች ግልጽ ያልሆኑ፣ አስገዳጅነት ያላቸው፣ የማይቋቋሙት ዕዳ በአገሮች ላይ የሚጭኑ፣ አካባቢን አውዳሚ ናቸው፣ እናም ሁልጊዜም በነዚህ አገራት የሚኖሩትን ሰዎች ይጠቅማሉ ማለት አይደለም " በማለትም አገራቸው ከዚህ በተለየ ስምምነቶችን እንደምትፈፅም አስረድተዋል።

2 ኮቪድ-19

በብሊንከን የተገለጸውና በሁለተኛ ደረጃ ቅድሚያ የተሰጠው የኮቪድ-19 ወረርሽኝን መዋጋት ነበር።

ዘ ግሎባል ኮቪድ ኮርፕስ በተባለ አዲስ የህዝብ- የግል ጅማሮ "የአሜሪካን የንግድ ድርጅቶች 'የመጨረሻ ማይል' ተብሎ በሚጠራው የሎጂስቲክስ እርዳታ ከሚያስፈልጋቸው አገሮች ጋር ያገናኛል" ብለዋል።

በአፍሪካ የመጀመሪያ ጉብኝት ያደረጉባት ኬንያ በአህጉሪቷ ይህንን ጅማሮ የተቀላቀለች የመጀመሪያ አገር ሆናለች።

የሱዳን ባለስልጣናት ክትባት ሲቀበሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጅማሮው ግን የአህጉሪቱን የጤና አራማጆች ከሚጠብቁት እጅግ ያነሰ ነው።

በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ህዝቦቻቸው የሚያስፈልጋቸውን የክትባት መጠኖችን በጅምላ ማምረት እንዲችሉ የአምራቾች የአእምሯዊ ንብረት መብቶች እንዲነሱ ሲጠይቁ ቆይተዋል።

እስካሁን ድረስ፣ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት የመጨረስና የመሙላት መብቶችን ያረጋገጡ ሲሆን ይህም በመሠረቱ የመጨረሻ ሂደቶችን እና ክትባቶችን ማሸግ ያካትታል።

አፍሪካ ከየትኛውም አህጉር ዝቅተኛው የክትባት መጠን ያላት ሲሆን ባለፈው ወር መጨረሻ ሙሉ ለሙሉ የተከተቡት አፍሪካውያን 6 በመቶ ብቻ መሆናቸውን የአለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

በንፅፅር፣ የአሜሪካ ሲዲሲ ከ58 በመቶ በላይ የሚሆነው የአሜሪካ ህዝብ ሙሉ በሙሉ መክተቡን ሪፖርት አድርጓል።

3የአየር ንብረት ለውጥ

የአፍሪካ አህጉር ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ በጣም የተጋለጠች ስትሆን ለለውጡ ግን አነስተኛ አስተዋፅኦ ነው የምታደርገው ።

አሜሪካ በአለም አቀፍ የአየር ንብረት መላመድ ፕሮጀክቶች ላይ ኢንቨስት እያደረገች መሆኑን ያሳወቀች ሲሆን ለዚህም ከአውሮፓውያኑ 2024 ጀምሮ በየአመቱ 3 ቢሊዮን ዶላር ለመመደብ አቅዳለች።

ሰዎችን ከኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በማገናኘት ላይ ያተኮረው የኦባማ ዘመን 'ፓወር አፍሪካ' ለታዳሽ ሃይል ከፍተኛ አድሎአዊ ባለው መልኩ ቀጥሏል።

"በአህጉሪቱ ከ25 ሚሊየን በላይ ቤቶችን እና ንግዶችን ከኤሌክትሪክ ጋር አገናኝተናል፣ 80 በመቶ የሚሆነው በታዳሽ ሃይል ላይ የተመሰረተ ነው" ያሉት ብሊንከን፣ አሜሪካ በአፍሪካ ትልቁ የፀሐይ እርሻ ተብሎ የሚጠራውና በቦትስዋና እና በናሚቢያ መካከል ያለው ትብብር ልማት ላይ ተሳታፊ ናት ብለዋል።

በአህጉሪቱ እየጨመረ የሄደውን የፀሃይ ብርሃን እና የንፋስ ሃይልን የሚጠቀሙ እርሻዎችን ይጨምራል።

4 ዲሞክራሲ

በብሊንከን ጉብኝት ወቅት "ዓለም አቀፍ ዲሞክራሲያዊ ድቀት" ሌላው ዋነኛ የመወያያ ነጥብ ነው።

ከአሜሪካ ባለስልጣን ባልተለመደ መልክ ባሳዩት ግልፅነት በትራምፕ አስተዳደር የተነሳውን ሁከትና ብጥብጥ በማጣቀስ፣የዲሞክራሲ ተግዳሮቶችን በመጥቀስ አሜሪካ ራሷ ስላለችበት ተጋላጭነት ተናግረዋል።

በዛምቢያ የተካሄደው ምርጫ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ይህ ሁኔታ በታናናሽ ወንድም ወይም እህት ላይ የገሳጭነት ሚና በመጫወትና ጣት በመጠቆም እንደ አስፈሪ ታላቅ ወንድም ሚና ሲወስዱ ከነበሩት የቀድሞ የአሜሪካ ባለስልጣናት ትልቅ ለውጥ ነው።

አፍሪካ በዘንድሮ ው ዓመት ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ ብዙ መፈንቅለ መንግሥትን አስተናግዳለች ።

በማሊ፣ ጊኒ እና በቅርቡም ሱዳን ውስጥ ወታደራዊው ሃይል ስልጣኑን ተቆጣጥሯል። ነገር ግን የተቃዋሚ መሪ በሆኑበት ዛምቢያ እንዲሁም ኒጀር ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ሽግግሮች ተካሂደዋል።

ብሊንከን በአምባገነን መሪዎች ዘንድ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እየጨመረ መሄዱን ተቃውመዋል።

"ዲሞክራሲን ለማጠናከርና በማያፈርስበት ሁኔታ ቴክኖሎጅዎችን እንዴት ማስተዳደር እንዳለብን በምንወያይበት ወቅት መንግስታት፣ ኢንዱስትሪዎች እና የፈጠራ ባለሙያዎች የሚያደርጓቸው ምርጫዎች በሰዎች መብት እና ነፃነት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ።" ብለዋል።

5 ሰላምና ደህንነት

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአፍሪካ ጉብኝት በዋናነት ከአፍሪካ ቀንድ እስከ ሳህል ድረስ ባለው ሰላም እና ደህንነት ላይ ያተኮረ ነበር።

ይህ ከፖለቲካ መረጋጋት እና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተያያዘ እያደገ ያለ ፈተና መሆኑ አያጠራጥርም።

በኢትዮጵያ ያለው ጦርነት አገሪቷን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ቀንድ ስጋት ነው ሲሉም ተናግረዋል።።

ከአንድ ዓመት በላይ ባስቆጠረውና በትግራይ ክልል ተቀስቅሶ ወደ አጎራባቾቹ የአማራና የአፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት እንዲቋጭም አገራቸው ከኬንያ፣ ከአፍሪካ ሕብረት እንዲሁም የሕብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ እና ከሌሎች አጋሮች በቅርበት እየሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በተለይም ይህንን በተመለከተ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን ከከፍተኛው ተወካይ ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ ጋር በመሆን ተፋላሚ ወገኖች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ጦርነቱን በአስቸኳይ እንዲያቆሙ፣ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዲቆም፣ በሰሜን ኢትዮጵያ በረሃብ ላይ የሚገኙ ሚሊዮኖችን ህይወት የማዳን እርዳታ እንዲመቻችና ሰብዓዊ አገልግሎቶች እንዲደርሱ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ጦርነቱ እየሰፋ በሄደ ቁጥርም አደጋ ላይ የሚወድቀው የዜጎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ጠቅሰው ይህም ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በትግራይ እንዲሁም በቅርቡ በአማራ ክልል ያለው ሕዝብ ለስቃይ መዳረጉን ጠቅሰዋል።

አዲስ ይፋ የሆነው የአሜሪካ አፍሪካ ፖሊሲ ቀደም ባሉት አስተዳደሮች የቀጠለ ቢሆንም በእኩል አጋርነት ላይ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶታል።

"ብዙ ጊዜ የአፍሪካ ሃገራት እኩል ከመሆን ይልቅ እንደ መለስተኛ አጋሮች ወይም በከፋ ሁኔታ ነው የሚታዩት" ብለዋል።

ግን ያ እኩልነት እውን መሆን አለመሆኑ ወደፊት የሚታይ ነው።

ነገር ግን ምንም ለአፍሪካ ፍላጎት ከሌለውና በአህጉሪቱ ለሚገኙ ፕሮግራሞች የበጀት ቅነሳን በመተግበር አገሮችን በማዋረድ ከሚታወቀው ከትራምፕ አስተዳደር አንፃር የአቋም ለውጥ እንዳለ ጥርጥር የለውም።

ለዚህ አቋም ለውጥም በከፊል የባይደንና- ካማላ ሃሪስ አስተዳደር ዋጋ ሊሰጠው ይገባል ።

ነገር ግን፣ በላቀ ደረጃ፣ አፍሪካ ችላ ለማለት አስቸጋሪ እየሆነች ነው።

ሁሉም ትንበያዎች አፍሪካ በአለም ኢኮኖሚ፣ ደህንነት እና ፖለቲካ ውስጥ እያደገ እና ተደማጭነት ያላት ሚና የምትጫወት አህጉር እንደምትሆን ያመለክታሉ።