በፖሊስ የተገደለው ጥቁር አሜሪካዊ ቤተሰቦች 15 ሚሊዮን ዶላር ሊከፈላቸው ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካዋ ኮሎራዶ ክፍለ ግዛት ባለሥልጣናት ከፖሊስ ጋር በነበረ እሰጣገባ ምክንያት የተገደለው ጥቁር አሜሪካዊ ቤተሰቦች 15 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንደሚከፈላቸው አስታውቀዋል።
የ23 ዓመቱ ኢላይጃህ ሸነን ማክሌይን በፈረንጆቹ 2019 አውሮራ በምትባል ሥፍራ ነው ሕይወቱ ያለፈው።
ግለሰቡ ሕይወቱ ከማለፉ ከሶስት ቀናት በፊት ሶስት ፖሊሶች አስቁመውት አደገኛ ማደንዘዣ መደኃኒት ሰጥተውት ነበር።
የሟች ቤተሰቦች ባለፈው ዓመት ክስ መሥርተው ፖሊስ ለኢላይጃህ ሞት ኃላፊነቱን እንዲወስድ ሲጠይቁ ነበር።
የኮሎራዶ ክፍለ ግዛት በስህተት በተፈፀመ ሞት አማካይነት ይህን ያክል ገንዘብ ለከሳሽ ስትከፍል የመጀመሪያዋ ነው።
የኢላይጃህ እናት ሺና የሕግ አማካሪ በቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው እናቱ ሕዝቡ ባሳያቸው ድጋፍ ደስተኛ መሆናቸውንና የልጃቸው ሞት "ከባድ ለውጥ ለሚያስፈልገው" ፖሊስ እንደምክንያት እንደሚሆን ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።
በሟች ቤተሰብ በፖሊስ መካከል የተገባው ስምምነት ምን እንደሚያካትት እስካሁን ይፋ አልተደረገም።
የኢላይጃህ ጉዳይ ይበልጥ ትኩረት ያገኘው ምንም ዓይነት መሣሪያ ሳይታጠቅ ባለፈው ዓመት በፖሊስ የተገደለው ጆርጅ ፍሎይድ ክስተት አሜሪካን ካናወጠ በኋላ ነው።
ወጣቱ ኢላይጃህ ነሃሴ 24/2019 ዴንቨር ውስጥ በምትገኘው አውሮራ ካለ አንድ ጎዳና ላይ ብቻውን ሲራመድ ሶስት ፖሊሶች ያስቆሙታል።
አንድ ተጠርጣሪ እያፈላለጉ ያሉት ፖሊሶች በተሰጣቸው ጥቆማ መሠረት ኢላይጃህ "ተጠርጣሪውን መስሎን ነበር" ሲሉ ተናግረው ነበር።
ሶስቱ ፖሊሶች ኢላይጃህ ታጥቆ እንደሆን ለመፈተሽ ቢሞክሩ ወጣቱ ግን እንዳይነኩት በመፈለግ ይሸሻል።
ከፖሊስ ካሜራ ላይ የተገኘው ምስል እንደሚያሳየው ኦቲዝም ያለበት ኢላይጃህ "እኔ ከቤት ብዙ አልወጣም፤ እባካችሁ ብዙ አትቅረቡኝ" እያለ ነበር።
ነገር ግን የፖሊስ መኮንኖቹ በግድ ይዘውት ከመሬት ያጣብቁታል።
የኢላይጃህ ቤተሰብ ፖሊስ አላስፈላጊና ከመጠን በላይ የሆነ ኃይል ተጠቅሟል፤ ይህ ሲሆን ልጃችን እያስመለሰ ነው፤ መተንፈስ አቃተኝ እያለ ነበር ሲሉ ከሰዋል።
ፖሊሶቸ ተጨማሪ እርዳታ ከጠሩ በኋላ 500 ግራም ኬታሚን የተባለ አደንዛዥ መድኃኒት እንደወጉት ተነግሯል።
ከሶስት ቀናት በኋላ የኢላይጃን አእምሮ ሙሉ በመሉ መሥራት አቆመ።
ከሁለት ዓመታት በኋላ ሶስቱ ፖሊሶችና መድኃኒቱን የወጉት ሁለት የሕክምና ሰዎች በ23 መዝገቦች ተከሰዋል።
የጆርጅ ፍሎይድ ቤተሰቦች ተመሳሳይ ክስ ፖሊስ ላይ መሥርተው 27 ሚሊዮን ዶላር እንደተከፈላቸው ይታወሳል።












