የፅንስ መጨንገፍ - በርካታ ሴቶች የማይናገሩት ጥልቅ ህመም

የቢቢሲዋ ጋዜጠኛ ቱሊፕ ማዙምዳር በርካታ ዘገባዎቿ በእናቶች ጤና እና ሴቶችን በዓለም ዙሪያ በሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች ላይ የሚያተኩሩ ናቸው።
በዚህ ዘገባዋ ደግሞ የራሷን የእርግዝና ታሪክና የፅንስ መጨንገፍ ያሳደረባትን ጥልቅ ህመምና ተደራራቢ ሃዘን ታሪክ ጽፋለች።

አንዳንድ ሁኔታዎች በራሳችን ላይ ይፈጠራሉ ብለን በጭራሽ አናስብም። ነገር ግን ህይወት በጠበቅናት መልኩ አትሄድም ራሳችንን በማይሆኑ ክስተቶች ውስጥ እናገኛለን።
ራሴን መመርመሪያ ክፍል 9 ውስጥ ባለው አልጋ ላይ ቁጭ ብዬ ነጭ በሆነው የሆስፒታል አንሶላ ላይ ደማቅ ሰማያዊ ካልሲዬን እያየሁ ባለሙያዎቹ የሚሉኝን ነገር እጠባበቃለሁ።
ግን በአንፃሩ ፀጥታ ሰፈነ። ይልቅስ ሌላ ባለሙያ ጠሩ። ባለሙያዋ ከመናገሯ በፊት ባለችው ጥቂት ሴኮንዶች ዓለሜ ሁሉ ልትገለባበጥ እንደሆነ ተገነዘብኩ።
"በጣም አዝናለሁ" ነበር የተባልኩት።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ አራት የፅንስ መጨንገፍ አጋጥሞኛል። ሁለቱ በመጀመሪያዎቹ የእርግዝና ወቅት ሲሆን ሁለቱ ደግሞ እርግዝናዎቹ ከገፉ በኋላ የተከሰቱ ናቸው።
በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ውስጥ ከአራት እርግዝናዎች መካከል ቢያንስ አንዱ ፅንስ ይጨነግፋል። ወደ 50 በመቶ የሚሆነው የፅንስ መጨንገፍ ባልተለመደ የክሮሞዞም የሚከሰቱ ሲሆን ይህም ማለት በጭራሽ ህፃኑ ሊተርፍ የማይችልበት እርግዝና ነው።
ከዚያ በኋላ ግን በዚህ መልኩ ፅንሳቸው የጨነገፋባቸው አብዛኛዎቹ ሴቶች ጤናማ እርግዝና ይኖራቸዋል።
እንደ እኔ ግን ከ100 ሴቶች አንዷ ተደጋጋሚ የፅንስ መጨንገፍ ያጋጥማታል። ይህም በዩኬ ውስጥ በተከታታይ ሦስት የፅንስ መጨንገፍ ተብሎ ይገለጻል። ተደጋጋሚ የፅንስ መጨንገፍ ባጋጠመን ቁጥር ቀጣዩ የተሳካ እርግዝና የመሆን እድሉም እየተመናመነ ይሄዳል።
ነገር ግን ለበርካታ ባለትዳሮች ፅንስ በምን ምክንያት እንደሚጨነግፍ አይታወቅም። ለዚህም ጥናት ባለመሰራቱ እንዲሁም የገንዘብ ድጋፍ ባለማግኘቱ ነው። የሴቶች ጤና ጉዳዮች ብዙ ትኩረት የማይሰጣቸውና ጥናቶች ያልተደረገባቸው ናቸው።
የእኔ ፅንስ መጨንገፍ ወደ ከፋ ደረጃ ተባብሷል። የመጨረሻው ፅንሴ የተጨናገፈው በግሪክ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ የእናቶችን ጤንነት በተመለከተ ለሥራ በተመደብኩበት ወቅት ነው።
ቀስ ብዬም ወደ ካምፑ ተንቀሳቃሽና ቆሻሻ ሽንት ቤት መሄድ ነበረብኝ። በወቅቱም ሥራዬን በማጠናቀቅ ላይ ማተኮር ነበረብኝ።
በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች በካምፑ በታጨቁበት ሁኔታ ፅንሴ የተጨናገፈብኝ እኔ ብቻ እንዳልሆንኩ እረዳለሁ። ነገር ግን በስደተኞች ካምፕ ካሉት ሴቶች በተለየ ወደ አገሬ ወደ ቤቴ ስመለስ በአግባቡ እንክብካቤ እንደሚደረግልኝ አውቃለሁ።
ከዚያም ሪቫህ ነበር፤ ትንሹ ጨቅላዬ!
ያለ ልብ ምት ተወለደ። አንዳንድ ሰዎች በመተኛት የተወለደ ብለው መግለፅን ይመርጣሉ።
ሪቫህ ከአስጨናቂና አስደሳች ምጥ በኋላ ነው የተወለደው። ምጡና አወላለዱ ላይ መደሰቴን መቀበል እንግዳ ነገር ሆኖ ተሰማኝ።
ነገር ግን ከባለቤቴ ጋር አብረን ማድረግ የቻልነው በምጥ ወቅት እጄን ይዞ አይዞሽ ማለት ብቻ ነበር፤ ልጃችንን ማቀፍ ሳንችል ቀረን።
ከዚያም ልጄን ካጣሁ በኋላ የነበሩት ጥቂት ሳምንታት በብዥታ የተሞሉ ነበሩ። ከዚያ በኋላ የነበሩትም ትዝታዎች የተቀነጫጨቡ ናቸው።
የጨቅላው ልጄ አስከሬን ይመረመር ይሆን? በመቃብር ስፍራ ተገኝቶ ትንንሸ የአስከሬን ሳጥኖች መመልከትና መምረጥ፣ እንዲሁም ለመጀመሪያ ጊዜም ቆንጆውን የወንድሜን ልጅ ያገኘሁት። በርካታ ነገሮች የተመሰቃቀሉብኝ ወቅት ነበር።
ይህንን ማንበብ ምን ያህል አስጨናቂ እንዲሁም አስፈሪ ሊሆን እንደሚችል ይገባኛል።
ነገር ግን በርካታ ሴቶች እና ቤተሰቦች ተመሳሳይ ገጠመኞች ይኖራቸዋል፣ ሆኖም በጣም ጥቂቶች ናቸው ልምዳቸውን በግልፅ መናገር እንደሚችሉ የሚሰማቸው።

በርካቶች ታሪኬን ስነግራቸውና ፊታቸው ላይ ሐዘናቸውንና ስሜታቸው ሲቀያየር ስመለከት ጭራሽ መጥፎ ስሜት እንዲሰማቸው ስላደረገው ታሪኬ ይቅርታ እጠይቃለሁ።
እንደ እኔ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶች ልጃቸው ለምን እንደሞተ መልስ አያገኙም። እኔ ግን እዚህ ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ባገኘሁት ጥሩ እንክብካቤ እራሴን እንደ "ዕድለኛ" አድርጌ እቆጥራለሁ።
ስለ እናቶች ጤና ከብዙ የዓለም ክፍሎች ሪፖርት አድርጌያለሁ፣ እናም ምን ያህል ሴቶች፣ በተለይ በአንዳንድ ታዳጊ አገራት፣ ልጆቻቸውን ከማጣታቸው በፊት፣ በወቅቱም ሆነ ከዚያ በኋላ ወደ ህክምና ማዕከላት እንደማይሄዱ ተገንዝቤያለሁ።
ትዝ ይለኛል የ17 ዓመቷን ሱላይናን ያገኘኋት በማዕከላዊ ኡጋንዳ ነው። ከምትኖርበት የሁለት ሰዓት ርቀት ላይ ወዳለው ሆስፒታል ከመድረሷ በፊት ለሁለት ቀናት ያህል በትንሽ ጎጆዋ ወለል ላይ ምጥ ላይ ነበረች። ሴት ልጇም ስትወለድ በህይወት አልነበረችም።
ሱላይና ልጇን ማቀፍ አለመቻሏን ነገረችኝ፣ እናም ይባስ ብሎ ወደ ቤቷ ስትመለስ በማኅበረሰቡ ተገለለች።
እርግዝናው ገፋ ብሎ የሚያጋጥም ፅንስ መጨንገፍ ብዙ ያልተለመደ ነው፣ ከ100 እርግዝናዎች 1 ያህሉ ላይ ይከሰታል።
አንድ ፅንስ በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ከ24 ሳምንታት በኋላ ወይም በአሜሪካ ከ20 ሳምንታት በኋላ ከጨነገፈ ሞቶ እንደተወለደ ነው የሚገለጸው፤ ህጻኑም በሟች መዝገብ ውስጥ በይፋ ይሰፍራል።
ከዚያ በፊት አንድ ሕፃን ከተወለደ የፅንስ መጨንገፍ ይባላል እና በይፋ ዕውቅና አይሰጥም። እንግሊዝን ጨምሮ በብዙ አገሮች በይፋ እንኳን አይቆጠርም ።
እናም "ዕድለኛ አይደለሽም" ተባልኩኝ። ሁሉም ምርመራዎቼ ምንም ችግር እንደሌለብኝና እና በቀላሉ እንደገና እንድንሞክር ተመከርኩ።
ስለዚህ እኛም ሞከርን እናም በዚያው ዓመት እንደገና አረገዝኩ። በጣም ፈራሁ፣ ተጨንቄአለሁ፣ እንዲሁም ሐዘን አድክሞኛል።ነገር ግን ዕድሜዬ ወደ 40ዎቹ እየተቃረበ በመሆኑ መጠበቅ ጥሩ አማራጭ ሆኖ አልታየኝም።ኢትዮጵያውያን 'የሌሉበት' ስለ ኢትዮጵያ የሚዘክረው ሬድ ሲ ዳይቪንግ ሪዞርት ፊልም
እንዳላደርግ በጥብቅ የተመከርኩትን ማድረግ ጀመርኩ። የልጄን የልብ ምት ቤት ሆኜ አዘውትሬ አዳምጣለሁ። የልብ ምቱን መስማት ጥሩ ስሜት ውስጥ ከተተኝ።
በአካባቢዬ ባለው ሆስፒታል አስደናቂ የሆነች ሳራ የተባለች አዋላጅ አገኘሁ። በርካታ ምርመራዎችን እያደረገችልኝም ፅንሱ ጥሩ እንደሆነ ታረጋግጥልኝ ጀመረ። ወደ ሥራ ተመለስኩና ቀናትን፣ ሳምንታትንና ወራትን ለማሳለፍ ሞከርኩ።
ከዚያም ወደ መመርመሪያ ክፍል 9 እንደገና ተመለስኩ። ከአራት ቀናት በፊት ምርመራ አድርጌ የልጄ የልብ ምት ጠንካራ ነበር። ምንም ችግር አልነበረም። ቀዝቃዛውን ቅባት ሆዴ ላይ ሲቀቡ እንባዬ ቢወርድም ስሜቴ ሁሉም ነገር ደህና ይሆናል የሚል ነበር።
ሪቫህን ካጣሁ በኋላ ይህ ምላሽ ለሁሉም ምርመራዎቼ ተመሳሳይ ነበር ።
መሳሪያውን በሆዴ ላይ ስታንቀሳቅስ መመርመሪያው ክፍል በዝምታ ተዋጠ።
ከዚያም ምላሿ "በጣም አዝናለሁ" የሚል ነበር።
'ራዬ' ብዬ የሰየምኩት ልጄ ከአራት ቀናት በኋላ ተወለደ። ውልደቱ በጣም አሰቃቂ ነበር። በጣም ብዙ ደም ስለፈሰሰኝ ቀዶ ህክምና ማድረግ ነበረብኝ።
ልክ ከሪቫህ ጋር እንዳደረግኩት ከራዬም ጋር አደርኩ። በትንሽ ቢጫ ጋዋን ጠቅልለው ማቀዝቀዣ በሆነች ሳጥን ውስጥ አድርገው አጠገቤ አስተኙት።
ለሪቫህ ማስታወሻ ብለን ከተከልነው ዛፍ ቅርንጫፎችን ቆርጠን አመጣን እንዲሁም ሪቫህ በሞተበት ወቅት የተጎዘጎዘው የፅጌረዳ አበቦችንም እንዲሁ አምጥተን ነበር።
ሪቫህን ማጣቴ ልምድ ስለሰጠኝ የነበረችን አጭር ጊዜም እንዴት ማሳለፍ እንዳለብኝና በተለየ መልኩም አክብሬ መሰናበት እንዳለብኝ አውቄ ነበር። ሻማዎች አመጣሁ፣ ላነብለት የምችለውን መፅሐፍ፣ እንዲሁም ያስገቡበትን ትንሽዬ ነጭ ሳጥን አሸበረቅኳት። የተሰጠንንም ትንሿን አሻንጉሊትም ጨቅላው ልጄ አስከሬን አጠገብ አስገባሁት።

ይህ ሁሉ ምን ያህል እንደሚያሳዝን አውቃለሁ፤ እውነት ነው ያሳዝናል። ለእኔ ደግሞ ፍቅሬን ሐዘኔን ማሳያና አስፈላጊ ነበር።
ብዙ ሴቶች እና አጋሮቻቸው ይህን ማድረግ እንደማይችሉ ወይም እንደማይፈልጉ አውቃለሁ። ባለቤቴም ይህንን ላለማድረግ መረጠ።
ነገር ግን ልጅ ሞቶ መወለድ ውስጥ ካለው አስደንጋጭና አስፈሪ ሁኔታዎችን የተወሰነውን በመቀነስ በፍቅር ለመተካት መሞከሬን ለማሳየትም ነው እዚህ የምጠቅሰው።
እናት ለተሸከመችው ሕፃን ያላት ፍቅር።
ፅንሳችሁ ጨንግፎ ከሆነ፤ እርግዝናችሁን አጥታችሁ ከሆነ በጣም አዝናለሁ።
ፅንሳቸው የጨነገፈባቸው ሴቶችን የምታውቁ ከሆነ ጠይቋቸው፣ ህመማቸውን ተጋሯቸው።
ምን ማለት እንዳለብን ማወቅ በጣም ከባድ ነው። ሁሉም እናቶች የተለያዩ እንደ መሆናቸው መጠን በተለያየ መንገድም ነው ሐዘናቸውን የሚገልፁት።
የሪቫህ ሞቶ መወለድ ባጋጠመኝ ወቅት ለወራት ማድረግ የፈለግኩት ነገር ቢኖር ስለ እሱ እያንዳንዱን ዝርዝር ነገር መንገር ብቻ ነበር። በራዬ ወቅት ያጋጠመኝ ተቃራኒው ነው። በዝምታ ተዋጥኩኝ።
ለእኔ ግን በአሁኑ ወቅት ከፈለግኩኝ ወይም አስፈላጊ ሆኖ ካገኘሁት ስለጨነገፉት ፅንሶቼም ሆነ ስላጣኋቸው ልጆች አወራለሁ። ይህ ጨለማና አሳዛኝ ምስጢር መሆን አያስፈልገውም፣ በዝግታ፣ በለሆሳስ ቃና ብቻ መወያየት የምንችለው ጉዳይ ሊሆን አይገባም።
ለጠፉትም ውድ ህይወቶች እውቅና መስጠት ነው።

















