አንዳንድ ሴቶች ከወሊድ በኋላ ባሕሪ ይቀይሩ ይሆን?

ልጇን ያቀፈች እናት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ማሕደር አካሉ ትባላለች። ከሁለት ዓመት በፊት መንታ ልጆችን በቀዶ ጥገና ነው የተገላገለችው። ነፍሰጡር እያለች ክብደቷ በጣም ስለጨመረ ከ30 ሳምንት በኋላ መተኛት አልቻለችም ነበር።

"ቁጭ ብዬ ነበር የማድረው" ትላለች። ስትወልድ ከዚህ ሁሉ ችግር እንደምትላቀቅ ብታስብም፣ እንደፍላጎቷ ግን አልሆነላትም ነበር።

መንታ ልጆቿን በየሁለት ሰዓት ልዩነት ማጥባት እና እንደልብ መንቀሳቀስ አለመቻል ችግር ሆነውባት ነበር።

በዚህ አላበቃም ማሕደር "እኔ በምክንያት እና በውጤት የማምን ነበርኩ፤ በትንሽ ነገር ስሜታዊ አልሆንም ነበር፣ ከወልድኩ በኋላ ግን ማልቀስ እና ሰዎች ለምን አይረዱኝም በማለት ማኩረፍ ጀመርኩ። በተለይም በእናቴ እና በባለቤቴ እናደድ ነበር" ትላለች።

ማህደር አንዲት ሴት ስትወልድ፣ አዲስ የሕይወት ምዕራፍ ስለምትጀምር የተለየ ልምድ ውስጥ ነው የምትገባው በማለት የነበረውን ሁኔታ ትገልፀዋለች።

ለዚህ ደግሞ ቤተሰብም ሆነ ሐኪሞች ቀድመው አያዘጋጁንም ስትል የራሰወን ልምድ በመጥቅ ታስረዳለች።

እንቅልፍ ማጣት፣ ስራ ሳይሰሩ ለረዥም ጊዜ መቆየት፣ ከራስ በላይ ለጨቅላዎቹ ትኩረት መስጠት፣ ውጥረቱን ያብሰዋል ትላለች። ማሕደር ያሳለፈችውን ከባድ ጊዜ ስትገልጽም፣ "ራሴን እጠላ ነበር። በሕይወቴ ተስፋ እቆርጥ ነበር፣ እንዲሁም ልጆቼ ሲያለቅሱ በጣም ስለምናደድ እናቴን 'ነይ ውሰጃቸው' ስል እጠራት ነበር።"

ይኹን እንጂ እንዲህ ባሕሪዋን የቀየረው ነገር ሴቶች ከወሊድ በኋላ ሊገጥማቸው የሚችል የአእምሮ ድባቴ እንደሆነ ያወቀችው ከሶስት ወር በኋላ ነው።

"ይህ ነገር ምንድን ነው ብዬ ጉግል ሳደርግ ፖስት ማርተም ዲፕረሺን የሚባል ሕመም እንደሆነ ተረዳሁ። እኔም የዚያ ተጠቂ መሆኔን አወቅሁ" ስትል ታብራራለች።

ይህ ጉዳይ የባህሪ መቀየር ጉዳይ እንዳልሆነ እና እንደ ማንኛውም ዓይነት በሽታ መሆኑን ስታውቅ መጀመሪያ የወሰደችው እርምጃ ራሷን መቀበል እና ከራሷ ጋር ለመታረቅ መሞከር ነበር።

ከዚያ በመቀጠል ደግሞ በአካበባቢዋ ለሚገኙ ሰዎች ማስረዳት ነበር።

እንደ ማህደር ገለጻ ይህ ቀላል አልነበረም። ምክንያቱም ትላለች "በከፍተኛ የስሜት መለዋወጥ ውስጥ ስለነበርኩኝ ችግሬን በአግባቡ ማስረዳት እንኳ አልቻልኩም ነበር።"

ኋላ ላይ ወደ መደበኛ ስራዋ ስትመለስ ከሰዎች ጋር መገናኛት ስትጀምር እና ችግሯን መግለጽ ስትጀምር እየቀለላት መጣ።

ከዚህ በኋላ ለትምህርት ከአገር ርቃ ሄደች።

"ለትምህርት ወደ ውጪ አገር እስከ ምሄድበት ለብቻዬ ጊዜ እስካገኝ ድረስ ተስፋ የመቁረጥ እና ስሜታዊ የመሆን ነገር ቢቀንስም አልጠፋም ነበር።"

ቤተሰቦቿ በአራስነት ጊዜዋ በጣም ተጎድታ ስለነበር ትልቁ ትኩረታቸው እርሷን በምግብ መጠገን ነበር።

"ስለዚህ ያመጣሁት የባህሪ ለውጥ ብዙም አልታያቸውም። ብዙ ጊዚያቸውን ልጆቹን በመንከባከብ ነበር የሚያሳልፉት።" ስትል ሁኔታውን ታስታውሳለች።

በተጨማሪ " ብቻዬን ሆኜ አለቅሳለሁ። ወይ ደግሞ አመመኝ የሚል ምክንያት እሰጣለሁ።" ያለምክንያት ስታለቅስ ማንም ሊረዳ ት እንደማይቸል የምትናገረው ማሕደር ከባድ ወቅት ማሳለፈን ለቢቢሲ አካፍላለች።

ከራስ አልፎ ለሌላ መትረፍ

ማሕደር ይህን ያሳለፈችውን ጊዜ የማህበራዊ ሚዲያ ላይ ካሉ ጓደኞቿ ጋር ቡድን በመፍጠር ማካፈል ጀመረች።

ያኔ ሰዎች ስልክሽን ስጪን። ስለዚህ ጉዳይ ልናዋራሽ እንፈልጋለን በማለት አጭር መልዕክት ይሉኩላት ጀመር።

ከእነዚህ ጓደኞቿ ጋር በማህበራዊ ሚዲያ በምታደርገው ውይይት ብዙዎቸ ወንዶች ይህንን ጉዳይ ከእነ አካቴው ሰምተውት እንደማያውቁት፣ ገሚሶቹ ሴቶችም እውቀቱ እንደሌላቸው፣ ሌሎቹ ደግሞ ጉዳዩ ቢገጥማቸው እንኳ የችግሩ ምንነት እንደማይረዱት ግንዛቤውን አገኘች።

"በአጭር መልዕክት ካዋሩኝ ሰዎች አንዷ 'ባለቤቴን ላየው አልፈልግም።' ሌላዋ ደግሞ 'ልጄን እጠላዋለሁ' ስትለኝ ከወለድሽ ስንት ጊዜሽ ነው ብዬ ጠየኳት። ከዚያም 'ሰላይ ነሽ እንዴ? ልጄን እጠላዋለሁ ስልሽ እብድ ነሽ እንዴ ያላልሽኝ ለምንድን ነው?' አለችኝ።

ልጇን ያቀፈች እናት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አንድ ሁለት ሶስት የሚሆኑ ሴቶች ደግሞ ራሳችንን ልናጠፋ ስንል ቤተሰብ ነው ያዳነን የሚል ነገር ነግረውኛል።" በማለት ያጋጠሟትን ታሪኮች ታካፍላለች።

ከዚያም ይህ ነገር ቀላል አለመሆኑን ተረዳሁ የምትለው ማሕደር፣ "እኔ ራሴ በዚህ ጉዳይ ውስጥ ስላለፍኩኝ ጉዳታቸው ይሰማኛል" ስትል የፈጠረባትን ስሜት ታስረዳለች።

የአእምሮ ጤና ጉዳይ ሌሎች ሰዎች ስለማይረዱት እና ችግሩ የደረሰባቸው ደግሞ ፍርድን ወይንም መፈረጅን ስለሚፈሩ አያወሩትም።

ስለዚህ እኔ እንደዚህ አይነት ሰዎችን ቀረብ ብዬ ልምዴን አካፍዬ አንድ ሰው እንኳ ብረዳ ብዬ ነው ታሪኬን ማካፈል የጀመርኩት ትላለች።

ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ ይህንን ጉዳይ አካፍላለሁ ስትልም ነግራናለች።

ይህ ጉዳይ የበረታባቸውን ሴቶች ደግሞ የስነ አእምሮ ባለሙያ እንዲያያቸው ለማገናኘት እንደምትሞክር እና አድራሻ እንደምትጠቁማቸው አክላ ታስረዳለች።

አስቀድሞ ማወቅ ይረዳል

ሴቶች የእርግዝና ክትትል ሲያደርጉ በሐኪሞች በኩል አንዲት ሴት ከወሊድ በኋላ የድህረ ወሊድ ድባቴ ሊገጥማት እንደሚችል ሊነገራት ይገባል።

ይሀንን ጉዳይ ከታወቀ በኋላ ደግሞ ቤተሰብ ልክ ሰውነቷን እንዲጠገን እንደሚረዳት ሁሉ ለአእምሮ ጤናዋም ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል።

ይህ ሕመም አንዳንድ ሴቶች ቶሎ ቢለቅም ሌሎች ላይ ግን ረዥም ጊዜ ሊቆይ ስለሚችል "የወለደች ሴት ለተወሰነ ጊዜ ብቻዋን መተው የለባትም። ምክንየቱም በዚያ ጊዜ ውስጥ በስሜት የምትወስናቸው ውሳኔዎች ስለማይታወቅ ትላለች" ማሕደር።

የተለየ ምልክት ከታየ ደግሞ ወደ ሕክምና ባለሙያ መሄድ ወሳኝ መሆኑን ታስረዳለች።

የሕክምና ባለሙያዎች ምን ይላሉ?

በጅማ ዩኒቨረስቲ መምህር የሆኑት የማሕፀንና ጽንስ ባለሙያው ዶ/ር ደምሰው አመኑ እንደሚሉት ይህ የድባቴ ሕመም በእርግዝና ጊዜም ሊያጋጥም ይችላል።

እነዚህ ሴቶች ቀድሞውኑ ሐኪም ያላወቀው የድባቴ ሕመም ሊኖርባቸውም ይችላል ይላሉ።

ይኹን እንጂ ብዙ ሴቶች በእርግዝና ጊዜ ሰውነታቸው ውስጥ የሆርሞን መለዋወጥ ስለሚፈጠር ከወሊድ በኋላ ሰውነታቸው ወደ ቀድሞ ስፍራው ለመመለስ በሚያደርገው ትግል ይህ ሕመም ሊመጣ ይችላል።

በተጨማሪም ሴቶች በሚወልዱ ጊዜ ልጃቸው ችግር ያለበት ከሆነ ሕመሙ ሊብስ ይችላል። ያደጉ አገራት መረጃ እንደሚያሳየው በአጠቃላይ 50 በመቶ የሚሆኑ ወላድ ሴቶች ይህ 'ፖስት ፓርተም ዲፕረሽን' ያጋጥማቸዋል።

በቀላሉ ሊለይ የሚችል ምልክት የሚያዩት ግን ጥቂቶቹ ናቸው ይላሉ ሐኪሙ።

እነዚህ ሴቶች ከሚያሳዩት የሕመም ምልከቶች ውስጥ

  • ከሰዎች ጋር በቀላሉ መግባባት አለመቻል
  • ለልጃቸው ተገቢውን እንክብካቤ ለመስጠት መቸገር
  • እንቅልፍ ማጣት
  • የሚቀርቧቸውን ሰዎች የመጥላት ስሜት
  • ውጥረት
  • ስሜታዊ መሆን (ማልቀስ፣ ማኩረፍ) ይኖራሉ

ቀድሞውኑ የደም ግፊት፣ ስኳር እንዲሁም ድባቴ የሚያማቸው ሰዎች ለዚህ ሕመም ይበልጥ ተጋላጭ ናቸው።

ለዚህ ሕመም የተጋለጡ ሴቶች ሌሎች ሰዎች በድባቴ ሲያዙ ከሚያሳዩት ምልክት የተለየ ላያሳዩ ይችላሉ።

ይህ ሕመም ከተወሰኑ ቀናት እስከ ስድስት ሳምንት ሊቆይ ይችላል።

አንዴ ምልክቱ ከተለየ መድሃኒት የሚሰጥ ሲሆን፣ የስነልቦና ባለሙያዎች ደግሞ የምክር ድጋፍ ይሰጣሉ።

ይህ ከወሊድ በኋላ የሚመጣ ሕመም ለልጃቸው እንክብካቤ ለመስጠት ካለመፈለግ አልፎ የራሳቸውን ሕይወት እስከማሳለፍ ድረስ ሊደርስ ይችላል ብለዋል ዶ/ር ደምሰው።

ይኹን እንጂ ሴቶች ሲወልዱ ወዲያው ሊያጋጥማቸው የሚችለው ድባቴ እዚያው የሕክምና ማዕከል ውስጥ እያሉ በቀላል ሁኔታ ድጋፍ ሊያገኙበት የሚችሉት ነው።

ከሕክምና መስጫ ከወጡ እና ከዚህ ካለፈ ግን ሊረዳቸው የሚችለው የማህፀንና ጽንስ ባለሙያ ሳይሆን የስነ አእምሮና የስነልቦና አማካሪ ድጋፍ ነው ሲሉ ተናግረዋል።