ልጁን ጡት ያጠባው አባት

የፎቶው ባለመብት, Maxamillian Kendall Neubauer
በአሜሪካ ዊስኮንሰን ግዛት የሚኖሩ ባልና ሚስት ልጃቸውን ለመገላገል ወደ ሆስፒታል አቅንተው አባትየው አስቦት የማያውቀው ነገር ገጥሞታል።
የእናት እርግዝና የተወሳሰበ ከመሆኑ በተጨማሪ ከፍተኛ የደም ግፊት ስላጋጠማት በቀዶ ጥገና ልትገላገል ችላለች።
ልጅቷ ከተወለደች በኋላም ችግሩ ባለመቀረፉ ልጇን ልታቅፍና ልታጠባም አልቻለችም።
አባት 3.6 ኪሎ ግራም የምትመዝነውን ልጁን ሰውነታቸው እንዲነካካ በማለት ልብሱን አውልቆ መጀመሪያም እንዳቀፋት ተናግሯል።
ጡጦ መጥባት እንዳለባትና በእጁ ጠብ እያረገ አፏን ሊያርሰው እንደሚገባ ነርሷ ነገረችው።
ነርሷም በመቀጠል ጡቱን እንዲሰጣትና እንዲያጠባት ነገረችው። ''ምንም ነገር ከመሞከር ወደኋላ ስለማልልና ሁሌም ስለምቀልድ ለምን አልሞክረውም አልኩ" ብሏል።
ነርሷም አባትየው ጡት ላይ ፕላስቲክ በመለጠፍ ወተቱ በሲሪንጅ እንዲተላለፍ አድርጋለች።
"ጠብቼ አላደግኩም፤ መቼም ቢሆን በሺ አመታት በጭራሽ የማላስበው ጉዳይ ነው። ልጄንም ለማጥባት የመጀመሪያው ሆኛለሁ" ብሏል።
"አማቴ የምታየውን ነገር ማመን አልቻለችም" ያለው አባት "አያቴ በመጀመሪያ ምንም ማለት ባይፈልግም በመጨረሻ ግን ሁኔታውን ተቀብሎታል"በማለት ተናግሯል።
"ከልጄ ጋር ለየት ያለ ግንኙነት እንዳለኝ ተሰምቶኛል። ልጄ ለወደፊትም ጡት እንደዚህም መጥባቱን ትለምደዋለች ብየ ተስፋ አደርጋለሁ" ብሏል።
ጡት እያጠባ የሚያሳዩ ፎቶዎች በማህበራዊ ሚዲያ ዘንድ መልካም ተቀባይነትንም አግኝተዋል።
እንዲህ አይነት አማራጭ በማቅረቧ ነርሷን ያመሰገኑ እንዳሉ ሁሉ አባትየው ጡት ማጥባቱ ግራ ያጋባቸውም አልታጡም።
ፎቶዎቹ በማህበራዊ ሚዲያዎች ሰላሳ ሺ ያህል ጊዜ የተጋራ ሲሆን ብዙዎችም መልካም አስተያየትን ችረውታል።
"መልካም አባት ለመሆን ነው ይህንን ያደረግኩት፤ ምሳሌ ለሆኑኝ ነርሶችም ጀግንነትን ለማሳየት ነው። ከነሱ የበለጠ ማንንም አታገኝም።ከዚህ ሁሉ በላይ የሆኑትን እናቶችን መዘንጋት የለብህም " ብሏል።












