ከነጭ ሴቶች ይልቅ ጥቁሮች ስለምን ጽንስ አልረጋ ይላቸዋል?

ዶረን ቶምፕሰን

በቅርብ የተደረገ አንድ ጥናት ጥቁር ሴቶች ከነጮች 40 ከመቶ በበለጠ ለጽንስ ማቋረጥ የቀረቡ ናቸው ይላል።

ይህ ጥናት በላንሴት አማካኝነት የተካሄደ ነው።

ወደ 5 ሚሊዮን እርግዝናዎችን በሰባት አገራት ክትትል በማድረግ ጥናቱ መደረጉ ልዩ ያደርገዋል።

እንዳለመታደል ሆኖ ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ በርካታ አገራት የጽንስ ማቋረጥ ላይ መረጃ አይሰበስቡም።

ነገር ግን ይህ ጥናት እንደተነበየው 15 % እርግዝናዎች በጽንስ ማቋረጥ ይደመደማሉ።

1% ሴቶች ደግሞ ከአንድ በላይ ጽንስን ያቋርጣሉ።

ጥናቱ በተጨማሪ እንዳረጋገጠው ጽንስ ያቋረጡ ሴቶች ለበርካታ ሥነልቡናዊ ምስቅልቅሎች ይጋለጣሉ። ይህም ብቻ ሳይሆን የደም መርጋት፣ የልብ ሕመም እና ድብታ ይከተላቸዋል።

ዶሪን እና ሪጌ ባልና ሚስት ናቸው። ዶሪ 7 ጊዜያት ያህል ጽንስ አቋርጣለች።

"ለመጀመርያ ጊዜ እርጉዝ የሆንኩ ጊዜ በደስታ ሰክሬ ነበር" ትላለች።

ደስታዋን ለራሷ ደብቃ ማስቀረት አልቻለችም ነበር። ጓደኞቿንና ቤተሰቧን አበሰረቻቸው። ለሚጠበቀው ልጅም ስም እንዲያወጡ አሳሰበቻቸው።

ነገር ግን እርጉዝ መሆኗን ባወቀች በ2ኛው ወር ላይ አስወረዳት።

"ስለማስወረድ ብዙ እንሰማለን። በኛ የሚከሰት ግን አይመስለንም" ትላለች።

በድጋሚ ሞከረች። አልሆነም። በሦስተኛ ጊዜ ስትሞክር አልሆነም። ተመሳሳይ ችግር ገጠማት።

ከዚህ በኋላ ነበር ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ የጤና አገልግሎት ምክር ፍለጋ ያመራችው።

ሆኖም ለምን በተከታታይ እንዳስወረዳት መልስ አላገኘችም።

ዶረን ከልጇ ጋር

የትኞቹ ሁኔታዎች በይበልጥ ለጽንስ አለመጽናት ያጋልጣሉ?

  • ከ20 ዓመት በታችና ከ40 ዓመት በላይ መሆን
  • ከዚህ ቀደም ውርጃ ተፈጽሞ ከሆነ
  • በጣም ከሲታ መሆን ወይም በጣም ወፍራም መሆን
  • ዝብርቅርቅ ያለ የሥራ ሁኔታ (በተለይ እያፈራረቁ ቀንና ሌሊት የሚሠሩ ሠራተኞች)
  • ጥቁር ሴት መሆን
  • ማጨስ
  • አደገኛ ዕጽ መጠቀምና የመጠጥ ሱሰኛ መሆን

ምን ዓይነት መፍትሄዎች ይሰጣሉ?

  • ጽንስ ለመቋጠር የሚያስችሉ የሕክምና ድጋፎችን በቅድም እርግዝና ወቅት ማግኘት
  • ተከታታይ ስካን መደረግና ጽንሰ መፈጠሩን ተከትሎ ተከታታይ የባለሙያ ክትትል ማድረግ
  • የማሕጸን አልትራሳውን በመነሳት የባለሙያ ድጋፍ ማግኘት
  • የሆርሞን ሕክምና ማድረግ
  • አስፕሪንና ሄፓሪን በሐኪም ትእዛዝ በመወጋት የደም መርጋትን ማቆም
  • ልል ማሕጸን ላላቸው ቅድመ ምርመራና ክትትል ማግኘት

አብዛኛው ጥናት የተደረገው በስዊድን፥ ፊንላንድ እና ዴንማርክ ሲሆን እነዚህ አገሮች የጽንስ መቋረጥ አሐዞችን በየፈርጁ በማደራጀት ይታወቃሉ። ሆኖም በዚህ እምብዛምም የሆኑት ዩናይትድ ኪንግደም፣ አሜሪካ፥ ካናዳና ኖርዌይም በጥናቱ ተሳትፈዋል።

"ማወቅ የቻልነው አንድ ነገር ቢኖር ጥቁር ሴቶች ከነጮች በብዙ እጥፍ በጽንስ ማቋረጥ የመሞት ዕድላቸው ሰፊ መሆኑን ነው" ይላሉ ፕሮፌሰር ሲዮብሃን ኩዩንቢ።

እኚህ ፕሮፌሰር በዩኒቨርስቲ ኦፍ ዎርዊክ መምህርና በጥናቱም ተሳታፊ የነበሩ ናቸው።

"ጥቁር ሴቶች በጽንስ ማቋረጥ እንደሚሞቱ ከቀድሞ ጥናቶችም እናውቅ ነበር። የገረመኝ ጥቁር ሴቶች ከነጭ ሴቶች ይልቅ ለውርጃ መጋለጣቸው ነው" ይላሉ ፕሮፌሰሩ።

ጥቁር ሰዎች ከነጮች የበለጠ ለስኳር በሽታ (ዓይነት 2) እና የልብ ሕመም ተጋላጭ ናቸው።

ይህ ሀቅ ምናልባት ለጽንስ ያለጊዜው ማስወረድ ምክንያት እንደሆነ ይታመናል።

ለዶሪን ይህ የጥናት ውጤት እጅግ የሚያሳዝን ሆኖ ነው ያገኘችው።

"እንዲህ ዓይነት የጥናት ውጤቶችን ስሰማ አዝናለሁ' ምናልባት ይህ የጥቁሮች ፍዳ እንዲበዛ ተቋማዊ ምክንያቶች ይኖሩ ይሆን? ለምን ጥቁር ሴቶች ጽንስ አይጸናላቸውም? ያ ከሆነ ደግሞ ከነጭ ሴቶች እኩል እንድንሆንና ለጤና ምስቅልቅል እንዳንዳረግ ተቋማዊ እኩልነት ያሻናል" ትላለች።

የአኗኗር ለውጦችን ማድረግ

ጽንስ መውረድ ከሚያጋጥማቸው ሴቶች መካከል 75 ከመቶዎቹ በድጋሚ የማርገዝ ዕድል አላቸው። ይህ በመሆኑም ነው ሐኪሞች ሴቶችን ደጋግመው እንዲሞክሩ የሚመክሩት።

ፕሮፌሰር ኩዊንቢ "የጽንስ መጽናት እንዲኖር አንዳንድ የምንረዳቸው ነገሮች አሉ" ይላሉ። ፕሮፌሰሯ የጽንስ ክትትል ሕክምናን የሚሰጥ ክሊኒክ ባለቤትም ናቸው።

አንዱ ምክር የአኗኗር ዘዬ ለውጦችን ማድረግ ነው።

እሷ ዘንድ ከመጡ 30 ከመቶ የሚሆኑት ጽንስ አልረጋ ካላቸው ታካሚዎች ውስጥ የስኳር ታማሚዎች፣ አጫሾች። የተጋነነ የሰውነት ክብደት የላቸውና የደም ግፊት የሚያሰቃያቸው ሆነው ተገኝተዋል።

ይህ ሁኔታ በአኗኗር ዘዬ ለውጥ፥ አዘውትሮ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በመሥራትና ጤናማ አመጋገብን በመከተል በድጋሚ መጸነስ የሚችሉበትን ዕድል ማስፋት ተችሏል።