በሰሜን ሸዋ ዞን የተፈጸመው ጥቃትና ያስከተለው ቀውስ

የፎቶው ባለመብት, Social media
ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በሚገኙ ወረዳዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች የበርካታ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱንና ከፍተኛ መጠን ያለው ንብረት መውደሙን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በኤፍራታ እና ግድም ወረዳ ሞላሌ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ አበይ ኃብተማርያም የተፈጠረው ጥቃት የእነርሱ ቀበሌ ላይም ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል።
"ጥቃቱ ከተጀመረ አንድ ወር ሆኖታል" ያሉት አቶ አበይ፣ መጋቢት 12/2013 ዓ.ም የመጀመሪያው ግጭት መቀስቀሱን እና በወቅቱ ግን ግጭቱ በአጎራባች ቀበሌዎች እንጂ እነርሱ ወዳሉበት አካባቢ አለመድረሱን ያስታውሳሉ።
በአሁኑ ጥቃት እርሳቸው በሚኖሩበት ሞላሌ ቀበሌ ብቻ ቢያንስ 250 የመኖሪያ ቤቶች ከነንብረታቸው በእሳት መውደማቸውንና ነዋሪዎችም ነፍሳቸውን ለማትረፍ አካባቢያቸውን ለቀው መሰደዳቸውን ተናግረዋል።
በጥቃቱ በዚሁ ቀበሌ ብቻ ከ10 ያላነሱ ሰዎች እንደሞቱ የተናገሩት አቶ አበይ ስምንት ሰዎች ደግሞ የመቁሰል ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጸዋል።
ከእሁድ ጀምሮ የመከላከያ ሠራዊትና ፌደራል ፖሊስ በአካባቢው ከተሰማራ በኋላ መረጋጋት እተመለሰ ቢሆንም፤ አቶ አበይ አሁን ያሉበትን ሁኔታ ሲናገሩም "ቤታቸው ተቃጥሎ አባት እና እናቶቻቸው የሞቱባቸው ልጆችን ይዘን ምን እንደምናደርጋቸው ጨንቆናል" ይላሉ።
ቀደም ሲል መጋቢት 12 ላይ የነበረውን ጥቃት ተከትሎ ከሞላሌ አቅራቢያ በምትገኘው ነጌሳ ቀበሌ ውስጥ የነበሩ ነዋሪዎች ቤት በመቃጠሉ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ሸሽተው በቀበሌዋ ተጠልለው እንደነበር ያስታውሳሉ።
ከዚህ በኋላ ባለፈው ሳምንት ዳግመኛ ያገረሸው ግጭት የተፈናቀሉ ሰዎች ወዳሉበት ወደሞላሌ ቀበሌ መስፋፋቱን ተናግረዋል።
አቶ አበይ እንደሚሉት በወቅቱ የመከላከያ ሠራዊት በአካባቢው ተሰማርቶ የነበረ ቢሆንም በስፍራው ብዙም ባለመቆየቱ የታጠቁት ኃይሎች ደወ ሞላሌ ቀበሌ በመምጣት ቤት ንብረት ማቃጠላቸውን ገልጸዋል።
በአሁኑ ጊዜ [ሰኞ ከሰዓት በኋላ] በአካባቢው ምንም አይነት የተኩስ ድምጽ ባይኖርም ቤት ንበረታቸው የወደመባቸው ተፈናቃዮች ግን ምንም ዓይነት እርዳታ እያገኙ አለመሆኑን ተናግረዋል።
እርሳቸው እንደሚገምቱት በቀበሌዋ ብቻ ከአምስት ሺህ በላይ ተፈናቃዮች የሚገኙ ሲሆን "መጠለያም ሆነ ምግብ ለማቅረብ ያነጋገረን የመንግሥት አካልም የለም" ብለዋል።
". . . ከሌላ አካባቢ የመጡ ናቸው"
አቶ አህመድ እንድሪስ ሲሆኑ የኩሪብሪ ቀበሌ ነዋሪ ነው።
ኩሪብሪ ቀወት ወረዳ ውስጥ የምትገኝ ቀበሌ ስትሆን ሰሞኑን የተቀሰቀሰው ጥቃት ከደረሰባቸው መካከል አንዷ ነች።
በቀበሌዋ ጥቃቱ የተፈጸመው አርብ ጠዋት እንደነበር የሚናገሩት አቶ አህመድ ሁኔታው በጣም አስቸጋሪ እንደነበር በማስረዳት "የሞተውን ሰው ለመቅበር ምቹ ሁኔታ አጥተን ማታ ከሦስት ሰዓት በኋላ ሾልከን በመሄድ ነው አውጥተን የቀበርነው" ይላሉ።
አቶ አህመድ አጎቱን ጨምሮ በጥቃቱ 11 ሰዎች እንደተገደሉ ማረጋገጣቸውን ይናገራሉ።
ከአካባቢው ነዋሪ ውጪ የመጡ ሰዎች ናቸው ጥቃቱን በመፈጸም በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሱት ታጣቂዎች የሚሉት አቶ አህመድ በከባድ መሣሪያ በመታገዝ ጥቃት መፈጸሙን ገልጾ ለጥቃቱ መንግሥትን ተጠያቂ አድርገዋል።
በቀበሌዋ የሚገኙ ነዋሪዎች ከጥቃቱ ለማምለጥ መኖሪያቸውን ለቅቀው ወደ አጎራባች የመንዝ ወረዳዎች ሸሽተዋል። በአንጻሩ በእዚህኛው ቀበሌ የሰው ሕይወት ቢጠፋም እንደሌሎች ቀበሌዎች ቤት አለመቃጠሉን አቶ አህመድ ይናገራሉ።
አካባቢው ከኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ጋር ተጎራብቶ የሚገኝ በመሆኑ በሠርግም፣ በሐዘኑም አብረን ነው የምንኖረው፣ ተጋብተናል የሚሉት አቶ አህመድ፣ "ጥቃቱን የሚፈጽሙት ታጣቂዎች ግን ከሌላ ቦታ የሚመጡ ናቸው" ሲሉ ሁኔታውን ያስረዳሉ።
ስምንት ቤተሰብ ይዘው የሸሹት አባወራ
ሌላኛው ቢቢሲ ያነጋገራቸው አቶ መላኬ የሸዋሮቢት ነዋሪ ሲሆኑ የጥቃቱን መጀመር ተከትሎ ስምንት የቤተሰባቸውን አባላት ይዘው ወደ ደብረሲና ተሰድደዋል።
እርሳቸው እንደሚሉት በሸዋ ሮቢት ችግሩ የተከሰተው ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ ሲሆን ይህንን በመስጋትም በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች አካባቢውን አስቀድመው ለቀው ለመውጣት መገደዳቸውን ይናገራሉ።
በወቅቱ ጥቃቱ ከሸዋ ሮቢት ከተማ ቀበሌዎች አንዷ በሆነችው ዙጢ ላይ ብቻ ተወስኖ ወደመሃል ከተማ አለመግባቱን ያስታውሳሉ።
አቶ መላኬ እንደሚሉት መከላከያ ሚኒስቴር ግጭቱ የተቀሰቀሰባቸው ስፍራዎች በዕዝ ማዕከል [ኮማንድ ፖስት] ስር እንዲሆኑ መወሰኑን ተከትሎ ልጆቻቸውን ደብረሲና ትተው እርሳቸው አሁን ወደቤታቸው መመለሳቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በዚህ ወቅት በሸዋሮቢት አንጻራዊ ሰላም መኖሩን የሚገልጹት አቶ መልኬ፣ እንደከዚህ ቀደሙ ባይሆንም በአብዛኛው ሰው እንቅስቃሴ እያደረገ እና ወደ መደበኛ ሕይወት እየተመለሰ መሆኑን ገልጸዋል።
ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ወደ ቀወት ወረዳ፣ ኤፍራታና ግድም ወረዳ፣ ሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር፣ ወደ ክልሉ ኮምዩኒኬሽ እንዲሁም ወደ አማራ ብልጽግና ፓርቲ በተደጋጋሚ ቢደውልም ቢያደርግም ስልካቸው ባለመነሳቱ ጥረቱ አልተሳካም።
እሁድ አመሻሹ ላይ የመከላከያ ሠራዊት ከሰሜን ሸዋ ዞን ደብረ ሲና ጀምሮ እስከ ደቡብ ወሎ ዞን ኮምቦልቻ ከተማ ድረስ ያሉት አካባቢዎች በኮማንድ ፖስት ውስጥ መሆናቸውን ገልጿል።
በእነዚህ አካባቢዎችም ከዋናው መንገድ በ20 ኪሎ ሜትር ርቀት ዙሪያ መሣሪያ ይዞ መንቀሳቀስ እንደማይቻል ተደንግጓል።
በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋና በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞኖች ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት ግችቶችና ጥቃቶች ሲፈጸሙ የቆዩ ሲሆን አሁን የተፈጸመው ግን እስካሁን ካጋጠሙት መካከል ሰፊ ቦታዎችን ከማዳረሱ በተጨማሪ ባስከተለው ጉዳት ቀደም ካሉት የከፋ መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ።
የአካባቢው ባለስልጣናት በአሁኑ ጊዜ የተፈናቀሉትን ወደ መኖሪያቸው ለመመለስና ቀሪውን ነዋሪ ለማረጋጋት ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ባለፉት ቀናት በተፈጸመው ጥቃት በሰውና በንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት ዝርዝር ለማወቅ አለመቻላቸውን ገልጸዋል።
ባለፈው መጋቢት ወር በአካባቢው በነበረ ጥቃትና ግጭት በተመሳሳይ ከባድ የሚባል ጉዳት የደረሰ ሲሆን በክስተቱ ከ300 በላይ ሰዎች መሞታቸውን ኤኤፍፒ የኢትዮጵያ እንባ ጠባቂ ተቋምን ባለስልጣንን ጠቅሶ መዘገቡ ይታወሳል።
ማን ምን አለ?
የአማራ ክልል የሰላም እና ደኅንነት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሲሳይ ዳምጤ በቀጠናው ከፍተኛ ጉዳት ማጋጠሙን ገልጸው ይህንን ጥፋት ያደረሰውም 'ኦነግ ሸኔ' መሆኑን ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን መግለጻቸው ይታወሳል።
አካባቢውን ሙሉ በሙሉ ጥቃት ካደረሰው ቡድን ነጻ ለማድረግ በቅንጅት እየሠሩ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ሲሳይ የመኖሪያ ቀየውን ለቆ ወደ ደብረሲናና ወደ ተለያዩ አካባቢዎች የሸሹ ነዋሪዎችን ለመመለስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በአማራ ክልል ውስጥ በሚገኘው የኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን የጅሌ ድሙጋ ወረዳ አስተዳዳሪ አሮ ሰይድ ጀማል ሐሰን ለሮይተርስ ዜና ወኪል እንደተናገሩት አርብ ዕለት ግጭቱ የተቀሰቀሰው "የአማራ ክልል ጸጥታ ኃይሎች አንድ ባለሱቅን መግደላቸውን ተከትሎ ነው።"
ጨምረውም "በአንድ ጤና ኬላ ውስጥ ብቻ 53 የቆሰሉና 18 የሞቱ ሰዎችን አይቻለሁ። ሁሉም ኦሮሞዎች ናቸው" ሲሉ አስተዳዳሪው ተናግረዋል።
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ ያለችው የቀወት ወረዳ አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ኤሊያስ አበበ እንዳሉት ውጊያው የተጀመረው ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር በተለየው ኦነግ-ሸኔ በተባለው ታጣቂ ቡድን እንደሆነ ለሮይተርስ ገልጸዋል።
እንዲሁም በአካባቢያቸው ስለደረሰው ጉዳት መረጃ እያሰባሰቡ መሆኑን ነገር ግን "በርካታ ሰዎች ሞተዋል፣ አብያተ ክርስቲያናት ሳይቀሩ ተቃጥለዋል" ሲሉም ተናግረዋል።
ሮይተርስ ከአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አለመሳካቱን ገልጿል።
በአማራ ክልል በስፋት የሚንቀሳቀሰው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲ ለችግሩ ዋነኛ ተጠያቂ ጠቅላይ ሚንስትሩ እና እርሳቸው የሚመሩት ብልጽግና ፓርቲ ናቸው ሲል መግለጫ አውጥቷል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ፤ ኢዜማ ደግሞ ጥቃቱን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ መንግሥት በአካባቢው በተደጋጋሚ የተከሰተውን ችግር "መነሻውን መርምሮ ከምንጩ ከማድረቅ ይልቅ ችግር በተፈጠረ ቁጥር ሠራዊት ሲያዘምት እና የተረጋገ ሲመስለው ሠራዊት ሲያሰወጣ ተመልክተናል" ብሏል።
ጨምሮም እንዲህ አይነቱ እርምጃ ትክክለኛ መፍትሄ አይደለም በማለት "መንግሥት የአስተዳደራዊና የጸጥታ መዋቅሩን መመርመር እንዳለበት" አሳስቧል።
የተቃውሞ ሰልፍ በደሴ
ሰሞኑን በሰሜን ሸዋ ዞን በሚገኙ ከተሞች የተፈፀመውን ጥቃት በመቃወም ዛሬ በደሴ ከተማ በርካታ ሰዎች አደባባይ በመውጣት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
ካለፈው ሳምንት ማብቂያ ጀምሮ በተፈጸሙ ተከታታይ ጥቃቶች ቁጥራቸው በውል ያልተገለጸ ሰላማዊ ሰዎችና የፀጥታ አካላት መገደላቸው የተነገረ ሲሆን በንብረትም ላይ ከፍተኛ ውድመት ደርሷል።
ሰልፉ የሰሞኑን ጥቃት መነሻ ያደረገ ቢሆንም በተለያየ ጊዜያት በኦሮሚያ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈፀመውን ጥቃትም የሚያወግዝ እንደነበር ቢቢሲ ያነጋገራቸው የሰልፉ ተሳታፊዎች ገልጸዋል።
የደሴ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ማዘንጊያ አበበ ስለ ሰልፉ ሲናገሩ የሰልፉ መንፈስ "በየቦታው በአማራ ላይ የሚፈፀመው ግድያ መቆም አለበት የሚል እንደነበር" ተናግረው፤ መንግሥት ይህንን ጥቃት እንዲያስቆም መጠየቁንም አመልክተዋል።
ሌላኛው ስሜ አይጠቀስ ያለ የሰልፉ ተሳታፊም በተለያዩ ስፍራዎች የሚገኙ የአማራ ተወላጆች ላይ የሚደርሰው መፈናቀልና ግድያ እንዲቆም የጠየቀ መሆኑን አመልክቶ "የማንም ፓርቲ አባል ሆነን ሳይሆን በንጹሃን ላይ የሚደርሰውን ግድያ እና መፈናቀል ተቃውመን ነው የወጣነው" ብሏል።
መንግሥት ብሔር ተኮር መፈናቀል እና ግድያን እንዲያስቆም፣ በሰልፉ ላይ መጠየቁን የሚናገረው ስሙ እንዳይገለፅ የጠየቀው ይህ ግለሰብ፣ ዜጎች በሰላም ወጥተው እንዲገቡ እንዲያደርግ መጠየቁ ተናግሯል።
ይህ ሰልፍ ማኅበረሰቡ በራሱ ተነሳሽነት ያካሄደው ሰልፍ እንደሆነ የተናገሩት ሌላኛው የደሴ ከተማ ነዋሪ አቶ ጋሻው ጉግሳ ተናግረዋል።
የደሴ ከተማ የሕዝብ ሰላምና ደኅንነት መምሪያ ኃላፊ ዋና ኢንሰፔክተር ሐሰን መሐመድ ሰልፉ መካሄዱን አረጋግጠው በሰላም መጠናቀቁን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
"ለልፉ የወጡ ግለሰቦች አስፈቅደው ሳይሆን በራሳቸው ተነሳሽነት የወጡ ናቸው" ያሉት ኢንስፔክተር ሐሰን የትኛውም የከተማው አስተዳደር ተወካይ አለመገኘቱን ጨምረው ተናግረዋል።












