በሰሜን ሸዋ ዞን የተፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ለቀው እየወጡ ነው

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በተፈፀመ ጥቃት ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ተገለጸ።
የዞኑ የጸጥታ ኃላፊ አቶ አበራ መኮንን ለቢቢሲ እንደገለፁት ጥቃቱ የተፈፀመው በዞኑ በሚገኙ አምስት ወረዳዎች ውስጥ ሲሆን "በጣም ከፍተኛ" ቁጥር ያለው የታጠቀ ኃይል "ወረራ" መፈፀሙን ተናግረዋል።
የታጠቀው ኃይል "ቤቶችን ያቃጥላል፤ ሰዎችን ይገድላል" በማለትም ወደ አካባቢው የገባው የፌደራል የጸጥታ መዋቅርና የመከላከያ ሠራዊትም "ከአቅሙ በላይ" መሆኑን ለቢቢሲ አስረድተዋል።
የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ለክልሉ መገናኛ ብዙሃን ተቋም እንደተናገሩት በጥቃቱ የደረሰው ጉዳት የከፋ መሆኑን አመልክተዋል።
ለጥቃቱም "ኦነግ ሸኔ እና ሌላ ተከታይ" ያሉትን አካል ተጠያቂ አድርገዋል። በጥቃቱ የጸጥታ አካላት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን አክለዋል።
ከትናንት በስቲያ ሐሙስ ማታ ጀምሮ በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን እና በሰሜን ሸዋ ዞን መካከል በሚገኙ አካባቢዎች የጸጥታ ችግር መኖሩን ገልጸው፤ ይህ ግን ጋብ ብሎ እንደነበር ኃላፊው አስታውሰዋል።
ይሁን እንጂ ትናንት አርብ ከረፋዱ 5፡00 ሰዓት ጀምሮ ከፍተኛ የታጠቀ ኃይል ወደ አካባቢው በመግባት በአጣዬ፣ በአንጾኪያና በኤፍራታ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተናግረዋል።
ኃላፊው እንዳሉት በጥቃቱ የጸጥታ አካላት እና የንጹሃን ሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን ከፍተኛ የሆነ ንብረትም ወድሟል።
ከሦስት ሳምንታት በፊት በአካባቢዎቹ በተፈፀመ ጥቃትና ግጭት የበርካታ ሰዎች ሕይወት ማለፉና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወሳል።
ነዋሪዎች ምን ይላሉ?
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ጥቃቱ በተፈፀመባቸው አጣዬ፣ ሸዋ ሮቢት፣ ካራ ቆሬ፣ ማጀቴ እና ሌሎች አካባቢዎች በርካታ ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው፣ ቤቶች መቃጠላቸውንና ንብረቶች መውደማቸውን ተናግረዋል።
ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ የኤፍራታና ግድም ወረዳ ነዋሪ "ትናንት ረፋድ ላይ ጀምሮ በርሃ አርሶ አምባና ብርቂቶ ከሚባለው አገር "ሰው አለቀ፤ ተለበለበ" ሲሉ የደረሰውን ጉዳት ገልጸዋል።
እርሳቸው አካባቢውን ለቀው እንደወጡ የገለጹት እኝህ ነዋሪ፤ ጥቃቱን የፈፀሙት "የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎችና ሌሎች የህወሓት ኃይሎች" ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።
በርካታ ንጹሃን ሰዎችና የጸጥታ ኃይሎች መገደላቸውንና የቤት እንስሳት፣ የተሰበሰበ ሰብል ሳይቀር መቃጠሉንና ነዋሪዎችም አካባቢያቸውን ለቀው እየወጡ መሆኑን ተናግረዋል።
"ሰዉ በእንዲህ ያለ ጥቃት ካለቀ በኋላ መንግሥትም ምኑን የስተዳድራል? ድንጋይ አይገዛ፤ ሰው እኮ ነው የሚገዛው" ሲሉ መንግሥት የነዋሪውን ደኅንነት እንዲጠብቅ ተማጽነዋል።
ትናንት ምሽት አርብ ያነጋገርናቸው እኝህ ነዋሪ፤ በአካባቢው የተኩስ ድምፅ እንደሚሰማ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
ሌላኛዋ የአጣዬ ነዋሪም ከዚህ በፊት በነበረው ግጭት የመከላከያና ሠራዊትና የፌደራል ፖሊስ በመግባቱ ተረጋግተው መቀመጣቸውን አስታውሰው፤ የዚህ ቀደሙ ጉዳት ሳይሽር ሌላ ጥቃት መፈፀሙ እንዳሳዘናቸውና የሕግ የበላይነት አለመከበሩ አሳሳቢ መሆኑን ተናግረዋል።
እርሳቸውም ቤተሰባቸውን ይዘው ወደ መሃል ሜዳ እየሄዱ እንደሆኑ የገለፁት እኝህ ነዋሪ "አሁንም ግጭት አለመቆሙንና የከተማው ነዋሪ በሙሉ ወደ ደብረ ብርሃንና እና መሃል ሜዳ ለቆ ሸሽቷል" ብለዋል።
በከተማው የገባው የጸጥታ ኃይልም ጥቃት የሚፈጽመው ኃይል ከአቅሙ በላይ መሆኑንና በከተማዋ ቃጠሎ መኖሩን ነዋሪው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገብረ ጻዲቅ ለአገር ውስጥ ሬዲዮ እንደተናገሩት በጥቃቱ በርካታ ሰዎች መሞታቸውንና በንብረት ላእ ከባድ ጉዳት መድረሱን አመልክተው "መንግሥት አስቸኳይ እርምጃ ወስዶ ኃይል ካልመደበ ችግሩ ከዚህም በላይ የከፋ ይሆናል" ብለዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን የጸጥታ ኃላፊ አቶ አበራ "ችግሩ በአጠቃላይ ከቁጥጥር ውጭ ሆኗል" በማለት ሕዝቡን የማረጋጋት አስቸኳይ ሥራ እየሰሩ መሆናቸውን ገልፀው፤ ቢቢሲ ላቀረበላቸው ጥያቄ ዝርዝር ማብራሪያ ከመስጠት ተቆትበዋል።
አቶ ግዛቸው ትናንት ምሽት ለክልሉ ሚዲያ በሰጡት መረጃ፤ ጥቃቱ ያልበረደ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ሆነው ወንጀል ፈጻሚዎችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ከሦስት ሳምንታት በፊት በሰሜን ሸዋና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች ውስጥ በተከሰተ ግጭት የበርካታ ሰዎች ሕይወት ማለፉ ይታወሳል።
በግጭቱ የደረሰው ጉዳት በዝርዝር ባይገለፅም፤ የኢትዮጵያ እንባ ጠባቂ ተቋምን ጠቅሶ ኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደዘገበው ከ300 በላይ ሰዎች ሕይወት አልፏል።
የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች በአካባቢው በተደጋጋሚ ስለሚፈፀመው ጥቃት ያሉት ነገር የለም።
በወቅተ ግጭቱን ለመቆጣጠርና ነዋሪውን ማረጋጋት የፌደራል ፖሊስና የመከላከያ ሠራዊት ወደ አካባቢው እንዲገቡ ተደርጎ ነበር።
በወቅቱ በአካባቢው ስለተከሰተ ግጭት የገዢው የብልጽግና ፓርቲ የአማራና የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፎች የተለያዩ መግለጫዎችን በማውጣት ሲወዛገቡ ነበር።
የአማራ ብልጽግና በወቅቱ ባወጣው መግለጫ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎችን ለጥቃቱ ተጠያቂ ያደረገ ሲሆን፤ የኦሮሚያ ብልጽግና በበኩሉ በአካባቢው ኦነግ ሸኔ እንደማይንቀሳቀስ መግለጹ ይታወሳል።
በዚያው ሰሞን በምዕራብ ወለጋ ጥቃት መፈፀሙን ተከትሎ የአማራ ክልል መንግሥትም በአማራ ተወላጆች ላይ የሚደርስ ጥቃት እንዲቆም የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገባና በአስቸኳይ መወያየት እንደሚፈልግ ገልጾ ነበር።
ይህንንም ተከትሎ የሁለቱ ክልል አመራሮች በአዲስ አበባ ተገናኝተው ችግሮችን በጋራ ለመፍታት መስማማታቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
በምን ጉዳይ ላይ እንደተወያዩ ግን በዝርዝር አልተገለጸም።















