"ህይወቴን እንዳጣ የሚደረግ ሙከራ ነው" አቶ ልደቱ አያሌው

አቶ ልደቱ አያሌው

የፎቶው ባለመብት, THE REPORTER

ለሦስተኛ ጊዜ ህክምና ለማግኘት ወደውጪ አገር እንዳይሄዱ የተከለከሉት ፖለቲከኛው አቶ ልደቱ አያሌው ድርጊቱ በህክምና እጦት "ህይወቴን እንዳጣ የሚደረግ ሙከራ ነው" አሉ።

አቶ ልደቱ አያሌው ለቢቢሲ ይህንን የተናገሩት ለህክምና ወደ ውጪ አገር ሊያደርጉት የነበረው ጉዞ ለሦስተኛ ጊዜ ከተስተጓጎለና ፓስፖርታቸው ከተወሰደ በኋላ ነው።

ያለባቸው የጤና ችግር በአገር ውስጥ ሊታከም የማይችል "የልብ ጉዳይ ነው። ከልብም የደም ቧንቧ መዘጋት [አርተሪ ብሎኬጅ] ነው። ስለዚህ ተገቢውን ህክምና ካላገኘሁ ለህይወቴ የሚያሰጋ ነው" ነው ሲሉ ጨምረው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ ልደቱ ከዓመት ከስምንት ወር በፊት ተመሳሳይ ህክምና ማግኘታቸውን ገልጸው፤ በአሁኑ ጉዟቸው የተደረገላቸው ህክምና በትክክል ስለመስራቱ ለማረጋገጥና ተጨማሪ ቀዶ ህክምና ለማድረግ ነበር።

የጤና ችግራቸው ያለህክምና የሚድን ስላልሆነ እንዲሁም የሚያስፈልጋቸው ህክምና ደግሞ በአገር ውስጥ ስለሌለ ያሉበት ሁኔታ "ለህይወቴ አስጊ" ነው ብለዋል።

በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ተጠርጥረው ለወራት በእስር ላይ የቆዩት አቶ ልደቱ አያሌው ባለባቸው የጤና ችግር ምክንያት እራሳቸውን ከዚህ በፊት ሲያደርጉት ከነበረው ንቁ የፖለቲካ ተሳትፎ ማግለላቸውን በቅርቡ መግለጻቸው ይታወሳል።

የተደረገባቸውን ተደጋጋሚ የጉዞ ክልከላ በተመለከተ "ምን ያህል ያለአግባብ ህይወቴን እንዳጣ እየተሞከረ እንደሆነ የሚያሳይ ነው። እኔም ከዚህ የተለየ ትርጉም ልሰጠው አልችልም" ብለዋል።

አቶ ልደቱ ካለባቸው የልብ ህመም ጋር በተያያዘ ከዚህ በፊት የተደረገላቸው ህክምና ያለበት ሁኔታን ለማወቅና ተጨማሪ ተከታይ ህክምና ለማግኘት ነበር ወደ አሜሪካ ሊጓዙ የነበረው።

ሐሙስ ዕለት ወደ አሜሪካ ለመሄድ ወደ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ያቀኑት አቶ ልደቱ ሻንጣቸውን አስረክበው ወደ አውሮፕላን ለመሳፈር የመጨረሻ ፓስፖርት በሚያሳዩበት ጊዜ ከአገር እንዳይወጡ እገዳ እንዳለባቸው በመግለጽ እንደመለሷቸው ተናግረዋል።

በዚህ ጊዜ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት የተጻፈ ደብዳቤን ቢያሳዩም "የፍርድ ቤት እገዳ ስላለብህ መውጣት አይችሉም" እንደተባሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ ልደቱ ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ ከአገር እንዳይወጡ በኢሚግሬሽን ሠራተኞች ተከልክለው እንደነበር መናገራቸው የሚታወስ ሲሆን፤ ሁለቱንም ጊዜ ጉዞ እንዳያደርጉ የተከለከሉት በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት መሆኑን ገልጸዋል።

ከአገር እንዳይወጡ በተከለከሉበት ጊዜ ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አቤቱታ አቅርበው የነበሩት አቶ ልደቱ፤ ክልከላው በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አለመፈጸሙን መግለጹ ይታወሳል።

የደኅንነት መሥሪያ ቤቱን ምላሽ ተከትሎም የነበረው ችግር ተፈትቷል በሚል ጉዞ ለማድረግ መነሳታቸውን የሚጠቅሱት አቶ ልደቱ፤ ነገር ግን ውጤቱ ቀደም ካሉት ጉዞዎች ጋር ተመሳሳይ ሆኗል ብለዋል።

ሐሙስ ዕለት ጉዞ ማድረግ እንደማይችሉ በተነገራቸው ጊዜም ለኮሚሽኑ ዋና ኃላፊ ለዶክተር ዳንኤል በቀለ በስልክ እንዳሳወቁና እሳቸውም የኢሚግሬሽን ባለስልጣናትን ለማነጋገር መሞከራቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዶ/ር ዳንኤልም ያገኙት መልስ "መውጣት አይችልም፤ የፍርድ ቤት እገዳ አለበት " የሚል ነበር ያሉት አቶ ልደቱ ከዚህ በኋላ ለጉዞ አስረክበው የነበረውን ሻንጣቸውን በመቀበል መመለሳቸውን ገልጸዋል።

ቀደም ባለው የጉዞ ክልከላ ወቅት "የመለሱኝ ብሔራዊ ደህንነቶች ናቸው። ሁለቱንም ጊዜ ሲመልሱኝ የፍርድ ቤት እገዳ አለብህ፤ መውጣት አትችልም እያሉ ነው። የት ነው የፍርድ ቤት እገዳ ያለብኝ ስላቸው የሚነግሩኝ ነገር የለም።" ብለዋል።

ለሦስተኛ ጊዜ ለህክምና የሚያደርጉት ጉዞ በማያውቁት ምክንያት መስተጓጎሉን የሚናገሩት አቶ ልደቱ፤ "ሁለት ጊዜ ከአገር እንዳልወጣ የከለከለኝ ብሔራዊ ደኅንነት ነበር" ብለዋል።

ቢቢሲ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት እንዲሁም ከኢሚግሬሽን መሥሪያ ቤት በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ለአሁን አልተሳካም።

በአንደበተ ርቱዕነታቸው የሚታወቁት አቶ ልደቱ አያሌው ለረጅም ዓመታት በተቃውሞው ፖለቲካ ውስጥ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ ፖለቲከኞች መካከል አንዱ ሲሆኑ፤ በተለይ በአወዛጋቢው የ1997 ምርጫ ወቅት በነበራቸው ሚና ከፍ ያለ እውቅና አግኝተዋል።

አቶ ልደቱ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ የተለያዩ ክሶች ቀርበውባቸው በኦሮሚያ ፖሊስ ቁጥጥር ስር ለበርካታ ወራት የቆዩ ሲሆን በመጨረሻም ከቀረቡባቸው ክሶች ነጻ ተብለው መለቀቃቸው ይታወሳል።