ታዋቂው ሶማሊያዊ ጋዜጠኛ በቦምብ ጥቃት ተገደለ

አብዲአዚዝ መሀሙድ ጉሌድ

የፎቶው ባለመብት, @Abdiaziz_afrika/Twitter

አልሸባብን በሰላ በመተቸት የሚታወቀው ሶማሊያዊ ጋዜጠኛ በዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ ውስጥ በተፈጸመ የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት ተገድሏል።

አብዲአዚዝ መሀሙድ ጉሌድ ወይም አብዲአዚዝ አፍሪካ በመባል የሚታወቀው ይህ ጋዜጠኛ ከቀትር በኋላ በከተማው ከሚገኝ ሬስቶራንት ሲወጣ ኢላማ ተደርጎም ነው የተገደለው።

ከጋዜጠኛው በተጨማሪ በአካባቢው የነበሩ ሁለት ሰዎች በፍንዳታው ቆስለው ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።

በሬድዮ ሞቃዲሾ ይሰራ የነበረው ይህንን ጋዜጠኛ ኢላማ እንዳደረገውና ጥቃቱንም እንዳቀነባበረ አልሸባብ አስታውቋል።

የአጥፍቶ ጠፊ ቦምብ ጥቃቱ የደረሰው ጉሌድ ከሶማሌ ብሄራዊ ቴሌቪዥን ዳይሬክተር እና አንድ ሹፌር ጋር ሬስቶራንቱ አቅራቢያ በሚገኝ አንድ መኪና ፊት ለፊት መሆኑን የሬድዮ ሞቃዲሾ ድረገፅ የፖሊስ ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።

ዘገባው አክሎም የሶማሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር መሀመድ ሁሴን ሮብሌ ሃዘናቸውን ለጉሌድ ቤተሰቦች መግለፃቸውን አትቷል።

"አብዲአዚዝ ለሀገሩ፣ ለወገኑ እና ለሃይማኖቱ በድፍረት እና ያለ እረፍት የሰራ ታታሪ ጋዜጠኛ እና የሀገር ጀግና ነበር" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው

ጉሌድ በአልሸባብ ታስረው ከተፈቱ ተጠርጣሪዎች ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ የሚታወቅ ሲሆን የሚያቀርበው ስርጭቱም በርካታ ታዳሚዎችን ይስባል።

በአረብኛ ቋንቋ ወጣት የሚል ትርጉም መጠሪያውን የያዘው አልሸባብ በተባበሩት መንግስታት የሚደገፈውን የመንግስት ወታደሮችን ከአስር አመታት በላይ ሲዋጋ የነበረ ጽንፈኛ እስላማዊ ቡድን ነው።

ቡድኑ ዋና ከተማዋን ሞቃዲሾን በአውሮፓውያኑ እስከ 2011 ድረስ በአፍሪካ ህብረት ወታደሮች ተገፍተው እስከወጡበት ጊዜ ድረስ ተቆጣጥሮ የነበረ ቢሆንም አሁንም በገጠር ውስጥ ግዛቶችን ተቆጣጥረው በሞቃዲሾ እና በሌሎችም ቦታዎች በመንግሥት እና በሲቪል ኢላማዎች ላይ ያነጣጠሩ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ይሰነዝራሉ

ቡድኑ በሳዑዲ በመነሳሳት ጥብቅ የሆነውን የዋሃቢ እስልምናን የሚደግፍ ሲሆን አብዛኞቹ ሶማሌዎች ደግሞ ሱፊዎች ናቸው።

በዝሙት የተከሰሱ ሴቶችን በድንጋይ ወግሮ በመግደል እና የሌቦችን እጅ መቁረጥን ጨምሮ በቁጥጥሩ ሥር ባሉ ቦታዎች ላይ ከባድ የሸሪዓ ህግን ተግባራዊ አድርጓል።

በሶማሊያ ለደረሱ አስከፊ የሽብር ጥቃት የመንግስት ባለስልጣናት ቡድኑን ተጠያቂ አድርገዋል።

ባለፈው አመት አርምድ ኮንፍሊክት ሎኬሽን ኤንድ ኢቨንት ፕሮጀክት የተባለ ድርጅት ባወጣው መረጃ መሰረት በአውሮፓውያኑ 2010 ጀምሮ ከ4 ሺህ በላይ ሰዎችን ለህልፈት የዳረገው አልሸባብ ነው።