የትውልድ ኢትዮጵያዊው አቤል ተስፋዬ ሥራ በቢልቦርድ ላይ የምንጊዜም አንደኛ ሙዚቃ ሆነ

አቤል ተስፋዬ (ዘ ዊኬንድ)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

'ብላይንድ ላይትስ' የተሰኘው የትውልደ ኢትዮጵያዊው የካናዳ ዜጋ ሙዚቀኛ አቤል ተስፋዬ ወይም 'ዘ ዊክንድ' ሙዚቃ በቢልቦርድ የሙዚቃ ሰንጠረዥ ላይ የምንጊዜም ቁጥር አንድ ዘፈን ለመሆን ቻለ።

በቢልቦርድ መረጃ መሰረት የዘ ዊኬንድ 'ብላይንድ ላይትስ' ሙዚቃ ላለፉት 90 ሳምንታትን ምርጥ 100 ዘፈኖች ከተባሉት ውስጥ ቆይቷል።

በዚህም 'ብላይንድ ላይትስ' በ1960ዎቹ የወጣውን የቹቢ ቼከርን 'ዘ ትዊስት' የተሰኘውን ሙዚቃ የቢልቦርድ ሰንጠረዥ ቦታ በመቆጣጠር አንደኛ መሆን ችሏል።

የቢልቦርድ ምርጥ መቶ ላለፉት 63 ዓመታት አንድ ሙዚቃ በሬዲዮ ላይ የሚጨወትበትን የሽያጭ እና የስርጭት ላይ መጠን ላይ በመመርኮዝ ምርጥ ዘፈኖችን ሲያቀርብ ቆይቷል።

አቤል ተስፋዬ ወይም ዊኬንድ እንደ አውሮፓውያኑ በኅዳር 2019 የለቀቀው 'ብላይንድ ላይትስ' እንደ አውሮፓውያኑ በ መስከረም 2021 ስፖቲፋይ ላይ ከ2.5 ቢሊዮን ጊዜ በላይ ተደምጧል።

ሙዚቃው በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ቲክ ቶክ መግነኑ እና እንደ አውሮፓውያኑ በ2021 በአሜሪካ ትልቁ የስፖርት ውድድር ሱፐር ቦውል የእረፍት ሰዓት ላይ መቅረቡ ለዚህ ስኬት አብቅቶታል።

በቹቢ ቼከርስ የተቀነቀነው 'ዘ ትዊስት' የተሰኘው እና በቢልቦርድ አንደኛ ሆኖ የቆየው ሙዚቃ ከአቤል ተስፋዬ 'ዘ ዊኬንድ' ጋር ተመሳሳይ አይነት የሙዚቃ ስልት ያለው ሲሆን አሁን ወደ ሁለተኛ ደረጃ ደረጃ ዝቅ ብሏል።

ትውልደ ኢትዮጵያዊው አቤል ተስፋዬ (ዘ ዊክኤንድ) ከሙዚቃው ባሻገር ለሰብአዊ እርዳታ ከፍተኛ ገንዘብ በመለገስ የሚታወቅ ሲሆን፣ በቅርቡም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም የበጎ ፈቃድ አምባሳደር አድርጎ ሰይሞታል።