አቤል ተስፋዬ (ዘ ዊኬንድ) የዓለም ምግብ ፕሮግራም አምባሳደር ሆነ

አቤል ተስፋዬ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አቤል ተስፋዬ

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ታዋቂውን ትውልደ ኢትዮጵያዊ ድምጻዊ አቤል ተስፋዬን የበጎ አድራጎት አምባሳደሩ አድርጎ ሾመ።

'ዘ ዊኬንድ' በሚለው የመድረክ ስሙ የሚታወቀው ድምጻዊው፤ በመላው ዓለም ረሃብን ለማስወገድ ከሚታገሉ በጎ ፈቃደኛ የዓለም ምግብ ፕሮግራም አምባሳደሮች ጋር በጋራ የሚሠራ ይሆናል።

ዘ ዊኬንድ ከወራት በፊት በትግራይ ክልል በተነሳው ጦርነት ለተጎዱ ሰዎች የሚውል አንድ ሚሊዮን ዶላር ለዓለም ምግብ ፕሮግራም መለገሱ ይታወሳል።

ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ፤ ዘ ዊኬንድ ይህንን አንድ ሚሊዮን ዶላር ጨምሮ ባለፈው ዓመት ለተለያዩ የረድዔት ድርጅቶች ከሦስት ሚሊዮን ዶላር በላይ እርዳታ ለግሷል።

በተባበሩት መንግሥታት ስር ያለው የዓለም ምግብ ፕሮግራም በየዓመቱ ከ80 በላይ በሆኑ አገራት ውስጥ የሚገኙ ከ100 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ሕይወት አድን የምግብ ድጋፍ ያደርጋል።

ከኢትዮጵያዊያን ቤተሰቦች ካናዳ ውስጥ የተወለደው አቤል ተስፋዬ [ዘ ዊኬንድ] በሰሜን ኢትዮጵያ የተነሳው ጦርነት ተጽዕኖ እንዳሳደረበት እና ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ጋር በቅርበት እየሠራ እንደሚገኝም ተገልጿል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም በተለያዩ አገሮች ነፍስ አድን የምግብ እርዳታ የሚሰጥ ትልቁ ተቋም ነው።

አሁን ላይ በሰሜን ኢትዮጵያ ሰብአዊ እርዳታ እያደረጉ ከሚገኙ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መካከልም ይጠቀሳል።

ድርጅቱ እርዳታ ከመስጠት ባሻገር ዓለም አቀፍ ተቋማትን እንዲሁም ግለሰቦችን ለድጋፍ በማስተባበር ይታወቃል።

በሙዚቃ ሥራዎቹ ከፍተኛ የሚባሉ የበርካታ ፕላቲኒየም እና ዳይመንድ ተሸላሚው ዘ ዊኬንድ በፖፕ ሙዚቃ ዝነኛ ከሆኑ ድምጻዊያን አንዱ ነው።

አቤል ተስፋዬ ስፖቲፋይ በተሰኘው የበይነ መረብ የሙዚቃ ማድመጫ መድረክ ላይ ከ86 ቢሊዮን ጊዜ በላይ በመደመጥ፤ ዘፈናቸው በርካታ ጊዜ ከተሰማላቸው ድምጻዊያን መካከል በዋናነት ይጠቀሳል።

ድምጻዊው ሁሉም ሙዚቀኞች የማያገኙትን የአሜሪካን ታላቁ የስፖርት ውድድር ሱፐር ቦውልን ጨምሮ በታላላቅ መድረኮች ሥራውን ለማቅብ የበቃ የዘመኑ ኮከብ ነው።

አምና ያወጣው "አፍተር አወርስ" የተባለው አልበም የምንጊዜም ምርጥ አርኤንድቢ ዝርዝር ውስጥ አንደኛነቱን መቆጣጠሩ ይታወሳል።