ዘ ዊኬንድ ፡ ድምጻዊ ኤቤል ተስፋዬ 'የግራሚ ነገር ባፍንጫዬ ይውጣ' አለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ካናዳዊው ድምጻዊ አቤል ተስፋዬ (ዘ ዊኬንድ) ለዚህ ዓመት የግራሚ ሽልማት አለመታጨቱን በማስመልከት ተጠይቆ በሽልማት ድርጅቱ መዘንጋቱ ግድ እንደማይሰጠው ተናገረ።
ድምጻዊ አቤል ተስፋዬ የዛሬ ሳምንት እሁድ፣ ፌብሩዋሪ 7 2021 ለሚያቀርበው የሱፐር ቦል ትርዒት እየተዘጋጀ ባለበት፤ በሕዳር ወር በተደረገው የግራሚ ሽልማት እጩዎች ዝርዝር ውስጥ ስሙ ስላለመካተቱ ምን እንደተሰማው በቢልቦርድ ተጠይቆ ነበር።
"በግሌ ከዚህ በኋላ ግድ አይሰጠኝም። አሁን ለኔ ምንም ማለት የሆኑ ሶስት የግራሚ ሽልማቶች አሉኝ" ብሏል።
"ንግግር ማድረግ ሰልችቶኛል። የሽልማት ዝግጅቶችን እርሷቸው" ሲል አክሏል።
በተጨማሪም ማሸነፍ እንደሚፈልግ ገልጾ "'ግራሚ ማሸነፍ እፈልጋለሁ። በቃ ይህ ነው የሆነው። ያ እስካልሆነ ድረስ አሁን በተንቆጠቆጠ መብራት ታጅቤ ማቀንቀን ነው የምፈልገው" ብሏል።
ዘ ዊኬንድ በአሁን ሰዓት ትኩረቱ ምን እንደሆነ ሲናገር "ለአድናቂዎቼ ከቤቴ መደወል እንዲሁም የሲኒማ ቀለምና ይዘት ያላቸው የሙዚቃ ድግሶችን ማቅረብ ነው የምፈልገው። ያንን ደግሞ በሱፐር ቦል ላይ ለማድግ እንፈልጋለን።"
የሙዚቀኛው ማናጄር የሆነው ዋሲም "ሳል" ስላይቤይ፤ የሱፐር ቦል ትርዒትን ያዘጋጁ አካላት የመድረክ ዝግጅቱን እና ተያያዥ ወጪዎችን ቢሸፍኑም ድምጻዊው ግን ከኪሱ 7 ሚሊዮን ዶላር በማውጣት "የሱፐር ቦል ዝግጅትን እንደሚያስበው ለማድረግ እየሰራ ነው" ብሏል።
ድምጻዊው በነሐሴ ወር ላይ ኤምቲቪ ቪኤምኤ ሽልማትን ባሸነፈ ወቅት ትኩረትን የሳበ ዝግጅት አቅርቦ ነበር።
በወቅቱ መድረክ ላይ ሲወጣ ፊቱ ደም ያዘለ ይመስል የነበረ ሲሆን በሕዳር ወር ላይ ደግሞ ኤሪካ ሚውዚክ አዋርድ ላይ ፊቱን በፋሻ ጠቅልሎ ታይቷል።
እነዚህ የገጽ ቅቦች በአዲሱ ሙዚቃው ላይ "ከጠጡ አይንዱ" ለሚለው መልዕክት ታስበው የተሰሩ መሆናቸው ተነግሯል።
የግራሚ እጩዎች ይፋ በተደረጉበት ወቅት አቤል ተስፋዬ አዘጋጆቹን "ሙሰኞች" ሲል ከሷቸው ነበር።
ድምጻዊው ይህንን ያለው በተለቀቀ በሰዓታት ውስጥ ቁጥር አንድ የነበረውን የሙዚቃ ስራውን እንዲሁም ብላይንዲንግ ላይትስ የተሰኘ ክፍተኛ ተቀባይነት ያገኘ ነጠላ ዜማውን በመጥቀስ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የግራሚ ሽልማት አዘጋጆች ግን ድምጻዊው ቅር በመሰኘቱ "እንዳዝኑ" ገልፀው በየዓመቱ ግን "የሚገባቸው" ድምጻዊያን እንደሚዘለሉ ተናግረዋል።
በ2021 ቢዮንሴ በዘጠኝ፣ ቴይለር ስዊፍት እና ዱዋ ሊፓ እያንዳንዳቸው በስድስት ሽልማቶች በመታጨት ግንባር ቀደም ድምጻውያን ነበሩ።
ግራሚ አለመታጨቱ ስላሳደረበት ስሜት የተጠየቀው ድምጻዊው ለቢልቦርድ ሲመልስ "እጢዬ ዱብ ነው ያለው ብል ደስ ይለኛል። ምክንያቱም ከየት መጣ ሳልለው ነው ጭው የሚል ስሜት የተሰማኝ። በትክክል ተሰምቶኛል. . . ይሰማኛል። ሐዘን ይሁን ንዴት ግን አላውቀውም። ሲመስለኝ ግን ግራ መጋባት ነው። መልስ ማግኘት እፈልጋለሁ።
"ምንድን ነው የሆነው? ሁሉንም ነገር በትክክል የሰራነው ይመስለኛል። ጋጠ ወጥ አይደለሁም። ሰዎች እንደምታጭ ነግረውኝ ነበር። ዓለም የነገረኝ እንደዚያ ነው። ይህ ያንተ ዓመት ነው ዓይነት. . .ሁላችንም በጣም ነው ግራ የተጋባነው።"
በተጨማሪም "ግራሚ ዘረኛ ነው ብላችሁ ከጠየቃችሁኝ ትክክለኛው መልስ የሚሆነው ባለፉት 61 ዓመታት የዓመቱ ምርጥ አልበም ያሸነፉ ጥቁር አርቲስቶች 10 ብቻ ናቸው" ብሏል። "ጉዳዩን የኔ ብቻ ማድረግ አልፈልግም፤ ሃቁ ይህ ነው" ሲል አክሏል።
አልበሙ በአሜሪካ በሰዓታት ውስጥ በዓመት ውስጥ በከፍተኛ ቁጥር የተሸጠ አራተኛ አልበም ተብሎ የተመዘገበ ሲሆን፤ ብላይንዲንግ ላይትስ የተሰኘው ነጠላ ዜማው ደግሞ በአሜሪካ ታሪክ ምርጥ አስር ውስጥ ስሙ በደማቅ የተጻፈ ስራው ነው።
እንደ ሰር ኤልተን ጆን ያሉ ታላላቅ ድምጻውያን በዘ ዌኬንድ ሃሳብ ተስማምተው ሃሳባቸውን በማህበራዊ ሚዲያ ላይ አጋርተዋል።












