በባሌ ዞን በቁጥጥር ስር የዋለው 'ኢስላሚክ ስቴት ሴንተር' ታጣቂ ቡድን ማን ነው?

የፎቶው ባለመብት, EBC screen capture
በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን ዳሎ መና ወረዳ ከአልሸባብና አይኤስ ቡድኖች ጋር ትስስር አለው የተባለ እና ራሱን 'ኢስላሚክ ስቴት ሴንተር' ብሎ የሚጠራ ቡድን በቁጥጥር ሥር መዋሉን ቢቢሲ ያነጋገራቸው በኦሮሚያ የአስተዳደርና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጂብሪል አህመድ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
ይህ ቡድን መርሆውና አስተምህሮው ከአይኤስ ጋር አንድ መሆኑን የሚናገሩት ቢቢሲ ያነጋገራቸው የወረዳው መጅሊስ ኃላፊ ሼህ ሁሴን አሊ በአካባቢው ለረዥም ጊዜ ሲንቀሳቀስ መቆየቱን ለቢቢሲ ገልፀዋል።
ቡድኑ አንድ እስላማዊ መንግሥት በአንድ ኢምር ስር ሆኖ መግዛት አለበት በሚል ዓላማ እንደሚንቀሳቀስም አቶ ጂብሪል አክለው ገልፀዋል።
በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ግለሰቦች መካከልም ወጣቶችና ሴቶች ይገኙበታል ሲሉ ተናግረዋል።
ይህ ቡድን ከኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች እንዲሁም ከሶማሊያ ክልል የተመለመሉ አባላት እንደሚገኙበትም ቢቢሲ ያነጋገራቸው እኚህ ኃላፊ አረጋግጠዋል።
መንግሥትን በኃይል ለመጣል እየተንቀሳቀሰ ነበር የተባለው ይህ ቡድን በአስተምህሮ ለመንግሥት ግብር መክፈል እንደማይገባ ሲያስተምር መቆየቱም ተገልጿል።
አቶ ጂብሪል እንዳሉት፤ ይህ ቡድን ሰዎችን በመመልመል፣ ገሚሱን ሥልጠና አስገብቶ ሌሎቹን ደግሞ ለሥልጠና እያዘጋጀ በነበረበት ወቅት በፀጥታ አካላት ክትትል ቁጥጥር ሥር ውሏል።
በደሎ መና ነዋሪ የሆኑት አቶ ሡልጣን ቡድኑ "ካዋሪያ በማለት ራሱን ይጠራል" ሲሉ ይገልጹታል። ከቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አስተዳደር ጊዜ አንስቶ በአካባቢው እንቅስቃሴ ሲያደርጉ እንደነበርም ይናገራሉ።
የካዋሪያ ቡድን ማን ነው?
የደሎ መና ነዋሪ የሆኑት አቶ ሡልጣን ይህ ቡድን በወረዳቸው ውስጥ ለረዥም ጊዜ እንቅስቃሴ ሲያደርግ እንደነበር ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከሌሎች የእስልምና እምነት ተከታዮች ራሱን በመለየት "የአክራሪነት አመለካከት" ይዞ ሲንቀሳቀስ ነበር ይላሉ።
የቡድኑ አባላት ግማሾቹ ከሶማሌ፣ ከሐረር፣ ከወለጋ እና ከሌሎች ቦታዎች መምጣታቸውንም ለቢቢሲ አስረድተዋል።
"ከዚህም ብዙ ሰዎች እንደተቀላቀሏቸው አውቃለሁ። እያስተማሩ ወደ ራሳቸው ይጨምሩ ነበር። ከሙስሊሞች ጋራ አይዋደዱም። ይህ ቡድን ለረዥም ዓመት የእኛን እምነት ያጠፋ ነው። መንግሥትም ይቆጣጠርልን በማለት ሕዝቡ አቤቱታውን ሲያሰማ ነበር የቆየው።"
እንደ አቶ ሡልጣን ይህ ራሱን ካዋሪያ ብሎ የሚጠራው ቡድን በደሎ መና ወረዳ አዮዳ እና ሸዌ የሚባሉ ስፍራዎች ሠፍሮ ነበር።
"አሁን ደግሞ የጦር መሳሪያ በመያዝ ወደ ደጋው ገቡ። እዚያም ተጋጭተው አንድ ታጣቂ እንደሞተ አውቃለሁ፤ ሴቶችም በመካከላቸው ይገኛሉ። ከፀጥታ አካላት ጋር ተታኩሰው ገሚሶቹ ሲሸሹ ቀሪዎቹ ደግሞ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አውቃለሁ" ብለዋል።
ሼህ ሁሴን አሊ በደሎ መና ወረዳ ነዋሪና የወረዳው መጅሊስ ኃላፊ ሲሆኑ ስለዚህ ቡድን ሲናገሩ "በፊት ካዋሪያ በመባል ይታወቃሉ፤ አሁን ደግሞ እስላማዊ መንግሥት እናቋቁማለን ነው የሚሉት፤ ይህ ደግሞ ትክክለኛው እስልምና አይደለም። ከውጪ አካላት እንደ ዳዒሽ ካሉ ጋራ ግንኙነት እንዳለው እየሰማን ነው። ከመለስ ዜናዊ አስተዳደር ጀምሮ ነው ስለ እነዚህ ሰዎች አቤቱታ ስናሰማ የነበረው። ይኹን እንጂ በቁጥጥር ሥር ካዋሏቸው በኋላ ለቀቋቸው" ብለዋል።
"ግብር መክፈል ሃራም ነው"
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የወረዳው ነዋሪ አቶ ሡልጣን እንደሚሉት ቡድኑ "በካፊር መንግሥት አንተዳደርም። ቢቆይም ሥልጣን እንይዛለን ብለው ያምናሉ፤ አቋማቸውንም ሕዝቡ ያውቃል" ይላሉ።
"ለዚህ መንግሥት ግብር መክፈልን አይፈልጉም። ግብር ለፈጣሪ ብቻ ነው የሚከፈለው። የሚከፈል ግብር ሃራም ነው የሚሉ አካላት ናቸው። ከራሳቸው ተከታዮች ውጪ ሌሎች ሴቶች እንኳ አያገቡም" በማለት አቶ ሡልጣን ያብራራሉ።
ራሱን ካዋሪያ በማለት የሚጠራው ይህ ቡድን እስላማዊ መንግሥት እናቋቁማለን ከሚሉ ጋር ተመሳሳይ አቋም እንዳለው የደሎ መና መጅሊስ ኃላፊ ሼህ ሁሴን አሊ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
"በእኛ መስጂድ አይሰግዱም"
ሼህ ሁሴን የዚህ ቡድን ተከታዮች ሌሎች ሙስሊሞች በሚሰግዱበት መስጂድ ውስጥ እንደማይሰግዱ ይናገራሉ። ሶላታቸውም የተለየ ነው ብለዋል።
"ዋናው ዓላማቸው ሙስሊምም ሆነ ክርስቲያን ሃሳባቸውን የሚቃወም ከሆነ ገድሎ ማጥፋት ነው። ከምሽት ከ4 ሰዓት እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በአንድ ግለሰብ ቤት ውስጥ ተሰብስበው ከተወያዩ በኋላ ሳይነጋ እንደሚበተኑ ስንሰማ ቆይተናል። በኋላ ላይ ደግሞ የራሳቸው የሆነ እስላማዊ መንግሥት እናቋቁማለን፤ ለመንግሥት ቀረጥ አንከፍልም፤ አሁን ያሉት መስጂዶች እና ቤተ ክርስትያናት መቃጠል አለባቸው በማለት ሲንቀሳቀሱ ነበሩ" ይላሉ የመጅሊሱ ኃላፊ ሼህ ሁሴን።
የቡድኑ አባላት ናቸው የተባሉት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው በተዘገበበት ወቅት በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣብያው አህመድ ረሻድ የሚባሉ ግለሰብ የዚህ ቡድን አስተምህሮች ከአይኤስ ጋር ተመሰሳይነት ሊኖረው እንደሚችል ሲናገሩ ተደምጧል።
ሼህ ሁሴን በበኩላቸው እንደ ሙስሊም ማህበረሰብ ስለዘህ ቡድን ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ መሰራቱን ይናገራሉ።
"የእነርሱ አስተምህሮ ትልቅ ስህተት ይፈጥራል። ቅዱስ ቁርዓንን አዛብተው ነው የሚናገሩት። ስለዚህ በትክክል ቁርዓንን የማያውቁ ሰዎችን ሊያሳስቱ ይችላሉ" ብለዋል ሼህ ሁሴን።
የአካባቢው ነዋሪ የሆኑት አቶ ሡልጣን እንደሚሉት፤ ቡድኑ ሼህ እንዳለውና፣ ገርባ ሃሬ በሚባል ስፍራ ላይ እንደሚያስተምሯቸው ይናገራሉ።
መንግሥት ምን አለ?
የኦሮሚያ አስተዳደርና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጂብሪል አሕመድ "ይህ ቡድን ራሱን ለሽብር ሲያዘጋጅ ነበር። በተለያዩ ስፍራዎች ላይ ሰዎችን በማሰባሰብ አዲስ ኃይል ለማሰልጠን የሥልጠና ስፍራ አስገብቷል። ሥልጠናውም የትጥቅ ስልጠና ነው። እንዲሁም ሌሎቹ በዝግጅት ላይ ነበሩ። ቡድኑ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሰላም በማወክ ወደ አፍሪካ ቀንድ ለመሸጋገር ያለመ ይመስላል" ብለዋል።
አቶ ጂብሪል፤ ይህ ቡድን ዓላማዬ እስላማዊ መንግሥት መመስረት ነው ቢልም በሱማሊያ ከሚንቀሳቀሰው አልሸባብ ጋር ግንኙነት በመፍጠር የአገሪቱን ሰላም ማወክና የሽብር ተግባር መፈፀም አጀንዳው ነበር ሲሉ አክለዋል።
መንግሥት ይህን ይበል እንጂ ቢቢሲ ከተባለው ቡድን በዚህ ጉዳይ ላይ ያረጋገጠው ነገር የለም።
"የአል ሸባብን ተልዕኮ በመቀበል በአገሪቱ ውስጥ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ናቸው። በፀጥታ አካላት ላይ ተኩስ ከፍተው ነበር። በፀጥታ አካላትም ከዚህ ቡድን አባላት ሰዎች ተገድለዋል" ብለዋል አቶ ጂብሪል።
በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎች የውትድርና ሥልጠና መውሰዳቸውን ሲገልፁ፣ በተጨማሪም ለሥልጠና ተዘጋጅቶ የነበረው ሥፍራ ላይ በመድረስ ማፍረሳቸውን ተናግረዋል።
አሁንም የፀጥታ አካላት ቡድኑ ሲንቀሳቀስበት በነበረው ሥፍራ ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ አቶ ጂብሪል አክለው ተናግረዋል።
ይኹን እንጂ ይህ ቡድን በማን እንደሚመራ እና ታጥቀው ጫካ ውስጥ ይገኛሉ ከተባሉት በቁጥጥር ስር የዋሉት ምን ያህል እንደሆኑ በግልጽ የታወቀ ነገር የለም።












