ህወሓት በተከዜ ግድብ ላይ ጥቃት ተፈጽሟል ማለቱን ኤሌክትሪክ ኃይል ሐሰት ነው አለ

የፎቶው ባለመብት, @Ethioelectric
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በተከዜ የኃይል ማመንጫ ግድብን ላይ ጥቃት ተፈጽሟል በሚል ህወሓት ያቀረበውን ክስ ሐሰት ነው በማለት ውድቅ አደረገው።
የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ትናንት ማክሰኞ በትዊተር ገጻቸው የተከዜ የውሃ ኃይል ማመንጫ ግድብ መመታቱን ገልጸው ነበር።
አቶ ጌታቸው ረዳ ትናንት "ዛሬ ጠዋት [ኅዳር 21] የተከዜ የውሃ ኃይል ማመንጫ ተመቷል" ሲሉ ጽፈዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በበኩሉ አመሻሹ ላይ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ የተከዜ የውሃ ኃይል ማመንጫ ግድብ በመንግሥት ተመቷል በሚል "በህወሓት የሚናፈሰው ወሬ የሐሰት ነው" ብሏል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በምላሹ፤ "የኃይል ማመንጫ ጣቢያው ሙያተኛ ባልሆኑ ሰዎች ከታለመለት ዓላማ ውጪ እንዲሰራ ከተደረገ ከፍተኛ መጠን ያለው ጉዳት ሊደርስበት እንደሚችል ይታመናል" ሲል አስጠንቅቋል።
አያይዞም "ሕዝብን ለማሸበር እና ዓለም አቀፍ ትኩረትን ለመሳብ" በሚል ህወሓት ከግድቡ ውሃው ሊለቅ እንደሚችል ጠቁሞ በታችኛው ተፋሰስ የሚኖሩ ማኅበረሰቦች "ጥንቃቄ አድርጉ" ሲል አሳስቧል።
ግድቡ በሚገኝበትና በሌሎች ጦርነት በሚካሄድባቸው የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች የግንኙነት አገለግሎቶች በመቋረጣቸው ስላለው ሁኔታ ለማጣራት አዳጋች ሆኗል።
ይሁን እንጂ ህወሓት በግድቡ ላይ ጉዳት ስለመድረሱ ሲገልጽ የትናንቱ የመጀሪያው አይደለም። ከዚህ ቀደምም ግድቡ ላይ ጥቃት ተፈጽሟል በሚል ህወሓት ከሶ የነበረ ሲሆን የፌደራል መንግሥቱ በተመሳሳይ ሐሰት መሆኑን መግለጹ ይታወሳል።
አምና ለወራት ያህል ተቋርጦ የነበረው የተከዜ የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ መጋቢት ወር አካባቢ ሥራ መጀመሩን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ገልጾ ነበር።
የኃይል ማመንጫ ጣቢያው ከብሔራዊ የኃይል ቋት ጋር የሚገናኝበት መስመር በመቋረጡ ምክንያት ኃይል ማመንጨት አቁሞ ነበር።
በተከዜ ወንዝ ላይ የተገነባው የተከዜ የውሃ ኃይል ማመንጫ ግድብ 188 ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፤ ይህም በቁመት ከአፍሪካ ትልቁ እንደሚያደርገው ይነገርለታል።
የተከዜ የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በአራት ዩኒቶች 300 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅምም አለው።
በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት ኃይሎች መካከል በሚደረገው ጦርነት በሕዝብ አገለግሎትና በሌሎች መሠረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ውድመት መድረሱ ሲነገር ቆይቷል።
በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የጤና ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች፣ የመንግሥት ተቋማት እና ሌሎችም ላይ ውድመትና ጉዳት መድረሱ የተለያዩ ወገኖች ሪፖርት አድርገዋል።
አንድ ዓመት ያለፈው በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ውስጥ የተቀሰቀሰው ጦርነት በአሁኑ ጊዜ በአማራና በአፋር ክልሎች ውስጥ እየተካሄደ ሲሆን ከባድ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት ማድረሱ ይነገራል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ እንዳለው ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ ሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር 9.4 ሚሊዮን ደርሷል።












