ባሎንዶር፡ እውን ሜሲ የዘንድሮው ሽልማት አይገባውም?

ከግራ ወደ ቀኝ- ሮበርት ሌቫንዶቭስኪ፣ ሊዮኔል ሜሲ እና ሞሐመድ ሳላህ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ከግራ ወደ ቀኝ- ሮበርት ሌቫንዶቭስኪ፣ ሊዮኔል ሜሲ እና ሞሐመድ ሳላህ

የዘንድሮው የባሎን ዶር ሽልማት አከርካሪ ሆኗል።

ሽልማቱ ለፖላንዳዊው ሌቫንዶቭስኪ ነው የሚገባው ከሚለው ወቀሳ ጀምሮ ሞሐመድ ሳላህ ሰባተኛ መውጣቱ አግባብ አይደለም የሚሉ ደምፆች እየተሰሙ ነው።

አርጀንቲናዊው ሊዮኔል አንድሬስ ሜሲ ሽልማቱን ለሰባተኛ ጊዜ በማንሳት ታሪክ ፅፏል። ነገር ግን እንደዚህ ቀደሙ የይገባዋል ድምፅ ሳይሆን ሌቫንዶቭስኪ እያለ እንዴት በሚሉ ትችቶች የታጀበ ሆኗል።

እርግጥ ነው የ34 ዓመቱ ሜሲ ያሳለፈው የውድድር ዘመን የከፋ የሚባል አልነበረም። ሜሲ በ2021 40 ጎሎች አስቆጥሯል። 28 ለባርሴሎና፤ 4 ለፒኤስጂ እንዲሁም 8 ለሃገሩ አርጀንቲና።

ሜሲ በእግር ኳስ ሕይወቱ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር የመጀመሪያውን ዓለም አቀፍ ዋንጫ ያነሳው በዚህ ዓመት አርጀንቲና የኮፓ አሜሪካ ዋንጫ አሸናፊ ስትሆን ነው።

እና ለምን ሽልማቱ አይገባውም የሚሉ ድምፆች በረከቱ?

በርካታ የእግር ኳስ ተንታኞች የባየር ሚዩኒክና ፖላንድ የፊት መስመር ተጫዋች የሆነው ሮበርት ሌቫንዶቭስኪ የዘንድሮው ባለን ዶር ሽልማት አሸናፊ ሊሆን በተገባ ነበር ይላሉ።

የ33 ዓመቱ አጥቂ ዘንድሮ ለባየርን በሁሉም ውድድሮች 53 ጎሎች በማስቆጠሩ የዓመቱ ምርጥ አጥቂ የተሰኘ ሽልማት ተበርክቶለታል።

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተሰረዘው የባለፈው ዓመት የባለን ዶር ሽልማት ተዘጋጅቶ ቢሆን ኖሮ አሸናፊው ሌቫንዶስኪ እንጂ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም የሚሉ ብዙዎች ናቸው።

ሌቫንዶቭስኪ ከባየርን ጋር ባለፈው ዓመት የጀርመን ዋንጫ፣ ቡንደስሊጋ እንዲሁም ቻምፒዮንስ ሊግ ማንሳት ችሏል።

በ2021 ባየርን ቡንደስሊጋ ለዘጠነኛ ተከታታይ ጊዜ ሲያነሳ ሌቪ በቡንደስሊጋው በአንድ የውድድር ዘመን በርካታ ጎሎች በማግባት በ41 ጎሎች የገርድ ሙለርን ክብረ ወሰን መስበር ችሎ ነበር።

እግር ኳስ ተጨዋቾች፣ አሠልጣኞች እንዲሁም ተንታኞች ትላንት አመሻሹን ከተከናወነው የባለን ዶር ሽልማት በኋላ ሐሳባቸውን ሰጥተዋል።

የሪያል ማድሪዱ አማካይ ቶኒ ክሩስ "ሜሲ ሽልማቱ በጭራሽ አይገባውም" ብሏል። ሜሲና ሮናልዶ ያለፈውን 10 ዓመት በበላይነት መያዛቸው የማያከራክር ቢሆንም ዘንድሮ ግን ሽልማቱ የሚገባው ለሌላ ሰው ነበር።

ሌላው ቀርቶ ሜሲ እንኳ ሳይቀር ሽልማቱን ሲቀበል ሌቪ ባለን ዶር ይገባው እንደነበር ተናግሯል።

በሌላ በኩል የወቅቱ የዓለማችን ድንቅ ተጫዋች እየተባለ እየተሞካሸ ያለው ግብፃዊው የሊቨርፑል አጥቂ ሞ ሳላህ ሰባተኛ መውጣቱ ብዙዎችን አስከፍቷል።

የሊቨርፑል አሠልጣኝ ዩርገን ክሎፕ ሞ ሳላህ የተሻለ ድምፅ ማግኘት በተገባ ነበር ሲሉ ማክሰኞ ዕለት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ክሎፕ አክለው ሜሲ የሕይወት ዘመን ሽልማት ቢሆን ኖሮ ወርቃማው ኳስ ይገባው ነበር ሲሉ የሽልማቱን አዘጋጆች ሸንቆጥ አድርገዋል።