የዩናይትድ ኪንግደም የስለላ ኃላፊ ቻይና ዘርግታዋለች ስላሉት 'የዕዳና የመረጃ ወጥመድ' አስጠነቀቁ

ሪቻርድ ሞር

የዩናይትድ ኪንግደም የስለላ ተቋም ኤምአይ6 ኃላፊ ሪቻርድ ሙር ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረጉት የቀጥታ ስርጭት ቃለ መጠይቅ የቻይናን "የዕዳ እና መረጃ ወጥመድ" ሥርዓትን ተቹ።

'ሲ' በሚል ቅጽል ስም የሚታወቁት ኃላፊው ከቢቢሲ ራዲዮ 4 ጋር በነበራቸው ቆይታ እነዚህ ወጥመዶች የአገራትን ሉአላዊነት አደጋ ላይ የሚጥሉ መሆናቸውን በመግለጽ የጥንቃቄ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት አሳስበዋል።

ኃላፊው ከዚህ በተጨማሪም በአፍጋኒስታን የወታደራዊ መረጃ ልውውጥ ሥርዓቱ ደካማ በመሆኑ ምክንያት ካቡል በታሊባን ቁጥጥር ስር ሆናለች የሚለውን ሀሳብን ውድቅ አድርገውታል። እንዲያውም ከትልልቅ የቴክኖሎጂ ተቋማት ጋር በቅርበት እየሰሩ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የቀድሞው ሰላይ የአሁኑ የስለላ ክፍል ኃላፊ በይፋ ወጥቶ መናገር በዘመናዊው ዴሞክራሲ በጣም አስፈላጊ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

በርካታ ጉዳዮችን በዳሰሰው የመጀመሪያ ቃለ መጠይቅ የኤምአይ6 ኃላፊው ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል፡

• ቻይና ከመላው ዓለም መረጃ ለመሰብሰብ አቅሙ እንዳላት በመግለጽ ሰዎችን በቁጥጥሯ ስር ለማድረግ ደግሞ ገንዘብን ትጠቀማለች ሲሉ አሳስበዋል።

• በአፍጋኒስታን የታሊባንን ግስጋሴ በትክክል መገመት አለመቻላቸውን አምነው ነገር ግን ካቡል በታሊባን እጅ የወደቀችው በወታደራዊ መረጃ ልውውጥ ክፍተት ነው የሚለውን አጣጥለዋል።

• በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል ያለውን አሳሳቢ ችግርም የቃኙ ሲሆን ሩሲያ ለዩናይትድ ኪንግደም ትልቅ ስጋት መሆኗንም ገልጸዋል።

ኃላፊው ቻይና አገራቸው ላይ ስለምትፈጥረው ስጋት ሲናገሩ ቻይና የእዳ ወጥመድ እና የመረጃ ወጥመድ እንደምትጠቀም አብራርተዋል።

"ቤይጂንግ የኢኮኖሚ ፖሊሲዋን በመጠቀም በርካቶች ላይ ጫና ለማሳደር ትጥራለች፤ አንዳንዴም ሰዎችን በገንዘብ ወጥመድ ውስጥ እንዲገቡ ታደርጋለች" ብለዋል።

ስለ መረጃ ወጥመዱ ሲያብራሩ ኃላፊው "አንዳንድ አገራት ስለሌሎች አገራት በጣም ወሳኝ የሆኑ መረጃዎችን እንዲሰበስቡና ስለኅህበረሰቡ እንዲያሳውቁ ከተፈቀደላቸው የአገራት ሉአላዊነት ጥያቄ ውስጥ ይገባል" ብለዋል።

አክለውም "ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ መሰል ነገሮችን ቀድመመን ለመከላከልና ለማስቀረት ተገቢውን እርምጃ እንደወሰድን አምናለሁ" ብለዋል።

በሌላ በኩል የእንግሊዝ እና የአሜሪካ ወታደሮች ከአፍጋኒስታን ለቀው የወጡበት ፍጥነትና ነገሮችን የተረዱበት መንገድ ስህተት እንደነበረ ያመኑ ሲሆን፣ የትኛውም ወገን ታሊባን በዚህ ፍጥነት ይንቀሳቀሳል ብሎ እንዳልጠበቀ ገልጸዋል።

የታሊባን ድል ያልተጠበቀና የተገላቢጦሽ እንደሆነ ያመኑት ኃላፊው፣ በሌላ በኩል በቤይጂንግ፣ ሞስኮ እና ቴህራን ለተቀመጡ አክራሪዎች ትልቅ የሞራል ግንባታ እንደሚሆን አምናለሁ ብለዋል።