የትዊተር ሥራ አስፈጻሚ ጃክ ዶርሲ ከኃላፊነቱ ለቀቀ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የትዊተር አንዱ መስራች ጃክ ዶርሲ ከኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚነት ኃላፊነቱ ለቀቀ።
በአሁኑ ወቅትም በድርጅቱ ዋና የቴክኒክ ኃላፊ ፓራግ አግራዋል እንደሚተካም ትዊተር አስታውቋል።
ዶርሲ ታዋቂ ከሆኑትና በርካታ ተጠቃሚ ካላቸው የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች አንዱ የሆነውን ትዊተርን ከ15 ዓመት በፊት የመሠረተ ሲሆን፣ የክፍያ አገልግሎት ተቋም የሆነውን 'ስኩዌር' እና የትዊተር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል።
"በመጨረሻም መልቀቅ ያለብኝ ጊዜ" ነው በማለት በመግለጫው ያተተው ጃክ ዶርሲ ኩባንያው ያለሱም "ለመቀጠል ዝግጁ ነው" ብሏል።
የትዊተር ስራ አስፈፃሚ ሆኖ በተተካው ግለሰብ ላይም "ጥልቅ እምነት አለኝ" ሲል ተናግሯል። " ለችሎታው፣ ለቀናነቱና ላለው መልካም ልብ አመሰግናለሁ። ለሱ ለምምራት ጊዜው አሁን ነው" ብሏል።
ፓራግ አግራዋል ትዊተርን የተቀላቀለው በአውሮፓውያኑ 2011 ሲሆን ከ2017 ጀምሮ የድርጅቱ የቴክኖሎጂ ኃላፊ ሆኖ አገልግለዋል።
ጃክ ዶርሲ አፍንጫው ላይ በሚያደርገው ጌጥ፣ ረጅም ጢሙ እና ዮጋን ጨምሮ እና በቀን አንድ ምግብ ብቻ በመመገብ የታላላቅ ድርጅት አሰራሮችን ሞግተዋል።
ባለፈው የፈረንጆች ዓመት አንዳንድ ወገኖች ትኩረቱን በአንድ ተቋም ላይ ብቻ እንዲያደርግ በመጠየቅ ከኃላፊነቱ እንዲለቅ ግፊት ሲያደርጉበት ነበር።
የጃክ ዶርሲ ከኃላፊነቱ ሊለቅ መሆኑ ወሬ ከተሰማ በኋላ የትዊተር የአክሲዮን ድርሻ ዋጋ በተወሰነ መጠን ጨምሯል።
የ45 ዓመቱ ዶርሲ ትዊተርን ከቢዝ ስቶን፣ ኢቫን ዊሊያምስ እና ከኖህ ግላስ ጋር በመሆን ነበር ያቋቋመው።
ቢሆንም ግን የመጀመሪያዎቹን የትዊተር መልዕክቶችን በማስተላለፍና ለረጅም ዓመታት በዋና ሥራ አስፈጻሚነት በማገልገል ከኩባንያው ስም ጋር በቀዳሚነት የሚነሳው ጃክ ዶርሲ ነው።
ዶርሲ እንደ አውሮፓውያኑ 2008 ትዊተርን በመልቀቅ የዲጂታል ክፍያ መተግበሪያ የሆነውና ባለብዙ ቢሊዮን ዶላር ኩባንያ የሆነውን 'ስኩዌር'ን መስርቶ እየሰራ ነበር።
ነገር ግን ከሰባት ዓመት በኋላ የትዊተር ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበረው ዲክ ኮስቶሎ ሥራውን መልቀቁን ተከትሎ ወደ ትዊተር ተመልሷል።
ዶርሲ ኃላፊነቱን እንዲለቅና ትዊተር ሙሉ ጊዜውን በኩባንያው ሥራ ላይ ብቻ ያተኮረ ሥራ አስፈጻሚ እንዲኖረው ግፊት ሲደረግ ቆይቷል።
በትዊተር አመራር ላይ ከሚደረገው ለውጥ በተጨማሪ በኩባንያው ቦርድ ዙሪያ በርካታ ለውጦች የተደረጉ ሲሆን፣ የተለያዩ አዳዲስ ሹመቶችም እየታዩ ነው።
















