የትዊተር መሥራች እና ጄይ ዚ በአፍሪካ ቢትኮይን እንዲስፋፋ ገንዘባቸውን ፈሰስ አደረጉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የትዊተር መሥራቾች ከሆኑት መካከል አንዱ የሆነው ጃክ ዶርሲ እና ራፐር ጄይ ዚ በአፍሪካ እና በሕንድ ቢትኮይን እንዲስፋፋ ከፍተኛ ገንዘባቸውን ፈሰስ ማድረጋቸውን ገለፀ።
ዶርሲ እንዳለው 23.6 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ 500 ቢትኮይኖችን ቢትረስት (₿trust) ለተባለ ፈንድ መመስረቻነት ሰጥተዋል።
ኳርትዝ የተሰኘው ድረ ገጽ እንደዘገበው ከሆነ ባለፉቱ አምስት ዓመታት በቢትኮይን ገበያ ከአሜሪካ በመቀጠል ስሟ የሚነሳው አገር ናይጄሪያ ናት።
የአፍሪካ ትልልቅ ከተሞች ከሆኑት መካከል ጆሃንስበረግ፣ ሌጎስና ናይሮቢ የሚኖሩ ሰዎች ገንዘባቸውን ከአንድ አገር ወደ ሌላው ለማዘዋወር ቢትኮይንን እንደ ቀላል አማራጭ እንደሚወስዱት ቢቢሲ የሰራው ዘገባ ያሳያል።
ይኹን እንጂ የናይጄሪያ ማዕከላዊ ባንክ ጉዳዩ ስላሳሰበው ባለፈው ሳምንት በክሪፕቶከረንሲ ከሚገበያዩ ጋር ግንኙነት ያላቸው አካውንቶች በሙሉ እንዲዘጉ ወስኗል።
ባለፈው ሳምንት የኤለን መስክ የመኪና ኩባንያ ተስላ 1.5 ቢሊየን ዶላር የሚያወጣ ቢትኮይን በታህሳስ ወር መግዛቱን አስታወቆ ነበር።
ኩባንያው ገንዘቡን ወደፊት መቀበል እንደሚጀምርም ጨምሮ ይፋ አድርጓል።
ይህ ዜና እንደተሰማ የቢትኮይን ዋጋ በ 17 በመቶ ወደ 44 ሺህ 220 አሻቅቧል ተብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቢትኮይን ምንድነው?
ቢትኮይን ማለት በቀላል ቋንቋ፤ ዲጂታል ገንዘብ+መገበያያ በማለት ማጠቃለል ይቻላል።
ይህ መገበያያ በኪሳችን ተሸክመን እንደምንዞረው የብር ኖት ወይም ሳንቲም ሳይሆን 'ኦንላይን' የሚቀመጥ ዲጂታል ገንዘብ ነው።
ሌላው የቢትኮይንና የተቀሩት የክሪይፕቶከረንሲዎች ልዩ ባህሪ በመንግሥታት እና በባንኮች አለመታተማቸው እንዲሁም ቁጥጥር አለመደረጉ ነው። ቢትኮይን የሚፈጠረው 'ማይኒንግ' በሚባል ሂደት ነው። በመላው ዓለም በኔትወርክ በተሳሰሩ ኮምፒውተሮች ቁጥጥር ይደረግበታል።
ቢትኮይንን የፈጠረው ግለሰብ/ቡድን በዓለም ላይ 21 ሚሊዮን ቢትኮይኖች ብቻ እንዲፈጠሩ ገደብ እንዳስቀመጡ ይታመናል። የብሎክቼይን መረጃዎች እንደሚያሳዩት እስካሁን 17 ሚሊዮን ያህል ቢትኮይኖች ማይን ተደርገዋል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
ማይክሮሶፍት፣ የፈጣን ምግብ አቅራቢዎቹ ኬኤፍሲ እና ሰብዌይ፣ የጉዞ ወኪሉ ኤክስፔዲያን ከመሳሰሉ ባለብዙ ሚሊዮን ገንዘብ ኩባንያዎችን አንስቶ እስከ ሆቴሎች እና ካፊቴሪያዎች ቢትኮይንን በክፍያ መልክ ይቀበላሉ።
በቢትኮይን አማካኝነት ክፍያ ሲፈጸም የገዢውን ማንነት ይፋ አለማድረግ ያስችላል። ይህም በርካቶች በኢንተርኔት አማካኝነት ማንነታቸውን ሳይገልጡ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ስለሚያስችላቸው በቢትኮይን አማካኝነት የሚደረጉ የንግድ ልውውጦች ቁጥር እጅጉን ጨምሯል።
ቢትኮይን እንደስጋት?
አሸረትስ በተባለ የፋይናንስ ተቆጣጣሪ ኩባንያ ውስጥ ባለሙያ የሆኑት ብራደሊይ ራይስ በቢትኮይን ላይ ምንም አይነት ቁጥጥር እንደማይደረግበት ያስታውሳሉ።
ቢትኮይንን በመጠቀም የገዢው ማንነት ይፋ ሳይደረግ በየትኛውም ሰዓት እና በየትኛውም ስፍራ የቢትኮይን ዝውውር ማድረግ ይቻላል። የገዢው ማንነት ይፋ ሳይደረግ ግብይት መፈጸም ይቻላል።
በዚህም ሕገ ወጥ ቡድኖች የጦር መሳሪያዎች እና እጾችን ሊገዙ እና ሊሽጡ ይቻላሉ፣ ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር እና አሸባሪዎችን ለመደገፍ ያስችላል በማለት ቢትኮይንን ጨምሮ ሌሎች ክሪይፕቶከረንሲዎች ላይ ያላቸውን ስጋት የሚያነሱ በርካቶች ናቸው።
በሌላ በኩል በርካታ የፋይናንስ ባለሙያዎች ቢትኮይን ላይ ምንም አይነት ቁጥጥር አለመደረጉ ተፈላጊነቱን እንደጨመረው ያወሳሉ።












