የትዊተሩ ጃክ ዶርሲ ለችግረኞች መደገፊያ የሚሆን 3 ሚሊዮን ዶላር ለገሠ

ጃክ ዶርሲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የትዊተር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጃክ ዶርሲ መሠረታዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት የሚያስፈልግ ገቢ ለችግረኞች ለመስጠት የሚያስችል ዕቅድ አውጥቶ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ የመጀመሪያው ባለሐብት ሆነ።

የተለየ ነው በተባለው በዚህ ዕቅድ ገንዘቡ የሚሰጣቸው ሰዎች ሥራ ይኑራቸው አይኑራቸው ከግምት ውስጥ የሚገባ እንዳልሆነ የተነገረ ሲሆን ለዚህም ጃክ ዶርሲ 3 ሚሊዮን ዶላር ለግሷል።

ይህ የችግረኞችን መሠረታዊ ገቢ የሚያሟላው ዕቅድ በ16 የአሜሪካ ከተሞች ከንቲባዎች አማካይነት የሙከራ ሥራው ተጀምሯል።

ዶርሲ ይህ ዕቅዱ "በሰዎች መካከል ያለውን የሐብትና የገቢ ክፍተት ለማጥበብ አንድ መሣሪያ ነው" ብሎታል።

ይህ በጃክ ዶርሲ የታቀደው የመሠረታዊ ገቢ ክፍያ ለእነማን እንደሚሰጥ በግልጽ ባይቀመጥም፤ ነገር ግን በተለይ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጫናን በፈጠረበት በዚህ ወቅት የሚያጋትምን ድህነት ለመቋቋም ለተቸገሩ አሜሪካዊያን የታሰበ መሆኑን በድረ ገጹ ላይ አመልክቷል።

በዚህ ዕቅድ መሰረት ስለሚሰጠው የገንዘብ መጠንና ይህ የመሠረታዊ ገቢ ድጋፍ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚዘልቅ አልተገለጸም።

ዶርሲ በትዊተር ገጹ ላይ እንዳሰፈረው "ይህ ዕቅድ የሀብትና የገቢ ልዩነትን ለማቀራረብ አንድ መንገድ ሲሆን፤ ሥርዓታዊ የሆነውን የዘርና የጾታ ልዩነትን በማስተካከል ለቤተሰቦች የገቢ ዋስትናን መፍጠር ነው" ሲል አላማውን ገልጿል።

ይህ ፕሮጀክት የስቶክተን ከተማ ከንቲባ በሆኑት ማይክል ቱብስ ታስቦ ከከተማው ባሻገር በአገር አቀፍ ደረጃና ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኋላም እንዲቀጥል ታስቦ የተጀመረ ነው።

አስፈላጊውን ገንዘብም ለማግኘት አንዱ መንገድ ጃክ ዶርሲን በመሳሰሉ ባለሐብቶች ላይ የግብር ጭማሪ በማድረግ ለማሟላት የታሰበ ነው።

እጅግ የረቀቀው ቴክኖሎጂ በርካታ ሥራዎችን በማስቀረት የበርካታ ሰዎች ገቢ ላይ ችግር በመፍጠሩ መንግሥታት መሠረታዊ ገቢን ለዜጎቻቸው መስጠትን የተመለከተው ሃሳብ መነጋገሪያ እየሆነ ነው።

ሁሉን አቀፍ መሠረታዊ ገቢ በመደበኛነት መንግሥታት ለዜጎቻቸው የሚፈጽሙት ክፍያ ነው። ይህም መስራት መቻልም ሆነ ሌላ መመዘኛ ሳይቀመጥለት የሚሰጥ ገንዘብ ሲሆን ሁሉም ዜጋ የሐብት መጠንን ወይም የሥራ ሁኔታን ከግምት ሳያስገባ የሚያገኘው ገቢ ነው።