ቻይና ጋዜጠኞችን ለመከታተል የ'ትራፊክ መብራት' ስርዓትን ልትጠቀም ነው

የቻይናዋ ግዛት ሄናን ጋዜጠኞችን እና ሌሎች "አስጊ ሰዎችን" ፊት መለየት የሚያስችል የቴክኖሎጂ ሥርዓት እያበለጸገች መሆኑ ተሰማ።
ይህ ሥርዓት በትራፊክ መብራት ቀለማት ተመስሏል።
በቢቢሲ እጅ የገቡ ሰነዶች እንዳመለከቱት ሥርዓቱ ጋዜጠኞችን በትራፊክ መብራት ቀለሞች ዓይነት የሚከፋፍል ሲሆን በሄነን ግዛት ያለ ጋዜጠኛ በአረንጓዴ፣ በብርቱካናማ ወይም በቀይ ቀለም ተለይቶ በደረጃ ይመደባል።
የሄናን የሕዝብ ደህንነት ቢሮ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ ቢጠየቅም ምላሽ አልሰጠም።
የደህንነት ክትትል ተንታኙ አይ ፒ ቪ ኤም አማካኝነት ሾልኮ የወጣው ይህ ሰነድ የውጭ ተማሪዎችን እና ሴት ስደተኞችን ጨምሮ ሌሎች "አስጊ ሰዎችን" የመከታተል እቅድን ይዘረዝራል።
ሂዩማን ራይትስ ዎች "ይህ ብዙ ሰዎችን ለመከታተል የበለጠ ሥልጣን የሚፈልግ መንግሥት አይደለም...በተለይ በሰላማዊ መንገድ ተጠያቂ ለማድረግ የሚሞክሩትን" ብሏል።
በዚህ ሥርዓት አማካኝነት የሄናን የሕዝብ ደህንነት ቢሮ ክትትል ከሚያደርግባቸው ቡድኖች አንዱ የውጭዎችን ጨምሮ ጋዜጠኞች ላይ ናቸው።
ሰነዱ ቀዳሚው ሀሳብ ዋና ዋና ጋዜጠኞችን በሦስት ደረጃዎች መከፋፈል ነው ይላል።
በዚህም መሠረት "በቀይ ምልክት የተደረገባቸው ሰዎች ቁልፍ ስጋት ናቸው። ሁለተኛው ደረጃ በቢጫ ምልክት የተደረገባቸው ሲሆን በጥቅሉ አስጊ ሰዎች ናቸው። ደረጃ ሦስት በአረንጓዴ ምልክት የተደረገበት ጎጂ ላልሆኑ ጋዜጠኞች ነው" ሲል ያትታል።
"አስጊ ጋዜጠኞች" "ቀይ" ወይም "ቢጫ" የሚል የሚመደቡ ከሆነ እና ከዚህ ቀደም የወንጀል ክስ ከነበራቸው ወደ ግዛቷ ለመጓዝ ትኬት እንዳይቆርጡ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል።
በተጨማሪም ሥርዓቱ የውጭ ተማሪዎችን በመገምገም በሦስት ምድቦች ይከፍላቸዋል "እጅግ ጥሩ የውጭ ተማሪዎች፣ መደበኛ ተማሪዎች እና ቁልፍ እና ያልተረጋጉ" በሚል ይከፋፍላቸዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ ሐምሌ ወር ማብቂያ ላይ ይፋ የሆኑት ሰነዶች የቻይና ኩባንያዎች አዲሱን ሥርዓት ለመገንባት እንዲወዳደሩ የሚያበረታታ የጨረታ ሂደት አካል ሲሆኑ በመስከረም 17 'ኒዎ ሶፍ' የተባለ ኩባንያ አሸንፏል።
ይህን ሥርዓት ይገነባዋል የተባለው 'ኒዎ ሶፍ' አስተያየት እንዲሰጥ ከቢቢሲ ጥያቄ ቀርቦለት ምላሽ አልሰጠም።
ሥርዓቱ በሄናን ውስጥ ከሚገኙ በሺዎች ከሚቆጠሩ ካሜራዎች ጋር የተገናኘ የሰው ፊት መለያ ቴክኖሎጂን የሚያካትት ሲሆን "አስጊ ሰው" ሲገኝ ለግዛቷ ባለሥልጣናትን ያሳውቃል።
"አስጊ ሰዎች" ዝርዝር ተልከው ቀድሞውኑ ካለው የመረጃ ቋት እና በግዛቱ ውስጥ ያሉ ሰዎች ምሥሎች ጋር የሚመሳከር ሲሆን ሥርዓቱ ከቻይና ብሔራዊ የመረጃ ቋት ጋርም ይገናኛል።
"የደህንነት ክትትሉ የሚደረገው በውጭ አገር ተማሪዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ፣ የፈተና ውጤት እና ከኃያላን አገራት የመጡ ከሆኑ እንዲሁም የትምህርት ቤት ሥነ ምግባራቸው ላይ በማተኮር ነው" ሲል ሰነዱ ያትታል።
ትምህርት ቤቶቹ ራሳቸው ለደህንነት አስጊ የሆኑ ተማሪዎችን ለግዛቷ ባለሥልጣናት ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል።
በዚህ መሰረት አስጊ ናቸው የተባሉት ክትትል የሚደረግባቸው ይሆናል።
በፖለቲካዊ ዐይን ልዩ ትኩረት የሚሰጣቸው እንደ ብሔራዊ ሕዝባዊ ኮንግረስ ዓመታዊ ስብሰባ ያሉ ጊዜያት ሲመጡ "የጦርነት ጊዜ ማስጠንቀቂያ ዘዴ" እንዲተገበር ይደረጋል የሚለው ሰነዱ፤ የተዘረዘሩትን ሰዎች የሞባይል ስልኮቻቸውን መከታተልን እና "ዋነኛ አስጊ" ተማሪዎችን መከታተል ይጨምራል ሲል ያብራራል።
ከስልኮች፣ እንደ 'ዊ ቻት'እና 'ዊቦ' ያሉ ማሕበራዊ ሚዲያ፣ የተሽከርካሪ መረጃ፣ በሆቴል የሚኖሩ ቆይታዎች፣ የጉዞ ትኬቶች፣ የንብረት ባለቤትነት እና ከነባር ዳታዎች የሚወሰዱ ፎቶዎች ሥርዓቱ ክትትል እንደሚያደረግ በሰነዱ ተጠቅሷል።
በሌላ በኩል በቻይና ውስጥ የመኖሪያ ፍቃድ በሌላቸው "በተሰደዱ ሴቶች" ወይም ቻይናዊ ያልሆኑ ስደተኛ ሴቶች ላይ ማተኮር እንደሚገባ ሰነዱ ላይ ሰፍሯል።
ብዙ ቁጥር ያላቸው ሴቶች ሥራ ለማግኘት ወደ ቻይና የሚገቡ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ከጎረቤት አገራት ተዘዋውረዋል።
በመሆኑም ሥርዓቱ ከብሔራዊ ኢሚግሬሽን ቢሮ፣ ከሕዝባዊ ደህንነት ሚኒስቴር እና ከሄናን ፖሊስ እና ከሌሎች ጋር መረጃዎቹን ለማስተሳሰር ይጠቅማል።
ሰነዶቹ ይፋ የሆኑት የቻይና መንግሥት በሄናንን ጎርፍ ዙሪያ የውጪ መገናኛ ብዙኃንን እየተቸ ባለበት ወቅት ነው።
ሰነዱ እንዲሾልክ ምክንያት የሆነው አይ ፒ ቪ ኤም ዳይሬክተር ኮኖር ሄሊ "በቻይና ያለው የጅምላ ክትትል ቴክኒካዊ ጉዳዮችን በሚገባ አልተረዳም...ነገር ግን የመንግሥት ጋዜጠኞችን አፈና ለማቀላጠፍ የተዘረጋው ቴክኖሎጂ አዲስ ነው" ብለዋል።
"እነዚህ ሰነዶች የቻይና የሕዝብ-ደህንነት ባለሥልጣናት ከጅምላ ክትትል ምን እንደሚፈልጉ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው" ሲሉም አክለዋል።
የቻይና ሰዎችን በፊትን የመለየት የቴክኖሎጂ ዘዴ በመላ አገሪቱ ጥቅም ላይ የዋለ ነው ተብሎ ይታሰባል።
ባለፈው ዓመት ዋሽንግተን ፖስት ሁዋዌ የኡጉር አናሳ ጎሳ አባላት የሆኑትን ሰዎች ለይቶ ማወቅ እና ፖሊስን ሊያስጠነቅቅ የሚችል ሰው ሰራሽ ልህቀት [አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ] ሶፍትዌር መሞከሩን ተዘግቧል።
የሂዩማን ራይትስ ዎች ቻይና ዳይሬክተር ሶፊ ሪቻርድሰን "ዓላማው ማቀዛቀዝ ነው። ሁሉም ሰው ክትትል እንደሚደረግበት እንዲያውቅ እና በጥላቻ መነሻ ምን እንደሚፈጥር ፈጽሞ እንዳያውቁ" ነው ሲሉ ገልጸዋል።












