የለንደኑ ነዋሪ የመጀመሪያው በ3ዲ የታተመ ሰው ሰራሽ ዓይን ሊተከልለት ነው

የፎቶው ባለመብት, MOORFIELDS EYE HOSPITAL
የለንደን ከተማ ነዋሪ የሆነው ግለሰብ በ3ዲ የታተመ ሰው ሰራሽ ዓይን ለመጀመሪያው ጊዜ ሊተከልለት ነው።
ስቲቭ ቬርዜ ለንደን ከተማ በሚገኘው የሞርፊልድ የዓይን ሆስፒታል በ3ዲ ቴክኖሎጂ የታተመው ዓይን ይተከልለታል።
አዲሱ ዓይን ከዚህ ቀደም ከነበረው ሰው ሰራሽ ዓይን የበለጠ ተፈጥሯዊ እንደሚመስል ተስፋ ተደርጓል።
በተጨማሪም ከዚህ ቀደም ለታካሚዎች ሰው ሰራሽ ዓይን ለመግጠም ይፈጅ የነበረውን የስድስት ሳምንታት ጊዜ የ3ዲ ቴክኖሎጂው በግማሽ ይቀንሳዋል ተብሏል።
ምንም እንኳ ይህ ሰው ሰራሽ ዓይን የማየት ችሎታን ባይመልስም የተፈጥሮ ዓይን ስለሚመስል የሰዎችን በራስ መተማመን ከፍ ያደርጋል ተብሏል።
ዕድሜ በ40ዎቹ ውስጥ የሚገኘው ቬርዜ "ከ20 ዓመቴ ጀምሮ ሰው ሰራሽ ዓይን ያስፈልገኝ ነበር። . . . ከቤቴ ስወጣ በመስታወት ውስጥ ዓይኔን እመለከታለሁ። እናም የማየው አያስደስተኝም" ብሏል።
"አዲሱ ዓይን ድንቅ ይመስላል። በ3ዲ ዲጂታል ማተሚያ ቴክኖሎጂ በመሠራቱ የተሻለ ይሆናል" ብሏል።
ለአንድ ግለሰብ ሰው ሰራሽ ዓይን ከመተከሉ በፊት በዓይኑ ልክ ሰው ሰራሸ አይኑ መቀረጽ ይኖርበታል።
በ3ዲ የታተመ ሰው ሠራሽ ዓይን የማምረት ሂደትን ከሁለት እስከ ሦስት ሳምንታት ይቀንሳል። የመጀመሪያ ቀጠሮው ግማሽ ሰዓት ብቻ እንደሚወስድም ተገልጿል።
በሞርፊልድስ የዓይን ሆስፒታል የዓይን ሕክምና አማካሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ማንዲፕ ሳጎ ሙሉ በሙሉ ዲጂታል በሆነው የሰው ሰራሽ ዓይን በማግኘታቸው ባልደረቦቻቸው "ደስተኛ" ነበሩ ብለዋል።
"መጪው ሙከራ የዚህን አዲስ ቴክኖሎጂ ጥቅም በተመለከተ ጠንካራ ማስረጃዎችን እንደሚሰጠን ተስፋ እናደርጋለን። ለታካሚዎች ምን ያህል ልዩነት እንዳለው ያሳያል" ብለዋል።












