ባርቤዶስ ከዩናይትድ ኪንግደም ዘውዳዊ ሥርዓት ወጥታ ሪፓብሊክ ሆነች

የሚጨፍሩ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ባርቤዶስ ንግሥት ኤልሳቤት ሁለተኛን ከርዕሰ ብሔርነት አንስታ ሪፓብሊክ አገር ሆነች።

የዌልሱ ልዑል ቻርልስ እና የባርቤዶስ ዜጋ የሆነችው ዝነኛዋ አቀንቃኝ ሪሃና በታደሙበት ስነ-ስርዓት ዳሜ ሳንድራ ሜሰን የባርቤዶስ ፕሬዝደንት ሆነው ቃለ መሃላ ፈጽመዋል።

ልዑል ቻርልስ በንግግራቸው በካረቢያኗ ደሴት በባርነት ስርዓት ውስጥ ግፍ መፈጸሙ እሙን ነው ብለዋል። ልዑሉ የክብር እንግዳ ሆነው በተገኙበት መድረክ ምንም እንኳ ባርቤዶስ ሕገ-መንግሥታዊ ለውጥ ብታደርግም የሁለቱ አገራት ወዳጅነት ይቀጥላል ብለዋል።

ንግስሥቷ ለባርቤዶስ "ወደ ፊት ደስታ፣ ሰላም እና ብልጽግና እንዲሆን መልካም ምኞት" ልከዋል ብለዋል ልዑል ቻርልስ።

ባርቤዶስ የእንግሊዟን ንግሥት ከርዕሰ ብሔርነት አንሳታ ሪፓብሊክ መሆኗ በአገሪቱ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ ሆኖ ተመዝግቧል።

የ72 ዓመቷ ዳሜ ሳንድራ ሜሰን ባለፈው ወር በአገሪቱ ፓርላማ ተመራጭ ፕሬዝደንት ሆነው ተመርጠው ነው። ፕሬዝደንቷ የባርቤዶስ ርዕሰ ብሔር በመሆን ንግሥት ኤልሳቤት ሁለተኛን ይተካሉ።

ባርቤዶስ በኮመን ዌልዝ አገራት ውስጥ ሆና ሪፓብሊክ የመሆን ውጥን እንዳላት ያስታወቀችው ባለፈው ዓመት ነበር።

ዳሜ ሳንድራ ሜሰን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዳሜ ሳንድራ ሜሰን

ባርቤዶስ ከቀደምት የእንግሊዝ በባርነት ከተገዙ ቅኝ ግዛቶች መካከል አንዷ ነች። የእንግሊዝ ሰፋሪዎች እአአ 1672 ላይ በደሴቲቷ ላይ የሰፈሩ ሲሆን፤ ባርቤዶስ በብሪታኒያ ቅኝ በተገዛች ወቅት ከአፍሪካ የመጡ ሰዎች የሸንኮራ ልማት የሚያከናውኑባት ደሴት ሆና ቆይታለች።

በባርቤዶስ የባሪያ ስርዓት እአአ 1834 እንዲቆም የተደረገ ሲሆን ደሴቲቱ እአአ 1966 ላይ ደግሞ ነጻነቷን አውጃ ነበር።

ከባርቤዶስ በፊት ለመጨረሻ ጊዜ ንግሥት ኤልዛቤት ሁለተኛን ከርዕሰ ብሔርነት ያነሳች አገር ሞሪሺየስ ስትሆን ይህም እአአ 1992 ላይ ነበር።

ንግሥት ኤልሳቤት ሁለተኛ ከዩናይትድ ኪንግደም በተጨማሪ አውስትራሊያ፣ ካናዳ እና ኒው ዚላንድን ጨምሮ የ15 አገራት ርዕሰ ብሔር ናቸው።

285ሺህ ሕዝብ ብቻ ያላት ባርቤዶስ፤ በካረቢያን ከሚገኙ የበለጸጉ ደሴቶች መካከል አንዷ ነች።