በጋምቤላ የስደተኞች መጠለያ የሚፈተኑት ሴቶች እና ሕጻናት

ንያበል ጆክ

የፎቶው ባለመብት, UNFPA ETHIOPIA

የምስሉ መግለጫ, ናያቤል ጆክ በጋምቤላ ጀዊ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ በሚገኘው የጤና ተቋም የእርግዝና ክትትል ካደረገች በኋላ

የ19 ዓመቷ ደቡብ ሱዳናዊት ናያቤል ጆክ የምትኖረው ጋምቤላ በሚገኘው ጃዊ የስደተኞች መጠለያ ነው።

ነፍሰ ጡሯ ናያቤል ወርሃዊ የሕክምና ምርመራ ታደርጋለች። "ብቸኛው ደስታዬ ልጄ ነው። በሕይወቴ ሌላ ነገር የለኝም" ትላለች።

በደቡብ ሱዳን ከምትገኘው ናስር ወደ ኢትዮጵያ የተሰደደችው ከአምስት ዓመታት በፊት ነበር። እአአ በ2013 በተነሳው ግጭት ሳቢያ 1.5 ሚሊዮን ሰዎች ተፈናቅለዋል።

ናያቤል ወደ ኢትዮጵያ ስትገባ ከለበሰችው ልብስ ውጭ አንዳችም ንብረት አልነበራትም።

"አገሬን ትቼ የተሰደድኩት ከባድ ችግር ስለገጠመኝ ነው። እዚህ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ ያለው ሕይወትም አልጋ በአልጋ አይደለም" ትላለች።

"ምግብ፣ የግል ንጽህና መጠበቂያ ወይም ሌላም መሠረታዊ አቅርቦት ለማግኘት የእርዳታ ሰጪዎችን ድጎማ መጠበቅ አለብን" ስትል የመጠለያውን ኑሮ ትገልጻለች።

ጀዊ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ 61,971 ሰዎች ይኖራሉ። በመላው ጋምቤላ ክልል በሚገኙ ስምንት መጠለያዎች ያሉ ስደተኞች ቁጥር ወደ 349,542 ይጠጋል።

ባለፈው ዓመት ከደቡብ ሱዳን ወደ ጋምቤላ 11,000 ሰዎች ተሰደዋል። ከእነዚህ 55 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች እና ሕጻናት ናቸው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) እንዲሁም ሌሎችም የተራድኦ ድርጅቶች የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ይፋ የሚያደርገው ሪሊፍዌብ ድረ ገጽ እንዳስነበበው፤ ስደተኞቹ በምን መንገድ ሕይወታቸውን እንደሚገፉ የሚጠቁም የረዥም ጊዜ ዕቅድ የለም።

በቅርቡ ለስደተኞቹ የሚቀርበው የምግብ መጠን እንደሚቀንስ ተገልጿል። የስደተኞቹ እጣ ፈንታ ከቀን ወደ ቀን አስጨናቂ እየሆነም መጥቷል።

ናያቤል ወደ አገሯ መመለስ አትችልም። የኢትዮጵያ ቆይታዋም እያሳሰባት ነው። አንዳችም ገቢ ማግኛ መንገድ ስለሌላት ኑሮን በእርዳታ ምግብ ነው የምትገፋው።

የእናቶች እና ሕጻናት ሞት

ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚኖሩ ስደተኞች አብዛኞቹ የሚገኙት በጋምቤላ ክልል ነው። ለስደተኞቹ የሚያስፈልጉ መሠረታዊ አቅርቦቶች እየጨመሩ በመምጣታቸው የክልሉ የጤና እና ማኅበራዊ መዋቅር እየተንገዳገደ መሆኑን ሪሊፍዌብ አስነብቧል።

በጀዊ የስደተኞች መጠለያ ያለው የጤና ማእከል ከ60,000 በላይ ለሆኑ ስደተኞች አገልግሎት ይሰጣል።

የስደተኛ እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር አስተባባሪ አቶ ቤዛነህ ፈንታሁንን ጠቅሶ ሪሊፍዌብ እንደዘገበው፤ ከእርግዝና ጋር በተያያዘ የጤና እክል የሚገጥማቸው ነፍሰ ጡር ሴቶች የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት ከስድስት ኪሎ ሜትር በላይ ለመጓዝ ይገደዳሉ።

"ይህን ያህል ርቀት መጓዛቸው ከፍተኛ የጤና ችግር ያስከትላል" ብለዋል አስተባባሪው።

የመሠረተ ልማት አለመዘርጋት አንዱ ፈተና ነው። የድንገተኛ ሕክምና የሚሰጡ ባለሙያዎች አለመኖራቸው አዲስ የሚወለዱ ጨቅላዎችን እንዲሁም የእናቶቻቸውን ጤና አደጋ ላይ ጥሏል።

አስናቀ ጌታቸው በጀዊ የስደተኞች መጠለያ በሥነ ተዋልዶ ክፍል ውስጥ አዋላጅ ናቸው። ብዙ እናቶች እና ጨቅላ ሕጻናት እንደሚሞቱ ይናገራሉ።

"በዚህ ዓመት ሦስት እናቶች እና ሁለት ጨቅላ ሕጻናት ሲሞቱ አይቻለሁ። ደም ቢሰጣቸው ኖሮ ይተርፉ ነበር። ነገር ግን አምቡላንስ ስለሌለ ይህንን ማድረግ አልተቻለም" ብለዋል።

አፈወርቅ ሰለሞንም አዋላጅ ናቸው። ከአስናቀ ጋር ነው የሚሠሩት። በአንድ ቀን በአማካይ አምስት ወይም ስድስት እናቶች እንደሚወልዱ ተናግረዋል።

የሥነ ተዋልዶ ክፍሉ ስድስት አዋላጆች ብቻ ነው ያሉት። በሥነ ተዋልዶ ጤና ላይ የሚሠራው በተባበሩት መንግሥታት የሕዝብ ድጋፍ (ዩኤንኤፍፒኤ) የለገሰው አንድ አምቡላንስ አለ።

"እዚህ ቀዶ ሕክምና አንሰጥም። ስለዚህ ለሁለት ሰዎች ሪፈር ከተጻፈ አንዷ ሄዳ ሌላዋ የግድ መጠበቅ አለባት" ብለዋል አፈወርቅ።

ድጋፍ ማጣት

ሪሊፍዌብ በድረ ገጹ እንዳስነበበው፤ ዩኤንኤፍፒኤ እአአ በ2021 በጋምቤላ የሕክምና መስጫ ተቋማት የድንገተኛ ጊዜ ሕክምና መሣሪያዎች አከፋፍሏል።

መድኃኒት እና መብራትን ጨምሮ ሌሎችም የሕክምና መሣሪያዎች ናቸው የተከፋፈሉት። ይህም እናቶች እና ጨቅላ ሕጻናትን መንከባከብን ጨምሮ ለሌሎችም የሥነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎች ያግዛል።

አገልግሎቱ የሚሰጠው ለ104,894 ስደተኞች እና የጋምቤላ ነዋሪዎችም ጭምር ነው።

አዋላጆች እና ሌሎችም ሕክምና ሰጪዎች ሥልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል። በወሊድ ወቅት ለሚገጥም ችግር አስቸኳይ ሕክምና ለመስጠት አንድ አምቡላንስ በተባበሩት መንግሥታት ተለግሷል።

"ዩኤንኤፍፒኤ የሰጠን አልትራሳውንድ እና ሌሎችም መሣሪያዎች በአፋጣኝ የጤና እክሎችን ደርሰንባቸው የብዙ ሴቶችን ሕይወት እንድናድን ረድተዋል" ብለዋል አዋላጆቹ።

ጋምቤላ ውስጥ ከጥቃት የተረፉ ሴቶችን እና ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ ሴቶችን የሥነ ልቦና እንዲሁም ማኅበራዊ ድጋፍ የሚሰጥ ማእከል ይገኛል።

ሴቶች ከጥቃት ነጻ የሆነ ሕይወት እንዲኖራቸው የሚደግፍ ነው ማእከሉ።

ነገር ግን በየቀኑ ስደተኞች ወደ ጋምቤላ ይገባሉ። ሪሊፍዌብ እንደሚለውም፤ የስደተኞች ቁጥር መጨመር የምግብ እጥረት አስከትሏል።

ክልሉ ለረሃብ ተጋላጭ እንደመሆኑ የእናቶች እና ሴቶችን ደኅንነት ለመጠበቅ አስቸኳይ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተመልክቷል።

ዩኤንኤፍፒኤ የ14 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል። ይህም የሥነ ተዋልዶ ጤና አቅርቦትን ለማሻሻል እንዲሁም ወሲባዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶችን ለመደገፍ እንደሚውል ተገልጿል።

የተባበሩት መንግሥታት ያስፈልጋል ካለው ገንዘብ እስካሁን ድረስ የተሟላው 24% ብቻ ነው።

ናያቤል ያለችበት ሁኔታ ቢያሳስባትም ተስፋ አልቆረጠችም።

"አንድ ቀን ከልጄ ጋር ወደ አገሬ እንደምመለስ ተስፋ አለኝ። ቤተሰቦቼን ተቀላቅዬ አዲስ ሕይወት እንደምጀምር አምናለሁ።"