የሌሴቶ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶማስ ታባን ሚስታቸውን በመግደል ተከሰሱ

የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከባለቤታቸው ጋር

የፎቶው ባለመብት, AFP

የሌሴቶ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶማስ ታባን እአአ በ2017 አብረዋቸው የማይኖሩትን የትዳር ጓደኛቸውን ሊፖሌሎ ታባንን በመግደል ወንጀል ተከሰሱ።

የአሁኗ ባለቤታቸው ሜሳኢህም ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወንጀል ተከሰው የነበረ ሲሆን በዋስ ተፈተዋል።

ሜሳኢህ ግድያው በተፈፀመበት ወቅት ከቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር ታባን ጋር አብረው ይኖሩ የነበረ ሲሆን ነፍሰ ገዳዮችን በመቅጠር ክስ ቀርቦባቸው ነበር። ይሁን እንጂ ሁለቱም በግድያው ምንም ዓይነት ተሳትፎ አልነበረንም ሲሉ ክሱን ተቃውመዋል።

የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ታባን በግድያው መጠርጠራቸውን ተከትሎ ለወራት በደረሰባቸው ጫና እአአ 2020 ላይ ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ ተገደዋል።

ጉዳዩ በርካቶችን አስደንግጧል። ሙሉ በሙሉ በደቡብ አፍሪካ በተከበበችው አነስተኛ የባህር በር በሌላት አገር ፖለቲካዊ ቁጣንም አስከትሎ ነበር።

ሜሳኢህ ታባን የ82 ዓመቱ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ፍርድ ቤት ሲሄዱ አብረዋቸው ነበሩ።

ታጣቂዎች ሊፖሌሎ ታባንን ተኩሰው የገደሏት ታባን ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ቃለ መሃላ ከመፈፀማቸው ከሁለት ቀናት በፊት እአአ ሰኔ 14 2017 ላይ ነበር።

ሊፖሌሎ ወደ ቤቷ እየተመለሰች ሳለ ነበር የተገደለችው።

ታጣቂዎቹ አድፍጠው ከጠበቋት በኋላ በቅርብ ርቀት በርካታ ጊዜ በጥይት ተመትታ በአንድ ቆሻሻ ጎዳና ዳር ሞታ የተገኘችው። ያኔ 58 ዓመቷ ነበር።

በዚያን ጊዜ ሊፖሌሎ ከታባን ጋር በመራራ የፍቺ ሂደት ውስጥ እያለፈች ነበር። ከ2012 ጀምሮም ከባለቤቷ ጋር ተለያይተው ነበር ይኖሩ የነበሩት።

በዚህ ጊዜ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታባን ከ2012 እስከ 2017 ባሉት ጊዜያት ሜሳኢህ ጋር መኖር ጀመሩ። ከሜሳኢህ ጋር የተጋቡትም ሊፖሌሎ ከሞተች ከሁለት ወራት በኋላ ነበር።