ስለአዲስ አበባ የሚነገረው እና መሬት ላይ ያለው እውነታ

የፎቶው ባለመብት, AYELE
አለማየሁ ተስፋዬ ትዳሩን ከመሰረተ ገና አንድ ወር እንኳን አላስቆጠረም። ጥቅምት 21 ቀን "ድል" ባለ ሠርግ ነው ያገባው።
ታዲያ አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ በሚመሰርተው አዲስ ህይወት ብሎም በሠርጉ ቀን ላይ ጫና ሊያመጣ ይችል ይሆን በሚል ብዙ አውጥቷል አውርዷል።
"እንደ ሰው አገር ጦርነት ላይ ሆና፣ ሰው እየሞተ እኛ ሠርግ ስንደግስ ብዙ ደስ አይልም። ግን ደግሞ ህይወት ይቀጥላል" የሚለው አለማየሁ በሠርጉ ቀን ምን ይፈጠር ይሆን የሚለው ስጋት በትንሹም ቢሆን እንደነበረው ይናገራል።
"በእንዲህ አይነት ሁኔታ ማግባት፣ የተረጋጋ ኑሮ መመስረት እና ልጅ መውለድ የሚገፋፋ ባይሆንም የተሻለ ነገር ይመጣል ብለን እና እግዚያብሔርን አምነን ነው የተጋባነው" ሲል አሻግሮ ያያል።
መጪው ጊዜ እንዴት ይሆናል ብሎ ቢሰጋም፣ ከሕይወት አጋሩ ጋር በአንድ ቤት መኖሩ ግን ይህንን ከባድ ወቅት የሚጋራው ሰው ማግኘትም የአዲሱ ህይወቱ ሌላኛው ገጽታ መሆኑን ይናገራል።
መዲናዋ በነዋሪዎቿ እይታ እንዴት ሰንብታለች?
አለማየሁ ስለመጪው ጊዜ አነሳ እንጂ አሁን ላይ መዲናዋ አዲስ አበባ ያለችበት ሁኔታ በተለይም በውጭ የመገናኛ ብዙኃን ከሚሰማው ጋር እንደምትለይበት ይናገራል።
"በሚዲያ የምሰማው ነገር 'ከተማዋን ሌላ ቦታ ወሰዷት እንዴ?' ያስብላል። እኛ እየኖርነበት ነው። እንቅስቃሴው ሁሉ ሰላማዊ ነው። እንደውም አሁን ካፌ ተቀምጬ ማኪያቶ እየጠጣሁ ነው" ሲልም በአየር ላይ የሚሰማው በመሬት ላይ ከሚያየው ጋር እንዴት እንደሚጋጭበት ያነጻጽራል።
ይህ ሃሳብ የአለማየሁ ብቻ ሳይሆን ቢቢሲ ያናገራቸው ሌሎች የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጭምር ነው። አብዱም ከእነዚህ መካከል አንዱ ነው። ከተማዋ ውስጥ የተለየ ስጋት እንደሌለ ነገር ግን ከአገር ውጪ ያሉ ሰዎች "ጠዋት ሥራ መሄዳችን ጭምር እንደሚገርማቸው ይነግሩናል" ብሏል።
ጦርነቱን በመሸሽ የመጡ ዘመዶቹ በአንድ እስላማዊ ትምህርት ቤት ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ እና የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ተፈናቃዮችም አዲስ አበባ ውስጥ መታየት እንደጀመሩም ያክላል።

"የዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ ምላሽ ግነት ይኑረው እንጂ የአዲስ አበባ ኑሮ ግን እንደተለመደው አልቀጠለም፤ ሰዓት እላፊ ባይኖርም ሰዎች በጊዜ ወደ ቤታቸው ይገባሉ'' የሚለው መሐሪ* ትውልዱ እና እድገቱ አዲስ አበባ ሲሆን ቤተሰቦቹ የትግራይ ተወላጆች ናቸው። ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ የተማረው እዚያው አዲስ አበባ ነው።
ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ጀምሮ መገለል እንደሚደርስበት እና በተለይም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከወጣ ጀምሮ በትግርኛ ማውራትም ሆነ ሙዚቃዎችን መስማት አስፈሪ መሆኑን ይናገራል። ጠዋት ከቤቱ ሲወጣም "ላልመለስ እችላለሁ" በሚል ለእስር ተዘጋጅቶ እንደሚወጣ ይናገራል።
ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረገችው ራሕዋ* በተመሳሳይ "ግዴታ ካልሆነብኝ ከቤቴ አልወጣም። መታወቂያዬ ብሔር ባይገልጽም በአባቴ ስም የትግራይ ተወላጅ መሆኔ ስለሚታወቅ እሳቀቃለሁ። ከቤት ከወጣሁ ግን ልታሰር እችላለሁ በሚል ተዘጋጅቼ ነው የምወጣው" ትላለች።
በተለይም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኩል መንግሥት በተደጋጋሚ በማንነት ማንነት ላይ የተመሰረተ እስር እያካሄደ እንዳልሆነ አስተባብሏል። ይልቁንም በሽብርተኛ ቡድንነት ከሰየማቸው ቡድኖች ጋር ግንኙነት ባላቸውና መረጃ በተገኘባቸው ላይ ብቻ ያነጣጠረ እርምጃዎች ናቸው ሲልም ክሶቹን አጣጥሏል።
ከጦርነቱ አንጻር ያለው አመለካከት እና የሚሰጠው ምላሽ በማኅበረሰቡ መካከል ለዘመናት በነበረው ማኅበራዊ ትስስር ላይ የራሱ የሆነ ጥላን በማሳረፉ ስጋትና ጥርጣሬን መፍጠሩ አልቀረም።
መሐሪ "ራሴን እንደፈለኩ አልገልጽም። በቅርቡ በአንድ ጓደኛዬ ሠርግ ዕለት ትግርኛ ዘፈን መክፈት የሚያሳቅቅ ስሜት ተፈጥሮ ነበር" ሲል ያስታውሳል።
ራሕዋ አማራ ክልል ውስጥ ተወልዳ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ነው ወጣትነቷን ያሳለፈችው። ''ጦርነቱ ሲቀሰቀስ ትግራይ ውስጥ ስላሉ ቤተሰቦቼ ይጠይቁኛል ያጽናኑኛል ብዬ ጓደኖቼን ብጠብቅም ያ አልሆነም። አንዳንዴ ይገባቸዋል የሚል መልክት ጭምር በማኅበራዊ ሚዲያቸው ሲጽፉ አይ ነበር። ከዚህ ጦርነት በፊት ብሔር የለኝም ኢትዮጵያዊ ነኝ ብዬ ነበር የማስበው። አሁን ግን አብረን ክፉ እና ደግ ያሳለፍን ጓደኞቼ አገር እንደካደ ሰው ነው የሚያገሉኝ" ስትልም ታስረዳለች።

ከዚህ ቀደም በዞን ዘጠኝ የጦማሪያን ቡድን ውስጥ እንዲሁም አሁን በሚሳተፍበት የሲቪል ማኅበረሰብ ሥራው የሚታወቀው በፍቃዱ ኃይሉ እንደከተማዋ ነዋሪ ብሎም የአገሪቱን ፖለቲካ በቅርበት እንደሚከታተል ሰው በእርግጥም እነዚህ እውነታዎች በመዲናዋ እየታዩ እንደሆነ ታዝቧል።
"አዲስ አበባ ውስጥ አሁን የትግራይ ተወላጅ መሆን ከባድ ነው" የሚለው በፍቃዱ፣ አንዳንድ ሰው የተለየ የፖለቲካ አመለካከት ካላቸውና እዚህ ላይ ብሔር ሲጨመርበት በቀላሉ ለህወሓት ወግነዋል በሚል በቀላሉ ይጠረጠራሉ'' ይላል።
"ይህ የሚመነጨው ከመንግሥትም ከማኅበረሰቡም ነው። ምክንያቱም ማኅበረሰቡ በትግራይ ተወላጅ እና በህወሓት መካከል ያለውን ቀጭን ልዩነት ለመረዳት አቅም ወይም ፍላጎት የለውም። ስለዚህ ጉዳዩን ይህ እንዳከበደው መረዳት ይቻላል'' ሲልም ያስረዳል።
ነገር ግን አሁን እየተከሰተ ስላለው ሁኔታ ለመረዳት ወደ ኋላ ሄዶ አውዱን መዳሰስ የግድ አስፈላጊ ነው ብሎ በፍቃዱ ያምናል።
የአዲስ አበባ ለውጦች አውዱ ሲዳሰሱ
በፍቃዱ አሁን አዲስ አበባ ውስጥ ያለው ሁኔታ የሚገልጸው ቃል ቢኖር "ድንጋጤ" ነው ይላል። አሁን የሚዋጉት የፖለቲካ ኃይሎች ግጭት በቀድሞው ኢሕአዴግ አባላት መካከል ሲሆን፣ ተጽዕኖ ፈጣሪው ህወሓት ትግራይን እንዲሁም ቀሪዎቹ ደግሞ የፌደራል መንግሥቱን ይዘው "አላውቅህም ተባባሉ" ሲል ያስታውሳል።
ይህ ሲጦዝ የቆየ የፖለቲካ ውጥረት ወደ ጦርነት ሲሸጋገርና እየተስፋፋ ሲመጣ "አዲስ አበባ ላይ መዳረሻውን እንዳደረገ ምልክቶቹ መታየት ጀመሩ'' ሲል በፈቃዱ ድንጋጤ ሲል የጠራውን ሁኔታ ያብራራል።
"ድንጋጤው በምን ይገለጻል ከተባለ፤ መንግሥት ደንጧል። ለዚያ ነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጀው። ከፍተኛ ቁጥጥርና ፍተሻ በየመንገዱ አለ፣ ሬዲዮና ቴሌቪዥኑ የሚያወራው ተጠንቀቁ ራሳችሁን ጠብቁ ነው። ይህ ደግሞ ማኅበረሰቡ እርስ በእርስ በጎሪጥ እንዲተያይ ያደረገ ነው።"
አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች ምናልባት ነገሮች ከተባባሱ በሚል ከተለመደው በላይ የሚሆን አስቤዛ የመግዛት አዝማሚያ አለ የሚለው በፍቃዱ "የምሽት ህይወቱ ቢቀንስም የተወሰነ እንቅስቃሴ አለ" ሲል ይጠቅሳል።
ይህ ሁኔታ ደግሞ በትግራይ ተወላጆች ዘንድ እንደሚለይ የሚናገረው በፍቃዱ በአገሪቱ ውስጥ ያለው ጥልቅ የፖለቲካ ክፍፍል ያመጣው የትርክት ልዩነት መሆኑን ያመለክታል። በዚህ የትርክት ልዩነት ምክንያት የትግራይ ተወላጅ በሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የጥርጣሬና የጥቆማ ኢላማ የመሆን አዝማሚያ መኖሩንም ይናገራል።

የፎቶው ባለመብት, Addis Ababa City Press Secretary/fb
የዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ ርብርብ ግነት ወይስ የተጨባጭ ስጋት ምልክት?
ዲፕሎማቶች አገር ጥለው ሲወጡ መመልከቱን የሚናገረው ከአየር ትራንስፖርት ጋር የተገናኘ ሥራ ያለው አብዲ "የውጭ ሚዲያዎች የምታወሩት ግን እዚህ ካለው የተቃረነ ነው። ይሄ ነው ከውጪ አገር አልፎ አገር ውስጥ ያለውን ሰው ጭንቀት ውስጥ የሚከተው። እኔ ፖለቲካ ነው ብዬ አስባለሁ" በማለት ምን ሸሽተው ነው የሚወጡት የሚል ጥያቄ ያነሳል።
ይህ በርካታ ሰዎች በተይም በማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች ላይ ሲያጋሩት የነበረ ጥያቄያቸው ነው።
በርግጥም በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ኤምባሲዎች ከሠራተኞቻቸው ባሻገር ዜጎቻቸው ኢትዮጵያን፤ ብሎም አዲስ አበባን ለቀው እንዲወጡ ሲወተውቱ ሰንብተዋል። እነዚህ ማስጠንቀቂያዎች አሁንም ተጠናክረው ቀጥለዋል።
አንዳንድ ተቋማት አገር ለቀው ለመውጣት ለሚፈልጉ የአገር ውስጥ ሠራተኞች ሳይቀር አማራጮች በመስጠት ከሌላ አገር ሆነው ሥራቸውን እንዲቀጥሉ እያመቻቹ ነው።
በፍቃዱ የዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ ለቆ የመውጣት ርብርብ የተወሰነ ግነት ያዘለው መሆኑን እና ለዚህም ሁለት ምክንያቶች አሉ ይላል።
''ምዕራባዊያኑ ከአፍጋኒስታን ድንጋጤያቸው እየወጡ ስለሆነ እንደዚያ አይነት ነገር ሳይከተል በሚል የሚደረግ ርብርብ ይመስለኛል። ነገር ግን ስጋቶች ሊኖራቸውም ይችላል።"
ለግነቱ ሌላው ገፊ ምክንያት በምዕራቡ ዓለም ያሉ የተዛቡ አረዳዶች ናቸው የሚለው በፍቃዱ "የተዛቡ ዘገባዎች እና ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ባለሞያዎች ይህንን ስጋት አጋነው እና አዛብተው ግብአት መስጠታቸው ተደራርቦ ለዲፕሎማሲ ጫና ዳርጓል» ሲል ያስረዳል።
የ'ክራይስስ ግሩፕ' ተንታኝ የሆነው ዊሊያም ዳቪሰን በተለይም የአሜሪካ መንግሥት በቅርቡ ያወጣቸውን መግለጫዎች እና የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎችን ነጣጥሎ ይመለከታል።
የአሜሪካ መንግሥት ስለአየር መንገዱ እና ስለሽብር ጥቃት ስጋቶች ያወጣቸውን መግለጫዎች ሲያዘጋጅ የተመሰረተበት መረጃዎች ሊኖሩት እንደሚችሉ ከግምት መክተት ቢያስፈልግም ነገር ግን "እነዚህ መግለጫዎች በቅርቡ በካቡል በነበረው ክስተት ጫና ስር የወደቁ ናቸው ብዬ አምናለሁ" ይላል።
እናም "መግለጫዎቹ የአሜሪካ ዜጎችን ለመድረስ ያሰቡ ቢሆኑም ኢትዮጵያውያን ያሏቸውን ስጋቶችን ግን ከግምት ውስጥ ያላስገቡ ናቸው" ሲል ያስረዳል።
ሁለተኛው በመገናኛ ብዙኃን በኩል ያለው ጉዳይ ነው የሚለው ዳቪሰን፣ ለምሳሌም ሲኤንኤን አማጺያኑ አዲስ አበባ ጥግ ላይ ደርሰዋል ሲል መዘገቡን እንደ ምሳሌ ያነሳል።
"የተወሰኑ የኦሮሞ ነጻነት ጦር ታጣቂዎች 50 እስከ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ያለው ቦታ ላይ ይንቀሳቀሳሉ ቢሉ እሺ። ይህም ምናልባት ነው። ይህ ግን አዲስ አበባ ጥግ ደርሰዋል ማለት ግን አያስችልም። ስለዚህ አንዳንዶች ሆን ተብሎ ሊጨመር የተፈለገ ጫና አለ እንዲሉ ያደረገ ይመስለኛል። ነገር ግን ይህ በተወሰነ መልኩ ስህተት የሆነ ዘገባ እና ስር የሰደደ ትኩረት ለማግኘት የሚደረግ ዘገባ (sensational coverage) ተደምረው ያመጡት ውጤት ነው" ሲል ዳቪሰን ለቢቢሲ ተናግሯል።
ጨምሮም የዓለም አቀፉ ሕብረተብ ያለ ምንም መሰረት ነው ለቆ እየወጣ ያለው ማለት ግን "ስሜት የማይሰጥ ትንተና" ነው ይህም አማጺያኑ ደሴ እና ኮምቦልቻን ከያዙ በኋላ ባሉ ቀጣይ ሳምንታት እና ወራት አዲስ አበባ ሊደርሱ እንደሚችሉ የሚያሳይ ስጋት መፍጠሩ የማይካድ ነው ይላል።
ስጋት ስላለ እኮ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሲቪል ሥልጣናቸውን ለምክትላቸው ወክለው ጦር ሜዳ የሄዱት። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም የታወጀው እና የአካባቢ ጥበቃ ኮሚቴ በመላው አዲስ አበባ የተቋቋመው ስጋት ስላለ ነው" ሲልም ዳቪሰን ያስረዳል።
መንግሥት እንደመንግሥት ያለው ትልቁ ሥራ ሕብረተሰቡን ማረጋጋት፣ ማዘጋጀትና ማስተባበር ነው የሚለው ዳቪሰን የዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ ምላሾችን ማስተባበሉም የሚጠበቅ ነው ይላል። ይህም ሕብረተሰቡ ውስጥ ድንጋጤ ከተከሰተ በርካታ ሥርዓቶች እንደሚዛቡ እሙን መሆኑን ይጠቅሳል።
አዲስ አበባ ተስፋ እና ስጋቶቿ በልዩ ልዩ መነጽሮች እንዴት ይታያሉ?
አለማየሁ አና አብዲ ይህ ጦርነት እንዲያበቃ ብሎም ነገሮች እንዲረጋጉ መንግሥት ከሰራ በሕዝቦች መካከል የተፈጠረው መጠራጠር ሊጠብ ብሎም የተሻለ ቀን ሊመጣ እንደሚችል ያምናሉ።
"እንደ አንድ አማኝ ሰው ይህን ጊዜ ጠንካራ እምነት እና ሥነልቦና ያለው ሰው ያልፈዋል ብዬ አምናለሁ። አሁን ካለው ችግር አለፍ ብዬ ስመለከት ተስፋ የሚሰጥ ጊዜ ይመጣል ብዬ አምናለሁ" ሲል አብዲ ለቢቢሲ ተናግሯል።
መሐሪ ግን በግሉ ለመጪው የህይወት ዘመኑ የሚታየው ተስፋ ማጣቱን ያብራራል።
"እኔ አዲስ አበባ ተወልዶ እንዳደገና ትግራይ ሄዶ ለማያውቅ ሰው ተስፋ አይታየኝም። አባቴ በልጅነቱ ነው ከትግራይ የወጣው። አሁን እናቴም አባቴም በህይወት የሉም። ሪፈረንደም የሚባለው ነገር ቢካሄድ እኛ የት ነው የምንኖረው? ማን አለን?" ሲል ይጠይቃል።
የራሕዋ ዕይታ ከመሐሪ ይለያል። "ጦርነቱ ሲያበቃ የተሰበረው ልቤ እንዴት ይጠገናል? ይቅር ለመባባል ምን ያህል ብርታት አለን? ይሄ አያቶቼም፣ ወላጆቼም እኔም በየትውልዳችን እያለፍንበት ያለ መከራ ነው። ልጆቼስ? አሁን ስሜታዊ ሆኜ ሊሆን ቢችልም ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ድሮው እንዴት እኖራለሁ? ሌላ አገር ውስጥ እየተሳደድኩ የምኖር እንጂ እንደ ዜጋ አይሰማኝም" ትላለች።
እንደመውጫ
በፍቃዱም ሆነ ዳቪሰን እንደሚሉት ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካ ትልቁ መግቢያ በር እና የዲፕሎማሲ ማዕከል የተባለችው የአዲስ አበባ ትልቁ ተስፋ የሚመነጨው ግጭቱን በጠረጴዛ ዙሪያ የመፍታት ዕድል ካላቸው ነው።
ዳቪሰን በበኩሉ ግጭቱ ካልቆመ አዲስ አበባ ሊደርስ የሚችልበት ዕድል የለም ብሎ መመልከት አይገባም ይላል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ ነዋሪ ብሎም በልሂቃን ዘንድ ያላቸው ድጋፍ እና ለህወሓት ከፍተኛ ተቃውሞ ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች በከተማዋ መኖራቸው አዲስ አበባ ጠንካራ ምከታ ሊኖር እንደሚችል ይገልጻል።
"እንዲሁም የትግራይ ተወላጆች ላይ የሚታየው እስር ወደ ጥቃት ካመራ ምን አልባት አማጺያኑ ባልተጠና እና ለሚከተለው ውጤት ሳይዘጋጁ ከገቡ፣ ከከተማዋ አልፎ በአገሪቱ እንዲሁም በአህጉር ደረጃ ዘርፈ ብዙ ቀውስ ሊከተል ይችል ይሆንል የሚል ትንተና መስጠት ይቻላል" ሲልም ዳቪሰን ያክላል።
በፍቃዱ "ብዙሃኑ አዲስ አበቤ ድጋፉ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ነው የሚል ግምገማ መስጠት ይቻላል" ይላል። አማጺያኑ ወደ አዲስ አበባ "አይመጡም፣ አይችሉም እና አያሸንፉም የሚል ዕይታ ነው በአብዛኛው የሚታየው'' ይላል።
በጦርቱ ውስጥ እተሳተፉ ያሉ አካላት እንደ ፓርቲም ይሁን እንደ ሕዝብ ህልውናቸው አደጋ ላይ እንደወደቀ ማሰባቸው ሰጥቶ በመቀበል ላይ የተመሰረተ መፍትሔ ለማምጣት የሚደረገውን ሂደት አስቸጋሪ እንደሚያደርገው ይጠቅሳል።
"በጦርቱ ውስጥ የሚሳተፉ አካላት 'በቃ ከአሁን በኋላ አቅማችን ለውጊያ ደክሟል፤ እስቲ ሌሎች አማራጮችን እንፈልግ' ብለው ወደ ንግግር ይገባሉ'' የሚል ተስፋ እንዳለውም ይናገራል።
ይህ ጦርነት ወታደራዊ አሸናፊ እንጂ ዘላቂ አሸናፊ ይኖረዋል የሚል እምነትም የለውም በፍቃዱ። የፌደራል መንግሥቱ መቀለን ሲይዝ እንደሆነው አይነት የውጊያ ድሎች ሊኖሩ ቢችሉም በዘላቂነት አንዱ አሸነፈ ለማለት አስቸጋሪ ነውም ይላል።
ጦርነቱ በፖለቲካ ልዩነት ቢጀመርም አሁን ሕዝቦች ከስሜት በሚመነጭ ሁኔታ እየተሳተፉበት በመሆኑ፣ ዋነኛው ተስፋ ውይይት ነው ብሎ እንዲያምን አድርጎታል።
*ለደኅንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዲቀየር የጠየቁ














