ደቡብ አፍሪካ በአዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ አትደናገጡ አለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የደቡብ አፍሪካ የጤና ሚኒስትር አሚክሮን ተብሎ በተጠራው ልውጡ የኮሮናቫይረስ ዝርያ "ፍጹም መደናገጥ አያስፈልግም" ብለዋል።
በልውጡ የተያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ባለበት ሁኔታም ሚኒስትሩ ከዚህ ቀደም እንዲሁ በከፍተኛ መጠን የሚተላለፈውና በደቡብ አፍሪካ የተገኘውን ቤታ የተባለውን የኮሮናቫይረስ ዝርያን በመጥቀስ "ከዚህ ቀደም አይተነዋል" ብለዋል ሚኒስትሩ ጆ ፋህላ
ደቡብ አፍሪካ በአገሪቱ ላይ የተጣለው የጉዞ እገዳ በአስቸኳይ መነሳት አለበት ስትልም አውግዛለች።
ልውጡ ኦሚክሮን አለምን በከፍተኛ አደጋ የጣለ የጤና ስጋት በሚል ተመድቧል። በአሁኑ ወቅት ያሉ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በከፍተኛ ሁኔታ የመተላለፍ ሁኔታና እንደገና የመያዝ አደጋም ደቅኗል።
ልውጡ በቅርቡ መጀመሪያ ላይ በደቡብ አፍሪካ ከተገኘ በኋላ ባለፈው ረቡዕ ለአለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ተደርጓል።
አዲሱ ዝርያ በቅርቡ በሁለት ሳምንታት ውስጥ በደቡብ አፍሪካ በርካታ ህዝብ በሚኖርባት ጓውተንግ ግዛት ውስጥ በኮሮናቫይረስ ለተያዙት አብዛኛዎቹ ተጠያቂ ነው።
በዓለም ጤና ድርጅት መረጃ መሰረት በሃገሪቱ ውስጥ በሁሉም ግዛቶች በኮሮናቫይረስ እየተያዙ ያሉ ሰዎች እየጨመረ መምጣቱንም ነው።
ደቡብ አፍሪካ በባለፈው ሳምንት እሁድ ዕለት 2 ሺህ 800 አዳዲስ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎችን ሪፖርት ያደረገች ሲሆን ይህም አኃዝ ከባለፈው ሳምንት ከነበረው 500 ዕለታዊ አማካኝ መጨመሩን ያሳየ ነው።
የመንግሥት አማካሪና የበሽታዎች አመጣጥ ተመራማሪ ሳሊም አብዱል ከሪም በያዝነው ሳምንት መጨረሻ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በቀን ከ10 ሺህ በላይ እንደሚደርስ እና የጤና ማዕከላት በሚቀጥሉት ሁለት እና ሶስት ሳምንታት ውስጥ ከፍተኛ ጫና ይደርስባቸዋል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር ፋህላ በበኩላቸው በድጋሜ የተናገሩት "በፍፁም መደናገጥ አያስፈልግም። ምክንያቱም ለኛ ይህ አዲስ አይደለም"
"በኮሮናቫይረስ ከ20 ወራት በላይ ልምድ አለን በዚህ ወቅትም አዳዲስ ልውጦችን እንዲሁም ያገረሹ ወረርሽኞችን አይተናል" ብለዋል ሚኒስትሩ ለመገናኛ ብዙኃን
ሰኞ እለት ጃፓን ሁሉንም የውጭ ዜጎች ወደ አገሯ እንዳይገቡ በማገድ ከባድ የድንበር ገደቦችን የጣለች የመጨረሻዋ ሀገር ሆናለች።ቀደም ሲል በደቡብ አፍሪካ እና በሌሎች ደቡባዊ የአፍሪካ ሃገራት ላይ የጉዞ እገዳ ከጣሉት መካከል እንግሊዝ፣ የአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ ይገኙበታል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የደቡባዊ አፍሪካ መገለል በጣም ያሳስበኛል ሲሉ ገልፀው "አፍሪካ ውስጥ ላለው ዝቅተኛ የክትባት ደረጃ የአፍሪካ ህዝብ ተጠያቂ ሊሆን አይችልም" ብለዋል።












