የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኢትዮጵያ ያለው ጦርነት በአስቸኳይ እንዲቆም ጠየቀ

የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በኢትዮጵያ ያለው ጦርነት በአስቸኳይ እንዲቆም በድጋሚ ጠየቁ።

የኮሎምቢያ መንግሥት ከቀድሞው የኮሎምቢያ አብዮታዊ ጦር ኃይሎች (ፋርክ) ሽምቅ ተዋጊዎች ጋር የተፈራረመውን የሰላም ስምምነት አምስተኛ ዓመት መታሰቢያን ለማክበር ኮሎምቢያን በመጎብኘት ላይ ያሉት አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የኢትዮጵያ መንግሥት አርአያነቱን እንዲከተል ጠይቀዋል።

"በኮሎምቢያ ያለው የሰላም ሂደት ኢትዮጵያን ለማዳን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አፋጣኝ የተኩስ አቁም እንዲደረግ በአገሪቱ ላሉ ተፋላሚ ወገኖች አስቸኳይ ጥሪ እንዳቀርብ አነሳስቶኛል" ብለዋል።

ዋና ፀሐፊው ተኩስ አቁም ስምምነቱ "በውይይት ቀውሱን ለመፍታት እና ኢትዮጵያ ለቀጠናው መረጋጋት እንደገና የበኩሏን አስተዋፅዖ እንድታደርግ ያስችላል" ብለዋል።

አሜሪካ ግጭቱ እየተባባሰ ባለበት በአሁኑ ወቅት "ወታደራዊ መፍትሄ" እንደሌለ ባስጠነቀቀችበት ወቅት ነው ዋና ፀሐፊው ይህንን የተናገሩት።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዲፕሎማሲ ለግጭቱ "የመጀመሪያው፣ የመጨረሻው እና ብቸኛው አማራጭ" ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አማፂያኑን ለመዋጋት ወደ ጦር ግንባር በመሄድ ሠራዊቱን እመራለሁ ያሉ ሲሆን የትግራይ ተዋጊዎችም ወደ ዋና ከተማዋ አዲስ አበባ እያመሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በትግራይ ተቀስቅሶ ወደ አጎራባቾቹ አማራና አፋር ክልል የተዛመተው ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስከተሉን ቀጥሏል።

በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች በረሃብ አፋፍ ላይ ሲሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደግሞ ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግሥታትና የእርዳታ ድርጅቶች አመልክተዋል።