ቦይንግ ከ737 ማክስ ጋር ተያይዞ ያለውን የደህንነት ስጋት ውድቅ አደረገ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
"በታሪክ እጅግ በከፍተኛ ሁኔታ የተፈተሸ የትራንስፖርት አውሮፕላን" ተብሎ ተጠርቷል፤ ነገር ግን አንዳንድ ተቺዎች ቦይንግ 737 ማክስ አሁንም ደህንነቱ የተጠበቀ አይደለም ብለው ያምናሉ።
በመቶዎች የሚቆጠሩ መንገደኞች ያለቁበት ሁለት አሰቃቂ አደጋዎችን ተከትሎ ከስራ እንዲቆም ተደርጎ የነበረው ቦይንግ 737 ማክስ ባለፈው አመት በድጋሚ እንዲበር በአሜሪካ ተቆጣጣሪዎች ተፈቅዶለታል።
ሆኖም ግን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በ737 ማክስ በረራዎች ላይ በርካታ እንደ ከባድ ችግሮች የሚታዩ ሁኔታዎች ተዘግበዋል።
ቦይንግ አውሮፕላኑ ደህንነቱ የተጠበቀ እና አስተማማኝ መሆኑን ገልጿል።
በያዝነው አመት ጥቅምት ወር ላይ 737 ማክስ አውሮፕላን ከሲያትል ቦይንግ ፊልድ አየር ማረፊያ ተነስቶ ወደ ብራስልስ አቀና። በረራው አዲሱን አውሮፕላን ለባለቤቶቹ ማለትም ቱኢ ለተባለ የጉዞ ቡድን ለማድረስ ያቀደ ነበር።
ነገር ግን ወደ አምስት ሺህ ማይል (ስምንት ሺህ ኪሎሜትር) ርቀት ያለውን ጉዞ በጀመሩ በደቂቃዎች ውስጥ አብራሪዎቹ አስቸኳይ "የበረራ መቆጣጠሪያ ችግር" ስላጋጠማቸው ወደ ኋላ መመለስ ነበረባቸው። ብዙም ሳይቆይ አውሮፕላኑ በሰላም አረፈ።
ችግሩ ያለ ፖይለት በራሱ የሚቆጣጠረው "አውቶ ፓይለት" ጋር የተገናኘ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን በአንጻራዊነት በፍጥነት ተስተካክሏል።
አውሮፕላኑ በማግስቱ እንደገና ወደ ብራስልስ አቀና እና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በመደበኛነት በረራ እያደረገ ነው።
ሆኖም፣ ይህ የብራስልሱ ጉዳይ የተናጠል ክስተት አልነበረም።
በአሜሪካ የሚገኝ ማንኛውም የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት አቅራቢ ወይም የጥገና ጣቢያ በአውሮፕላኑ ላይ ከባድ ብልሽት፣ ወይም ጉድለት ሲያገኝ፣ ይህንን ለሚቆጣጠረው የፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር "የአገልግሎት ችግር ሪፖርት" ተብሎ በሚጠራው በኩል ማሳወቅ አለበት።
737 ማክስ እንደገና ወደ አገልግሎት ከተመለሰ በኋላ ከ180 በላይ ሪፖርቶች ቀርበዋል።
አብዛኛዎቹ ስህተቶች በመሬት ላይ በነበሩ አውሮፕላኖች ላይ ቢሆኑም በ22 አጋጣሚዎች በበረራዎች ላይ የተከሰቱ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ አራቱ አብራሪዎች ድንገተኛ አደጋዎች በማለት ጥሪ አቅርበዋል።
የአሜሪካ አብራሪዎች በሞተር ብልሽት ሳቢያ ተጨማሪ ሁለት ጊዜ ድንገተኛ አደጋዎችን ሪፖርት አድርገዋል።
እነዚህ ክስተቶች በአሁኑ ጊዜ በፌደራል አቪየሽን አስተዳደሩ መረጃ ዝርዝር ውስጥ ባይታዩም በንግድ አቪዬሽን ውስጥ ያሉ አደጋዎችን እና ክስተቶችን በሚዘረዝረው በአቪዬሽን ሄራልድ ድረ-ገፅ ላይ ይገኛሉ።
ችግሮቹ የተከሰቱት እስከ ጥቅምት ወር አጋማሽ ድረስ ከ160 ባነሱ አሜሪካ አውሮፕላኖች ላይ ነው። ከነዚህ ውስጥ የተወሰኑት በኤሌክትሪክ ችግር ምክንያት ለብዙ ሳምንታት አገልግሎት እንዳይሰጡ ተደርገዋል።
ከአውሮፕላኑ ጋር የተያያዘ የአገልግሎት ችግር ሪፖርቶች በካናዳ ተቆጣጣሪ፣ ካናዳ ትራንስፖርት ይፋ ሆነዋል።
መረጃዎቹ እንደሚያመላክቱት ከ56 የ737 ማክስ የካናዳ አውሮፕላኖች ውስጥ 19ቱ ሪፖርት የተደረገባቸው ሲሆን ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ አምስቱ በበረራ ላይ የተከሰቱ ክስተቶችን የሚመለከቱ ናቸው።
737 ማክስ አሁንም ቢሆን ከፍተኛ ክትትል እየተደረገበት ሲሆን አውሮፕላኖቹ በአውሮፓውያኑ 2019 ለ20 ወራትም ያህል አገልግሎት እንዳይሰጥ የተደረገው በሁለት አሰቃቂ አደጋዎች 346 ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ ነው።
በቅርቡም ቦይንግ በኢትዮጵያ አየር መንገድ 737 ማክስ አደጋ ከሞቱት 157 መንገደኞችና የበረራ ሠራተኞች ቤተሰቦች ጋር ስምምነት ላይ ደርሷል።
የአውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ በአደጋው ለሞቱት ሰዎች ኃላፊነቱን እንደሚወስድና ተጠያቂነቱንም የሚቀበል ሲሆን በምላሹም የተጎጂ ቤተሰቦች ኩባንያው ላደረሰው ጉዳት በፍርድ ቤት ቅጣት እንዲጣልበት አይጠይቁም።












