ከትዳር ውጪ በመውለዷ ሳታውቅ ልጇ ለማደጎ የተሰጠባት ሕንዳዊት እናት

አኑፓማና ፍቅረኛዋ አጂት

የፎቶው ባለመብት, Vivek Nair

ሕንዳዊቷ እናት የጠፋውን ልጇን ለማግኘት ለአንድ ዓመት ያደረገችው ፍለጋ በቅርቡ በፍርድ ቤት በኩል ልጇን በማግኘቷ ፍፃሜውን አግኝቷል።

እንዴት ልጇን በፍርድ ቤት ልታገኝ ቻለች? ሶውስቲክ ቢስዋስ እና አሽራፍ ፓዳና በበርካቶች ዘንድ ቁጣንና ንዴትን ያስከተለውን እንዲሁም በፖለቲካውም በኩል ከፍተኛ ትኩረት ያገኘውን ቅሌት ዘግበዋል።

በሕንድ ደቡባዊ ክፍል ኬራላ ግዛት ባለትዳሮች የጠፋው ልጃቸው እንዲመለስላቸው በአንድ የጉዲፈቻ ኤጀንሲ ደጃፍ ላይ ከሁለት ሳምንታት በላይ ሲማፀኑ ቆይተዋል።

ባለትዳሮቹ ዝናብ ሳይበግራቸው ለሰዓታት ያለመሰልቸት በር ላይ ቆመው ልጃቸውን እንዲመልሱላቸው ይለምናሉ።

ሲመሽ እዚያ አካባቢ ያቆሟት መኪናቸው ውስጥ ገብተው ያድራሉ። በነገታውም ተነስተው ይህንን ያደርጋሉ።

እናትየው "ልጄን ስጡኝ" የሚል የተፃፈበት ፖስተር ይዛለች። ቤተሰቦቿ ያለፈቃዷ ልጇን ለማደጎ አሳልፈው እንደሰጡም ትናገራለች፤ ይህንን አባቷ አይቀበሉትም።

ባለፈው ዓመት በጥቅምት ወር መጀመሪያ አኑፓማ ኤስ ቻንድራን በአካባቢው በሚገኝ ሆስፒታል 2 ኪሎ ግራም የሚመዝን ወንድ ልጅ በሰላም ተገላለገለች።

የ22 ዓመቷ የመብት ታጋይ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆኖ የሚሰራው የ34 ዓመቱ አርጂት ኩመር ቤቢ ነው የልጇ አባት። አርጂት ኩመር ቤቢ ፍቅረኛዋ ሲሆን ግለሰቡ ከዚህ በፊት ትዳር መስርቶ የነበረ መሆኑና ልጃቸውንም ከጋብቻ ውጪ በመውለዷ ለአኑፓማ ማኅበራዊ መገለልን አድርሶባታል።

ግንኙታቸውም ሆነ እርግዝናዋ በቤተሰቡ ውስጥ ከፍተኛ ረብሻን ፈጥሯል።

በሕንድ ከጋብቻ ውጭ ልጅ መውለድ ከነውር በላይ ሆኖ ነው የሚታየው።

ከዚህ በተጨማሪ ጉዳዩን የተወሳሳበ ያደረገው አኑፓማ በሕንድ ባለው የማኅበረሰብ አመዳደብ ከፍ ካለው ስፍራ ከሚቀመጡ ቤተሰቦች የመጣች ሲሆን ጓደኛዋ አጂት ደግሞ ዳሊት ከሚባሉት ወይም ቀድሞ አይነኬ ናቸው ከሚባሉት ዝቅተኛ የማኅበረሰብ መደብ ነው የተወለደው።

በነዚህ ማኅበረሰቦች መካከል ደግሞ ጋብቻ የተወገዘ ነው።

አኑፓማና ፍቅረኛዋ አጂት

የፎቶው ባለመብት, Vivek Nair

ሆኖም ሁለቱ ግለሰቦች ከተለያየ መደብ የመጡ ቢሆኑም በመካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙት የአኑፓማም እና የአጂት ቤተሰቦች በርካታ ሕንዳውያን ተራማጅ ብለው ከሚጠሯቸው ይመደባሉ።

ሁለቱም ቤተሰቦች የግዛቲቷ ገዥ የሆነው የሕንድ ኮሚኒስት ፓርቲ ጠንካራ ደጋፊዎች ናቸው። ኬራላ የኮሚዩኒዝም መሰረት ከሚባሉት ግዛት አንዷ ናት።

የአኑፓማ አባት የባንክ ሥራ አስኪያጅ እንዲሁም የአካባቢው ፓርቲ መሪ ናቸው። አያቶቿ ደግሞ ታዋቂ የሠራተኛ ማኅበራት አነቃቂ እንዲሁም የማዘጋጃ ቤት አባላት ነበሩ።

የፊዚክስ ምሩቋ አኑፓማ በኮሌጅ በነበረችበት ወቅት የኮሚዩኒስት ፓርቲ የተማሪዎች ሕብረትን በመምራት የመጀመሪያዋ ሴት ነበረች። አጂት የፓርቲው የወጣቶች ክንፍ መሪ ነበር።

ያደጉት በአንድ ሰፈር ውስጥ ሲሆን የተገናኙት በኮሚዩኒስት ፓርቲ ውስጥ አንድ ላይ ሲሰሩ ነበር። ከሦስት ዓመታት በፊት አብረው መኖር ጀመሩ።

አጂት በወቅቱ ከሚስቱ ጋር ተለያይቶ የነበረ ሲሆን ከቀድሞ ትዳሩም ልጅ አልነበረውም።

"መጀመሪያ ላይ ስንተያይ በፍቅር ወድቀን ወይም እንደዚያ አይነት አልነበረም። ጓደኛ ሆነን ጀመርን። ከዚያም በኋላ አብረን ለመኖር ወሰንን" ትላለች አኑፓማ።

ባለፈው ዓመት አኑፓማ ፀነሰች እናም ጥንዶቹ ልጁን ለመውለድ ወሰኑ። "ሕፃኑን ለመውለድ ምንም አይነት ጥርጣሬ አልነበረንም። ወላጆች ለመሆን ዝግጁ ነበርን" ትላለች።

ለወላጆቿም ዜናውን የነገረቻቸው ልትወልድ አንድ ወር ተኩል ሲቀራት ነበር። ቤተሰቦቿ በጣም ነው የተደናገጡት።

ለእርግዝናዋ እንድትዘጋጅ ወደ ቤቷ እንድትመለስ ማሳመን ብቻ ሳይሆን ከፍቅረኛዋ አጂት ጋር እንዳትገናኝ ከለከሏት።

አኑፓማ ልጇን ተገላግላ ከሆስፒታል ስትወጣ ወላጆቿ እሷንና ልጅዋን ወደ ቤት ሊወስዱ መጡ።

ለጊዜው በዘመድ ቤት እንድትቆይና ሦስት ወር የቀረው የእህቷ ሠርግ ሲጠናቀቅም እንድትመለስ ነገሯት። ይህንንም የሚያደርጉት ለሠርግ የሚመጣው ወዳጅ ዘመድ ስለ አዲሱ ልጅ እንዲጠይቁ ባለመፈለጋቸው መሆኑንም አስረዷት።

አኑፓማ "ልጄን ስጡኝ" የሚል የተፃፈበት ፖስተር ይዛ

የፎቶው ባለመብት, Vivek Nair

የምስሉ መግለጫ, አኑፓማ "ልጄን ስጡኝ" የሚል የተፃፈበት ፖስተር ይዛ

አኑፓማ እንደምትናገረው ልጇን አባቷ ከሆስፒታል እንደወጡ በመኪና ሌላ ቦታ ወሰዱት። "ልጁን በኋላ ላገኘው ወደምችልበት ቦታ ደኅንነቱ የተጠበቀ ቦታ እየወሰደው እንደሆነ ነግሮኛል" ትላለች።

"ለጥቂት ጊዜ የደስታ ምንጬ የነበረው ልጄ ጠፋ" በማለት ታስረዳለች።

በቀጣዮቹ ጥቂት ወራት በሁለት ቤቶች መካከል በማፈራረቅ እንድትኖር ሲያመላልሷት የነበረ ሲሆን በመጨረሻም ከከተማዋ 200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኘው አያቷ ቤት ወሰዷት።

የእህቷን ሠርግ ለመታደም ወደ ከተማ ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ስትመጣም ልጇን ልታገኘው አልቻለችም፤ አጂትንም ደውላ ልጃቸው እንደጠፋ ነገረችው።

ቤተሰቦቿ ልጃቸውን ለማደጎ እንደሰጡትም አወቀች። ቤተሰቦቿንም ማየት አልፈልግም ብላ ከአጂትና ከቤተሰቦቹ ጋር መኖር ጀመረች። ልጃቸውንም መፈለግ ጀመሩ። ፍለጋው ቀላል አልነበረም፤ በበርካታ ውጣ ውረዶች የተሞላ ነበር።

ሆስፒታልም ሄደው የልጃቸውን የልደት የምስክር ወረቀት ሲያወጡ የሰፈረው የአባት ስም አጂት ሳይሆን የማያቁት ሰው ስም እንደሆነ አረጋግጠዋል።

በመጀመሪያም ልጃችን ጠፍቷል ብለው ሊያስመዘግቡ ሲሄዱ ፖሊስ ለመስማት ፈቃደኛ አልሆነም።

በተቃራኒው አባቷ አኑፓማ ከወላጆቿ ቤት "መጥፋቷን" አስመልክቶ ያቀረበውን ክስ እየመረመሩ እንደሆነ ነገሯት። በነሐሴ ወር ላይ ጭራሹኑ ፖሊስ ለጥንዶቹ አስገራሚ ነገር ነገሯቸው።

አባቷ አኑፓማ ልጁን ለማደጎ በገዛ ፍቃዷ አሳልፋ እንደሰጠች ነግረውናል አሏቸው።

በሁኔታው የተጨነቁት ጥንዶች ለገዥው ፓርቲ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለጉዲፈቻ ኤጀንሲ እና ለግዛቲቱ ፖሊስ ኃላፊ ቅሬታቸውን ላኩ።

በተጨማሪም የግዛቲቱ የባህል ሚኒስትር ሳጂ ቼሪያን "ወላጆቿ ሁሉም ሰው የሚያደርገውን አድርገዋል" ብለው ለአንድ የዜና ጣቢያ ከተናገሩ በኋላ የአኑፓማን ስም አጥፍተዋል በሚል ለፖሊስ ቅሬታ አቅርበዋል።

የአኑፓማ አባት
የምስሉ መግለጫ, የአኑፓማ አባት

ባለፈው ወር፣ አኑፓማ እና አጂት ሚዲያዎች ላይ ቀርበው ታሪካቸውን ተናገሩ።

በዚያን ወቅትም ነው የአገሪቱን ፖለቲከኞችና ባለሥልጣናትን ትኩረት የሳቡት። የተቃዋሚ ፓርቲ አባል የሆኑት የሕግ አውጪ ኬኬ ራማ በክልሉ ምክር ቤት ቀርበው "በአገሪቱ ውስጥ እንደ ክብር ወንጀሎች ከሚታዩት አንዱ ይህ ነው" ብለዋል።

አክለውም "በመንግሥት መዋቅሮች በጋራ የተፈፀመ የክብር ወንጀል" ብለውታል።

የአኑፓማ አባት ኤስ ጄያቻንድራን በበኩላቸው ድርጊታቸው ልክ እንደሆነ ተከላክለዋል።

"እንዲህ አይነት ነገር በቤታችን ውስጥ ሲከሰት እንዴት እናድርገው? ህፃኑን አኑፓማ በፈለገችበት ቦታ ነው የተውኩት። ልጁን ለመንከባከብና ለመጠበቅ አትችልም ነበር። እኛም ልንጠብቀው አንችልም" ሲሉ ለዜና ወኪሎች ተናግረዋል።

"አኑፓማ የሕፃኑ አባት ሚስት ያለው ሰው ነው ብላኛለች። ይህንን እየነገረችኝ ልጄንና ልጇን እንዴት ከእሱ ጋር አብሬ ልተዋቸው እችላለሁ? አኑፓማ ከወለደች በኋላ ጥሩ ጤንነት ላይ አልነበረችም። ስለዚህ ልጁን እንዲንከባከቡት ለጉዲፈቻ ኤጀንሲ አደራ ሰጥቼዋለሁ" ብለዋል።

ጄያቻንድራን ቤተሰቡ እንዴት "ሕገወጥ ልጅ" ማቆየት ይቻለዋል ሲሉ ይጠይቃሉ። ህፃኑንም ለጉዲፈቻ ኤጀንሲ አሳልፈው የሰጡት የኮሚዩኒስት ፓርቲውንና የሕግ ባለሙያውን ምክር ከተቀበሉ በኋላ እንደሆነ አስረድተዋል።

የቴሌቪዥን አቅራቢው ለልጃቸው የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ ሲጠይቃቸውም "ከእሷ ምንም መስማት አልፈልግም" ብለዋል።

በርካቶች ቁጣቸውን ማሰማታቸውን ተከትሎ ፖሊስ የአኑፓማ ወላጆችን ጨምሮ በእህቷ፣ በእህቷ ባለቤት ወንድም በአጠቃላይ በስድስት ሰዎች ላይ ክስ መስርቷል። ክሱም አፈና፣ ጠለፋ እና ማጭበርበር የሚል ሲሆን ሁሉም ክሱን አስተባብለዋል።

አኑፓማ ከልጇ ጋር ከቀናት በፊት

የፎቶው ባለመብት, Vivek Nair

የምስሉ መግለጫ, አኑፓማ ከልጇ ጋር ከቀናት በፊት

ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ከተመራም በኋላ ፍርድ ቤቱ ፕራዴሽ ግዛት ለሚኖሩ ጥንዶች በጉዲፈቻ ኤጀንሲው አማካኝነት የተሰጠውን ህፃን የዲኤንኤ (ዘረመል) ምርመራ እንዲደረግ አዘዘ።

ህፃኑም አሳዳጊ ወላጆቹ ከሚኖሩበት ፕራዴሽ ግዛት ወደ ትሪቫንድረም ግዛት እንዲዛወር ተደረገ።

በቅርቡም አኑፓማ እና አጂት ዲኤንኤያቸው ከህፃኑ ጋር እንደሚመሳሰል ተነገራቸው። ልጃቸውንም በጊዜያዊነት በነበረበት በበጎ አድራጎት ድርጅት የሚተዳደር የልጆች መኖሪያ ቤት ውስጥ ለአጭር ጊዜ አዩት።

ሕፃኑን በሕገወጥ መንገድ በማዘዋወር ወንጀል ኃላፊነት ያለባቸው ግለሰቦች እስኪቀጡ ድረስ ተቃውሟቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

ፍርድ ቤቱም የዲኤንኤ ማስረጃውን ከመረመረ በኋላ ሕፃኑን በያዝነው ሳምንት ረቡዕ ለወላጆች አስረክቧል።

በጣም አስቸጋሪ ዓመት ነው ይላሉ ጥንዶቹ። አኑፓማ አሁን ከአንድ ዓመት በላይ ስለሆነው ልጇ ያለማቋረጥ ተጨንቃለች።

"ከማን ጋር መኖር እና ልጅ መውለድ እንዳለብኝ መምረጥ መብቴ አይደለም?" በማለትም ትጠይቃለች።