ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ወደ ሥልጣናቸው ተመለሱ

አብደላ ሀምዶክ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ጥቅምት ወር ላይ በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣናቸው የተወገዱት የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ወደ ሥልጣናቸው መመለሳቸው ተገለጸ።

በቤታቸው ውስጥ በቁም አስር ላይ የሰነበቱት ሐምዶክ ከመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ ጄነራል አብደል ፋታህ አል ቡርሐን ጋር አዲስ የሥልጣን መጋራት ስምምነት ለመፈራረም ዛሬ እሁድ በአገሪቱ ቴሌቪዥን ቀርበው ታይተዋል።

ከሁለት ዓመት በፊት አብደላ ሐምዶክን ለጠቅላይ ሚኒስትርነት የሾመው የሲቪል ፖለቲከኞች ስብስብ ግን ከወታደሮች ጋር የሚደረግን ማንኛውንም አይነት አዲስ ስምምነት እንደማይቀበለው አሳውቋል።

"የሱዳን የወደፊት ዕጣ የሚወሰነው በአገሪቱ ውስጥ ባሉ ወጣቶች ነው" ሲል የነጻነትና የለውጥ ኃይሎች የተባለው ጥምረት ቃል አቀባይ የሆነው ሲዲቅ አቡ ፋዋዝ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ከመፈንቅለ መንግሥቱ መካሄድ በኋላ የተቀሰቀሰውና ለበርካታ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው ተቃውሞ እንደቀጠለ ነው።

በዋና ከተማዋ ካርቱም ጦር ሠራዊቱ ከአገሪቱ ፖለቲካ ሙሉ ለሙሉ እንዲወጣ የሚጠይቁ ሰልፈኞች ወደ ፕሬዝዳንታዊው ቤተመንግሥት በሚያመሩበት ጊዜ የፀጥታ ኃይሎች አስለቃሽ ጋዝ እንደተኮሱባቸው ተዘግቧል።

በጥቅምት ወር አጋማሽ ላይ ሠራዊቱ መፈንቅለ መንግሥት አካሂዶ የሲቪል አስተዳደሩን አመራሮች ከበተነና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከደነገገ በኋላ መፈንቅለ መንግሥቱን ተቃውመው አደባባይ ከወጡ ሰዎች መካከል ቢያንስ 40 የሚሆኑ ሰዎች ተገድለዋል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው አብደላ ሐምዶክ "የሱዳናውያን ደም ውድ ነው፣ ደም መፋሰሱን እስቁመን ወጣቱን ኃይል ወደ ግንባታና ልማት እንምራው" በማለት ግጭቶች እንዲቆሙ ከስምምነት መድረሳቸውን ተናግረዋል።

ወደ ሥልጣን የተመለሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዶክና ሲቪል ሚኒስትሮቻቸው ምን ያህል ሥልጣን እንደሚኖራቸው ግን ግልጽ አይደለም።

ከሥልጣናቸው የተወገዱት ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ መንበራቸው እንዲመለሱ የተደረገው የሱዳን ጦር፣ ሲቪል መሪዎች እንዲሁም የቀድሞ አማጺያን ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ ነው ሲሉ አሸማጋዮች አስታውቀዋል።

ይህ ስምምነት ቅዳሜ ምሽት የተደረሰ ሲሆን እሁድ ከሰዓት በኋላ ነው ተግባራዊ የተደረገው።

ምሁራን፣ ጋዜጠኞች እንዲሁም ፖለቲከኞች የተካተቱበት አሸማጋይ ቡድን የስምምነቱን ይዘት ለሕዝብ ይፋ አድርጓል።

ይዘቱ እንደሚያትተው በቁጥጥር ሥር የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክና የካቢኔ አባሎቻቸው ይለቀቃሉ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደግሞ ወደ ሥልጣናቸው ይመለሳሉ።

አክሎም ሱዳን ወደ ዲሞክራሲ የምታደርገው ሽግግር እንደሚቀጥል ይዘቱ ያትታል።

የሱዳን ሲቨል መሪዎችና የአገሪቱ ጦር ላለፉት ሁለት ዓመታት በሥልጣን ክፍፍል ሳቢያ እሰጥ-አገባ ውስጥ ነበሩ።

የሱዳን ጦር ወደ ሥልጣን የመጣው ለረዥም ዓመታት ሱዳንን የመሩት ፕሬዝደንት ኦማር አል-ባሽር ከመንበራቸው ከተወገዱ በኋላ ነው።

አገሪቱን በጋራ ለመምራት ሥልጣን የተረከቡት ወታደራዊው ኃይልና የሲቪሉ መንግሥት በበርካታ ጉዳዮች ሊስማሙ አልቻሉም ነበር።

ባለፈው ወር የጦር ኃይል ጄኔራል የሆኑት አብደል ፋታህ አል ቡርሐን ሲቪሉን መንግሥት መበተናቸውንና ባለሥልጣናቱን በቁጥጥር ሥር ማዋላቸው ይታወሳል።

ጄኔራሉ ክስተቱ "መፈንቅለ መንግሥት አይደለም የእርስ በርስ ጦርነትን ለማስቀረት እንጂ" ካሉ በኋላ አዲስ ምክር ቤት አቋቁመው ራሳቸውን የበላይ አድርገው ሾመው ነበር።

ከዚህ የፖለቲካ ውጥንቅጥ በኋላ ዋና ከተማዋ ካርቱምን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሕዝባዊ አመጽ የተቀጣጠለ ሲሆን ይህንንም ለመመከት የተሰማራው የአገሪቱ ጦር ሰልፈኞች ላይ ተኩሷል ተብሎም ተወቅሷል።

ሱዳናዊያን ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ እሑድ ቀነ ቀጠሮ ይዘው ሰልፍ ከመውጣታቸው በፊት ነው ስምምነቱ ይፋ የሆነው።

ወታደራዊው መንግሥት ከመፈንቅለ መንግሥቱ በኋላ አገሪቱን ወደ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር እንዲመልሳት ከባድ ጫና ሲደረግብት የቆየ ሲሆን፤ የአፍሪካ ሕብረት አገሪቱን ከአባልንት ሲያግድ የዓለም ባንክ ደግሞ ለሱዳን ሊሰጥ ያቀደውን ድጋፍ አግዷል።

ኦማር ሐሰን አል ባሽር ከሥልጣን ተወግደው የሽግግር አስተዳዳር ከተመሰረተ በኋላ በሠራዊቱ መሪዎችና በሲቪል ባለሥልጣንት መካከል አለመግባባት የቆየ ሲሆን፤ በዚህ ወር አል ቡርሐን ሥልጣናቸውን ለሲቪል መሪ ያስርክባሉ ተብሎ ሲጠበቅ ነው መፈንቅለ መንግሥት ያካሄዱት።