ከጉንፋን መሰል ሕመሞች ግማሹ ኮሮናቫይረስ ሊሆኑ እንደሚችሉ ባለሙያዎች አስጠነቀቁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጉንፋን ሲይዝዎ የሚሰማዎት ዓይነት ሕመም ከተሰማዎ በሽታው ኮሮናቫይረስ ሊሆን የሚችልበት ዕድም ሰፊ እንደሆነ ባለሙያዎች ገለጹ።
ጉሮሮ መከርከር፣ ራስ ምታት እና የአፍንጫ ፈሳሽ ምልክቶች ከሚታዩባቸው ሰዎች ከፊሉ ኮሮናቫይረስ እንዳለባቸው የጠቆሙት የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ባለሙያዎች ናቸው።
ዞይ የተባለው የዩኬ የኮቪድ-19 የጥናት ማዕከል ባደረገው ዳሰሳ መሠረት፤ ጉንፋን መሰል ምልክት ካሳዩ ሰዎች ግማሹ በወረርሽኙ መያዛቸውን ጠቁሟል።
ባለፈው ሳምንት በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እጅጉን ጨምሯል። ምክንያቱም አዲሱ የኦሚክሮን ዝርያ በስፋት መሰራጨቱ ነው።
በቀን 144,000 ሰዎች በኦሚክሮን እየተያዙ እንደሆነ ተገልጿል።
አብዛኞቹ ሕሙማን የተወሰነ ምልክት ሲያሳዩ፤ ምንም ምልክት የማያሳዩም አሉ።
ቫይረሱ ከሚጠናባቸው መካከል በዋነኛነት የሚጠቀሱት ክትባት ያልወሰዱ ናቸው።
የጉንፋን ምልክት ከታየብዎት ኮሮናቫይረስ እንዲመረመሩ ባለሙያዎች ይመክራሉ።
የዩናይትድ ኪንግደም እውቅ ሳይንቲስት ፕሮፌሰር ቲም ስፔክተር እንደሚሉት፤ ኦሚክሮን ከያዛቸው ሰዎች አብዛኞቹ ጉንፋን የያዛቸው ይመስላቸዋል።
ባለፈው ሳምንት በአገራቸው በአንድ ቀን ብቻ 106,122 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል።
በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በመጨመሩ ሳቢያ የጤና ሥርዓቱ እንዳይናጋ ተፈርቷል።
ኦሚክሮን ከመጀመሪያው የኮሮናቫይረስ ዝርያ አንጻር እምብዛም ለከፋ ሕመም አያጋልጥም። በኦሚክሮን ተይዘው ከፍተኛ ሕክምና ያስፈለጋቸው ሰዎችም ውስን ናቸው።
ሆኖም ግን ብዙ ሰዎች ሲታመሙ የሆስፒታል አልጋ የሚሹ ሕሙማን ቁጥር መናሩ አይቀርም።
ካለፈው ወር ወዲህ ወደ 1.3 ሚሊዮን ዜጎች ዩኬ ውስጥ በቫይረሱ ተይዘዋል። ይህም እስካሁን በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛው ነው።












