በአውስትራሊያ በአፍንጫ የሚወሰድ የኮቪድ-19 መከላከያ ላይ ሙከራ እየተደረገ ነው

የፎቶው ባለመብት, MONASH UNIVERSITY
የደም መርጋት ሲያጋጥም ጥቅም ላይ የሚውለው መድኃኒት (blood thinner) ኮሮናቫይረስን ለመከላከል እንዲውል የአውስትራሊያ አጥኚዎች ምርምር እያደረጉበት ይገኛሉ።
ሙከራ የተደረገበት መድኃኒት በአፍንጫ የሚሳብ (nasal spray) ነው።
አጥኚዎቹ እንዳሉት፤ መድኃኒቱ የኮሮናቫይረስ የፕሮቲን መጠን እንዳይጨምር በማድረግ የበሽታውን ስርጭት ይከላከላል ተብሎ ይታመናል።
በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች በአፍንጫቸው መድኃኒቱን ሲወስዱ በሽታውን ማስተላለፍ ማቆማቸውን ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል።
ሙከራው እአአ በ2022 አጋማሽ ነው የሚጠናቀቀው። ውጤታማ ከሆነ ለክትባት አጋዥ ይሆናል።
ይህ ዘዴ በቫይረሱ የተያዘን ሰው ለማከም እንዲሁም በአፍንጫ ከተወሰደ በኋላ ቫይረሱን ለመከላከለም እንደሚውል ተጠቁሟል።
የምርምሩ መሪ ፕ/ር ዶን ካምቤል "መድኃኒቱ ሰው በሚበዛበት አካባቢ ለሚሆኑ ሰዎች ይረዳል" ብለዋል።
ሰዎች ወደ መደብር ወይም ሌላ ቦታ ከመሄዳቸው በፊት መድኃኒቱን አፍንጫቸው ላይ ነፍተው ከቤታቸው መውጣት እንደሚችሉ ፕሮፌሰሩ ያስረዳሉ።
በሌሎች አገሮችም በአፍንጫ የሚወሰዱ መድኃኒቶች ላይ ምርምር እየተደረገ ሲሆን፤ የአውስትራሊያውን ልዩ የሚያደርገው ኸፕሪን ከተባለው የደም መርጋት መድኃኒት መሠራቱ ነው።
ኸፕሪን በአፍንጫ ሲወሰድ ወደ ደም ሳይገባ አፍንጫ ላይ ይቆያል። ስለዚህም ቫይረሱ ወደ ሰውነት እንዳይገባ ይከላከላል።
ሙከራው ከመንግሥት 3 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ተደርጎለት በ400 ኮሮናቫይረስ የያዛቸው ሰዎች ያሉባቸው ቤቶች ይተገበራል ተብሎ ይጠበቃል።
እያንዳንዱ ሰው በቀን ሦስት ጊዜ መድኃኒቱን በአፍንጫው ይስባል።
ሙከራ በሚደረግባቸው ቤቶች መድኃኒቱ የቫይረሱን ስርጭት መግታት አለመግታቱ ይፈተሻል።
በሙከራው ከሚሳተፉት መካከል ሜልበርን ዩኒቨርስቲ፣ ሞናሽ ዩኒቨርስቲ፣ ሜልበርነስ ኖርዘን ኸልዝ፣ ፒተር ዶርቲ ኢንስትቲትዩት፣ መርዶክ ችልድረንስ ሪሰርች እና ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ይገኙበታል።
የምርምሩ ተሳታፊ ፕሮፌሰር ሚቼል መክቶስ እንዳሉት፤ ኸፕሪን ለታካሚዎች እንዲሰጥ ፈቃድ ተሰጥቶት በስፋት ገበያ ላይ የሚገኝ መድኃኒት መሆኑ ጥናቱን ያፋጥነዋል።
ፕሮፌሰር ዶን በበኩላቸው በአፍንጫ የሚወሰደውን መድኃኒት ላለፉት 20 ወራት እንደተጠቀሙትና ምንም ዓይነት የጎንዮሽ ጉዳት እንዳላስከተለባቸው ገልጸዋል።
ጨምረውም "መድኃኒቱ ውጤታማ ይሆናል ብለን እናምናለን" ብለዋል።












