ኮቪድ-19፡ በቻይና ዢያን ከተማ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በመጨመሩ የእንቅስቃሴ ገደብ ተጣለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቻይና ውስጥ ዢያን በተባለች ከተማ የተቀሰቀሰውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመግታት በከተማዋ የሚኖረው ከ13 ሚሊየን በላይ ሕዝብ ከቤቱ እንዳይወጣ ጥብቅ ገደብ ተጣለ።
በአገሪቷ ሰሜናዊ ክፍል የምትገኘው ከተማ ባለፉት 14 ቀናት ብቻ 143 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን መዝግባለች።
በዚህ ረቡዕ ዕለት ይፋ በተደረገው አዲስ ገደብ መሠረት ከአንድ ቤት በየሁለት ቀኑ አንድ ሰው ብቻ አስፈላጊ ዕቃዎችን ለመግዛት ወደ ገበያ እንዲወጣ ይፈቀድለታል።
'ቴራኮታ ዋሪየርስ' በመባል የሚታወቁት የዢያን ነዋሪዎች አስቸጋሪ ሁኔታ ካልገጠማቸው አሊያም ከመንግሥት ፈቃድ ካላገኙ በስተቀር ከተማዋን ለቀው እንዲወጡ አይፈቀድላቸውም።
የተጣሉት ገደቦች ሐሙስ ሌሊት ጀምሮ ተግባራዊ መደረግ የሚጀምሩ ሲሆን ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆዩ ግን አልታወቀም።
ቻይና ሰፊ ምርመራ በማካሄድና የእንቅስቃሴ ገደብ በመጣል የኮቪድ-19 ሥርጭትን ሙሉ በሙሉ ለማስቆም ጥብቅ መመሪያን የምታስፈጽም አገር ናት።
ከሁለት ወር በኋላ በየካቲት 2022 የሚካሄደውን የክረምት ኦሊምፒክን ለማዘጋጀትም አገሪቷ በተጠንቀቅ ላይ ትገኛለች።
ዢያን ከተማ በምትገኝበት ሻንዚ ግዛት በሚሊየን የሚቆጠሩ ምርመራዎች ተካሂደዋል።
ረዥም ርቀት የሚጓዙ የአውቶብስ ጣቢያዎች የተዘጉ ሲሆን ወደ ከተማዋ የሚገቡ አውራ ጎዳናዎች ላይ የፍተሻ ኬላዎች ተቋቁመዋል። ከዢያን አየር ማረፊያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው በረራዎችም ተሰርዘዋል።
አንገብጋቢ ያልሆኑ የንግድ ተቋማትም የተዘጉ ሲሆን የመንግሥት ሠራተኞች ከቤት ሆነው እንዲሰሩ ተነግሯቸዋል።
ባለፈው የሳምንቱ መጨረሻ ባለሥልጣናት ለጥንቃቄ በሚል በቤት ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡ እንደ መጠጥ ቤቶች፣ የስፖርት ቤቶች፣ የፊልም ማሳያ ቤቶች እና የመሳሰሉት እንዲዘጉ ማድረጋቸውን ግሎባል ታይምስ የተባለው የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።
ባለሥልጣናት የተከሰተው የኮቪድ-19 ዝርያ 'ዴልታ' የተሰኘው እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፤ አዲሱን የቫይረስ ዝርያ ኦሚክሮንን አልጠቀሱም።
የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት በሺያን ከተማ ሌላም ለሞት የሚዳርገውና የደም ቧንቧዎችን የሚጎዳው 'ሄሞርሃጂክ' የተሰኘ በሽታ የተከሰተ ሲሆን ከተማዋ ሁለት ወረርሽኞችን እያስተናገደች ነው።
ኢቦላን በሚያስከትለው የቫይረስ ቤተሰብ ሳቢያ የሚከሰተው 'ሄሞርሃጂክ' በሰሜን ቻይና ከወቅት ጋር ተያይዞ በተለይ በገጠር አካባቢ የሚከሰትና የተለመደ በሽታ ነው።
ቻይና ኮቪድ -19 ለምታስተናግደው የክረምት ኦሊምፒክ ከፍተኛ ተግዳሮት እንደሆነባት ገልጻለች።
የኮሮናቫይረስ ለመጀመሪያ ጊዜ በተመዘገበባት ቻይና እስካሁን 113 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 4 ሺህ 849 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል።












