ኦሚክሮን፡ በፍጥነት በሚዛመተው አዲሱ የኮቪድ ዝርያ የሚያዙ ሰዎች ምን ይሆናሉ?

Omicron

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

እንሆ ሁለት ትላልቅ ጥያቄዎች፡ ኦሚክሮን በምን ያህል ፍጥነት ሊዛመት ይችላል? በኦሚክሮን ዝርያ የሚያዙ ሰዎች ምን ይሆናሉ?

እኒህን ሁለት ጥያቄዎች መልስ አገኘንላቸው ማለት ኦሚክሮን የተሰኘው አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ምን ያህል አደገኛ ነው የሚለውን መለስን ማለት ነው።

የምድራችን ሳይንቲስቶች እኒህን ጥያቄዎች ለመመለስ ደፋ ቀና እያሉ ነው። ትንሽ ፍንጭ የሚሰጥ ነገር ያገኙም ይመስላል።

የመከላከል አቅም በጣም አስፈላጊ ነው። ኦሚክሮን ሁሉን ነገር ወደኋላ መልሶ እንደአዲስ እንድንድህ ሊያደርገን ነው ባይባልም አዲሱ የኮቪድ ዝርያ ምን ያህል አስጊ ነው የሚለውን መመልስ ጥቂት ሳምንታትን ሊጠይቅ ይችላል።

ኦሚክሮን በምን ያህል ፍጥነት እየተዛመተ ይሆን?

መልሱ "በፍጥነት" የሚል ነው።

ይህ ዝርያ በክትባትም ይሁን በርካታ ሰዎች በመያዛቸው ምክንያት የተሻለ የመከላከል አቅም አዳብረዋል በሚባሉ ሥፍራዎችም በፍጥነት እየተስፋፋ ይገኛል።

ለምሳሌ ደቡብ አፍሪካ ከአንድ ወር በፊት ዴልታ ከተሰኘው የኮቪድ ዝርያ ጋር ተላምዳ በቀን የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 300 ወርዶ ነበር። አሁን ግን አራተኛው የኮቪድ ማዕበል ከ10 ሺህ በላይ ሰዎችን አዳርሷል።

ዩናይትድ ኪንግደምም ብትሆንም ኦሚክሮን እንደሰደድ እሣት እየተዛመተባት ይገኛል።

ሳይንቲስቶች የኦሚክሮንን ዱካ እያገኙ ያሉት ዝርያው የኮቪድ ምርመራ በሚደረግበት ወቅት ትቶ በሚያልፋቸው አሻራዎች አማካይነት ነው።

ይህ አሻራ ኤስ-ጂን ይሰኛል። ይህ ከኮቪድ ምርምራ ላይ የሚገኝ ቅንጣት ባለፈው ወር መጨረሻ ወደ 0.1 በመቶ ወርዶ ነበር። አሁን ግን ወደ 5 በመቶ አድጓል። ይህ በቁጥር ሲገለጥ በቀን 2500 ሰዎች በአዲሱ ዝርያ ይያዛሉ ማለት ነው።

ይህ ስሌት ሙሉ በሙሉ ትክክል ነው ማለት ባይቻልም በአራተኛው የኮቪድ ማዕበል የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ማሻቀቡ የማይታበይ ሐቅ ነው።

ለምሳሌ በዩናይትድ ኪንግደም የኦሚክሮን ቁጥር በየሦስት ቀኑ እጥፍ እየሆነ እንደሚሄድ መረጃዎች ጠቋሚ ናቸው።

ኦሚክሮን የሚዛመትበት ፍጥነት ዴልታ ከተሰኘው ዝርያ በላይ ሲሆን ኮሮናቫይረስ ባለፈው ዓመት መባቻ ሲጀምር ሲስፋፋ የነበረውን ዓይነት ፍጥነት እንዳለው ተደርሶበታል።

በዚህ ፍጥነቱ መዛመቱን ከቀጠለ በቀን 2500 የነበረው ቁጥር ከአንድ ወር በኋላ በቀን 100 ሺህ ይሆናል ማለት ነው።

እኔን ይይዘኝ ይሆን? በሽታው ምን ያህል ከባድ ነው?

ሳይንቲስቶች እስካሁን ድረስ ባደረጉት ጥናት ጭንቀት ውስጥ የከተተታቸው የኦሚክሮን ዝርያ የኮቨድ ክትባትን የመቋቋም አቅሙ ነው። ኦሚክሮን አሠራሩ ክትባቱ እንዲከላከል ከተሠራለት የመጀመሪያው የኮቪድ ዝርያ ለየት ያለ ነው።

ጥናቶች እንደሚጠቁሙት የኮቪድ ክትባት ሁለት ጊዜ የወሰዱ ሰዎች አዲሱን ዝርያ የመከላከል አቅማቸው ከ20 እስከ 40 እጥፍ ሊቀንስ ይችላል።

እርግጥ ነው እስካሁን በአዲሱ ዝርያ ዙሪያ አጠንጥነው የተሠሩ ጥናቶች ቁጥር ትንሽ ነው። ነገር ግን እኒህ ጥናቶች የአዲሱን ዝርያ የመዛመት ኃይል የሚያሳዩ ናቸው።

ቢሆንም ስለ አዲሱ ዝርያ መልካም ዜናም አልጠፋም። ፋይዘር-ባዮንቴክ የሠራው ሙከራ እንደሚያመለክተው ማጠናከሪያ ክትባት [ሦስተኛ ክትባት] የወሰዱ ሰዎች ኦሚክሮንን የመከላከል አቅማቸው ከፍ ይላል።

ለኦሚክሮን ሦስት ዙር መከተብ ማለት ለዋናውና የቀደመው ቫይረስ ሁለት ዙር እንደመከተብ ማለት ነው።

የኤደንብራ ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ኤሌኖር ራይሊ ይህን ሙከራ "አበረታች" ሲሉ ይገልፁትና "ማጠናከሪያው ክትባት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ የሚያሳይ ነው" ይላሉ።

ኦሚክሮን ምን ያህል ከባድ የኮሮናቫይረስ ዝርያ እንደሆነ ግን እስካሁን የምናውቀው ጥቂት ነው። በዝርያው ተይዘው ሆስፒታል የገቡ ሰዎች ጥናት እስኪደርግባቸው ድረስ ስለበሽታው ኃያልነት ያለው እውቀት እፍኝ አይሞላም።

እርስዎ ሁለት ጊዜ ክትባት ወሰዱ ማለት አሊያም ከዚህ በፊት ኮቪድ ይዞዎት ነበር ማለት ኦሚክሮንን የመከላከል አቅምዎ የተሻለ ነው ይላሉ ሳይንቲስቶች።

እና ወደፊት ምን ሊሆን ይችላል?

ኮሮናቫይረስን እንዲከላከሉ ተብለው የተዘጋጁት ክትባቶች ኦሚክሮንን ሊከላከሉ እንደሚችሉ ግምት አለ።

ነገር ግን አብዛኛዎቻችን ጤና ብንሆን እንኳ ሁላችንም ደህና ላንሆን እንችላለን። አንዳንድ ሰዎች የመከላከል አቅማቸው እጅግ የደከመ ነው። አንዳንዶች ቢከተቡም ላይከላከሉ ይችላሉ። አንዳንዶች ክትባት መውሰድ አይችሉ ይሆናል። አንዳንዶች ደግሞ በውዴታ ክትባት አንወስድም እያሉ ነው።

በዴልታ ቫይረስ የተጠቁ ሰዎች ሆስፒታል እስከመግባት ደርሰዋል። አዲሱ ዝርያ ብዙ ሰዎች በአንድ ጊዜ ወደ ሆስፒታል እንዲገቡ ካደረገ ችግር ሊፈጠር ይችላል።

የዋርዊክ ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ማይክል ቲልደስሊ "ማዕበል ትልቅ ከሆነ ባለፈው ጥር እንደተመለከትነው ዓይነት ሊሆን ይችላል። ሆስፒታሎችም ሊጨናነቁ ይችላሉ" ባይ ናቸው።

ነገር ግን አሁን ያለን መረጃ ጥቂት ስለሆነ ይህ ነው ብሎ መናገር እንደሚከብድ ያስረዳሉ።

የዓለም ሳይንቲስቶች የተስማሙበት ይህ ነው የሚባል ኦሚክሮን እየተዛመተበት ያለ ፍጥነት የለም። በሽታው ምን ያህል ከባድ ሊሆን እንደሚችልም በውል አይታወቅም። ክትባቱን ሊፈታተነው ይችላል ወይ የሚለውም ምላሽ አላገኘም።

ማድረግ የሚቻለው ራስን ከበሽታው እየጠበቁ በቀጣይ ሳምንታት የሚሆነውን በቅርበት መከታተል ነው።