በቀጣይ በዓለም ላይ የሚከሰቱ ወረርሸኞች ከኮቪድ በላይ ገዳይ ሊሆኑ ይችላሉ ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዓለማችን ከዚህ በኋላ የሚከሰቱ ወረርሽኞች ከኮሮረናቫይረስ በላይ የከፉ ገዳይ ሊሆኑ እንደሚችሉ የኦክስፎርድ አስትራዜኔካ ክትባትን ከፈጠሩት ተመራማሪዎች መካከል አንዷ ባለሙያ ተናገሩ።
ፕሮፌሰር ሳራህ ጊልበርት እንደሚሉት ወረርሽኞችን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ዝግጁነት ለመደገፍ መንግሥታት በቂ ድጋፍ ማድረግ ያለባቸው ሲሆን አሁን የተገኙ ስኬቶችንም ማስቀጠል አስፈላጊ ነው።
ፕሮፌሰሯ አክለውም ጥቅም ላይ እየዋሉ የሚገኙት ክትባቶች አዲሱን የቫይረስ አይነት ኦሚክሮን ለመከላከል ብዙም አቅም ላይኖራቸው እንደሚችልም ጠቁመዋል።
ስለአዲሱ ቫይረስ በቂ መረጃ እስከሚገኝ ድረስ ሰዎች በጥንቃቄ እንዲንቀሳቀሱም መክረዋል።
"ወረርሽኝ ሕይወታችንን እና አኗኗራችንን አደጋ ላይ ሲጥል ይህ የመጨረሻው የሚሆን አይመስለኝም። እውነታው ቀጣዩ ወረርሽኝ በጣም ከባድ ሊሆን እንደሚችል ነው። በፍጥነት የሚዛመት፣ በከፍተኛ ሁኔታ ገዳይ አልያም ሁለቱንም ያጣመረ ሊሆን ይችላል" ብለዋል።
"በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ያለፍነውን ችግር መርሳት የለብንም። ወረርሽኙ በምጣኔ ሀብታችን ላይ ያሳደረው ጫና ወደፊት የሚከሰቱ ወረርሽኞችን እንዳንቆጣጠር ሊያደርገን አይገባም'' ሲሉ ያሳስባሉ።
ፕሮፌሰር ሳራህ ጊልበርት ስለአዲሱ ኦሚክሮን ቫይረስ ሲናገሩ "አዲሱ ቫይረስ እራሱን አሻሽሎ ስለመጣ በክትባት መልክ ወይም በኮሮረናቫይረስ ስንያዝ የምናዳብረው በሽታ የመከላከል አቅም ብዙም ላይጠቅመን ይችላል" ብለዋል።
አክለውም ስለአዲሱ ቫይረስ በቂ መረጃ እስከሚገኝና ምርምሮች እስከሚደረጉ ድረስ ሰዎች ስርጭቱን ለመቀነስ ጥንቃቄ እንዲያደርጉና የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
በኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት የተገኘው ትምህርትና ክትባቶችን በፍጥነት የማድረስ ልማድ ሊቀጥል እንደሚገባ ያሳሰቡት ፕሮፌሰሯ ከዚህ በኋላ መሰል እርምጃዎች የተለመዱ መሆን አለባቸው ብለዋል።
የኦሚክሮን ስርጭትን ለመቆጣጠር እንዲቻል በማለት ቅዳሜ ዕለት ወደ ዩናይትድ ኪንግደም የሚጓዙ ሰዎች ከበረራቸው አስቀድመው የኮሮረናቫይረስ ምርምራ እንዲያደርጉ መንግሥት አሳስቧል።
በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) እስካሁን 246 ሰዎች በአዲሱ ኦሚክሮን መያዛቸው የተረጋተጠ ሲሆን ትናንት ዕሁድ ዕለት ብቻ 86 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን መንግሥት አስታውቋል።
ነገር ግን የዩኬን መንግሥት የሚያማክሩ አንድ ተመራማሪ የጉዞ እገዳውና ሌሎች መመሪያዎች የዘገዩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ፕሮፌሰር ማርክ ዉልሐውስ እንደሚሉት የመንግሥት ውሳኔ የዘገየ ሲሆን እዚህ ግባ የሚባል ለውጥ ያመጣል ብለው እንደማያምኑም ተናግረዋል።












