ከሥልጣን በመፈንቅለ መንግሥት የተነሱት አን ሳን ሱ ኪ የአራት ዓመት እስር ተፈረደባቸው

አንግ ሳን ሱ ኪ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣናቸው ተወግደው በእስር ላይ የሚገኙት አን ሳን ሱ ኪ የአራት ዓመት እስር ተፈረደባቸው።

የሚያንማር ፍርድ ቤት ሳን ሱ ኪ ግጭት በመቀስቀሳቸው እና የኮቪድ-19 ክልከላዎችን ተላልፈዋል በሚሉ ክሶች ጥፋተኛ ናቸው ብሏል።

ሳን ሱ ኪ 11 ክሶች የቀረቡባቸው ሲሆን በሁሉም ክሶች ጥፋተኛ አይደለሁም ብለው ተከራክረዋል።

የ76 ዓመቷ በአገሪቱ ጦር መፈንቅለ መንግሥት ተፈጽሞባቸው ከመንበረ ሥልጣናቸው ተነስተው ለእስር ከመዳረጋቸው በፊት በምርጫ የተመረጠ ሲቪል መንግሥት ይመሩ ነበር።

ጦሩ መፈንቅለ መንግሥቱን ያካሄድኩት ሳን ሱ ኪ አሸንፈዋል በተባለው ምርጫ የድምጽ ማጭበርበር ምልክቶችን በማስተዋሌ ነው የሚል ምክንያት ሰጥቶ ነበር።

line

ይህ በሳን ሱ ኪ ላይ የተላለፈው ፍርድ የተሰማው፤ ወታደራዊውን መንግሥት ለመቃወም አደባባይ በወጡ ሰዎች ላይ ጦሩ ሰዎችን በመኪና መግጨቱ ከተሰማ በኋላ ነው።

በሚያንማር የንግድ ማዕከል ያንጉን ወታደራዊ መኪና የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ የወጡ ሰዎች ላይ ወጥቶ በርካታ ሰዎችን ጎድቷል።

የዓይን እማኞች ለአገሪቱ መገናኝ ብዙኃን እንደተናገሩት መኪናው ጉዳት ካደረሰ በኋላ ወታደሮች በድንጋጤ እየሮጡ የነበሩ ሰልፈኞች ላይ ተኩስ ከፍተዋል፤ የተቀሩትንም ደብድበዋል።

ባለፈው የካቲት ከተካሄደው መፈንቅለ መንግሥት ጀምሮ 1200 ሰዎች በተቃውሞ ሰልፍ ላይ ሳሉ ተገድለዋል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ እሥር ቤት ገብተዋል።

የሚያንማር ጦር 11 ሰዎችን በቁጥጥር ሥር አውያለሁ ብሏል። ሦስቱ ሰዎች የተጎዱ ሲሆን አንድ ግለሰብ በሞትና ሕይወት መካከል ነው ያለው ተብሏል።

ጦሩ ወታደራዊ መኪና ተቃዋሚ ሰልፈኞች ላይ ስለመውጣቱ አስተያየት ባይሰጥም፤ "አመፀኞችን" መበተኑን ተናግሯል።

የወታደር መኪና ሰዎችን ገጭቷል የተባለበት ፀረ ወታደራዊ መንግሥት ተቃውሞ በዋና ከተማዋ ያንጉን እሑድ ዕለት ከተካሄዱ ሦስት ሰልፎች አንደኛው ነው።

የአገሪቱ ጦር ሰልፈኞች ላይ ጥይት ስለሚተኩስ ብዙውን ጊዜ ሰልፍ የሚካሄደው አነስ ባሉ ቡድኖች በመሰባሰብ ነው።

ሚያንማር

የፎቶው ባለመብት, ከማሕበራዊ ሚዲያ

የዓይን እማኞች እንዳሉት እሑድ ዕለት የተካሄደው ተቃውሞ በተጀመረ በደቂቃዎች ውስጥ ነው የተቋረጠው።

"ተመትቼ ከመኪናው ፊት ለፊት ወደቅኩ። አንድ ወታደር በዱላ ቢደበድበኝም እንደምንም ተከላክዬ ሩጫ ጀመርኩ። ነገር ግን ዚግዛግ ሠርቼ እየሮጥኩ ሳለ ተኮሰብኝ። እንደ ዕድል ሆኖ አመለጥኩኝ" ሲል አንድ ሰልፈኛ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግሯል።

የተባበሩት መንግሥታት የጦር ሠራዊቱ እየፈፀመ ያለው ተግባር በሰብዓዊነት ላይ የተፈፀመ ወንጀል ሊሆን ቢችልም ምርመራ ለማድረግ ወደ ሚያንማር ለመግባት ፈቃድ አለማግኘቱን ገልጧል።

የሚያንማር ጦር ባለፈው ዓመት የካቲት የተደረገውን መፈንቅለ መንግሥት ያደረግኩት የድምፅ ማጭበርበር ስላስተዋልኩ ነው ማለቱ አይዘነጋም። በወቅቱ ምርጫ ሚያንማርን ሲመሩ የነበሩት አንግ ሳን ሱ ኪ በሰፊ ውጤት አሸንፈው ነበር።

ገለልተኛ የምርጫ አጣሪዎች እንደሚሉት ምርጫ በአብዛኛው ነፃና ፍትሐዊ ነው፤ በሳን ሱ ኪ ላይ የተመሠረቱት ክሶችም ፖለቲካዊ ናቸው።

በዚህ ዓመት መባቻ በርካታ ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፎችን ሲያዘጋጁ የነበሩ አንቂዎች [አክቲቪስቶች] ተደብቀዋል፤ አሊያም በብሔር ተደራጅተው ነፍጥ አንስተው ድንበር አካባቢ ወታደራዊ ሥልጠና ከሚያደርጉ አማፅያን ጋር ናቸው።

በርካታ ታጣቂዎች በበርካታ ከተሞችና ገጠራማ ሥፍራዎች ከወታደራዊው መንግሥት ጋር አብረዋል ያሏቸውን ሰዎች ለማጥቃት ቦንብ አፈንድተዋል፤ ግድያዎች ፈፅመዋል።

ወታደራዊው አገዛዝ ደንበር አካባቢ በተለይ ደግሞ ከሕንድ ጋር በሚያዋስነው ሥፍራ ያሉ ታጣቂዎችን ለመዋጋት በሚል በርካታ ቤቶችን አቃጥሏል።