የማይሰሩ የሞባይል ስልኮች ለምንድን ነው ከአፍሪካ ወደ አውሮፓ የሚላኩት?

ኤሪክ አርተር

የፎቶው ባለመብት, ERIC ARTHUR

የምስሉ መግለጫ, ኤሪክ አርተር አብዛኛውን የሳምንቱን መጨረሻ ቀናት የሚያሳልፈው የተሰበሩ ተንቀሳቃሽ ስልኮችን በመሰብሰብ ነው።

ኤሪክ አርተር እዚህ ግባ የሚባል በትርፍ ጊዜ የሚያዝናናው ነገር የለም። አብዛኛውን የሳምንቱን መጨረሻ ቀናት የሚያሳልፈው በመላው ጋና በመዞር የተሰበሩ ተንቀሳቃሽ ስልኮችን በመሰብሰብ ነው።

በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ኬፕ ኮስት ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ እስከ 160 ኪሎሜትር ርቀት በመጓዝ ስልክ የሚጠግኑ ሱቆችን፣ ያረጁ እቃዎች መጣያዎችን እንዲሁም የተሰበሩ ስልኮችን ሊያገኝ የሚችልባቸውን ቦታዎች በሙሉ ይጎበኛል።

ጥሩ በሚባሉት ቀናት እስከ 400 የሚደርሱ ስልኮችን ይሰበስባል። በተጨማሪም ተመሳሳይ ሥራ የሚሰሩለት ስድስት ሰዎች በስሩ ያሉ ሲሆን፣ እነሱም በመላው አገሪቱ እየተንቀሳቀሱ በተመሳሳይ ያረጁና የተሰባበሩ ስልኮችን ይሰበስባሉ። ታዲያ በዚህ ዓመት በአጠቃላይ 30 ሺህ ስልኮችን ለመሰብሰብ አቅደዋል።

አርተር እና እሱ የቀጠራቸው ሰዎች ለሚሰበስቡት ስልክ ትንሽ ክፍያ ይፈጽማሉ። በአማካይ ለአንድ ሰልክ እስከ 44 ዶላር ድረስ ነው የሚከፍሉት።

ምንም እንኳን ስልኮቹ ተጠግነው ተመልሰው አገልግሎት ላይ መዋል የማይችሉ ቢሆን አንዳንድ ጊዜ ሰዎች የተበላሹ ስልኮቻቸውን እንዲሸጡ ማሳመን ከባድ እንደሆነ አርተር ይናገራል።

"አንድ አዲስ አንድሮይድ ስልክ እስከ 150 ዶላር ድረስ ሊሸጥ ይችላል። እኔ ደግሞ ስልኮቹ ከተበላሹ በኋላ በ1 ዶላር ልግዛችሁ እላቸዋለሁ። እነሱም 'በውድ ዋጋ ነበር እኮ የገዛሁት፤ እንዴት በትንሽ ገንዘብ ልሽጥልህ?' ይሉኛል። ነገር ግን ስልኩ ስለተበላሸ ከመጣል ውጪ ምንም አማራጭ የላቸውም።"

አርተር በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ለሚሰበስባቸው ስልኮች 'ክሎዚንግ ዘ ሉፕ' የተሰኘ የሆላንድ ኩባንያ ጠቀም ያለ ገንዘብ ይከፍለዋል።

ኩባንያው ደግሞ በአርተር እና ቡድኑ የሚሰበስቧቸውን ያረጁ ስልኮች ወደ አውሮፓ ይልካቸዋል። ተመልሰውም ጥቅም ላይ እንዲውሉ ይደረጋል።

አውሮፓ ያለው ድርጅት የስልኮቹን 90 በመቶ የሚሆነውን ብረት መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል ያደርጋል። ከፕላስቲክ ውጪ ማለት ነው።

ስልኮቹን በሺዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ወደምትገኘው አውሮፓ መላክ ለምን አስፈለገ?

የሆላንድ ኩባንያው መስራቾች መካከል አንዱ የሆነው ጁስት ዴ ክሉቬር እንደሚለው መልሱ በጣም ቀላል ነው።

በአፍሪካ አሁንም ድረስ እጅግ የተራቀቀ ቴክኖሎጂ የሚጠቀም ስልኮችን መልሰው ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚያደርግ ተቋም የለም። ከስልኮቹ የሚሰበሰቡት ብረቶች ደግሞ በጣም ውድና ተፈላጊ ናቸው።

"አፍሪካ ውስጥ ስልኮች መልሰው ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚያደርግ ድርጅት ማቋቋም በጣም ከባድ ነው። ለዚህ የሚረዳ መመሪያም ሆነ መሰረተ ልማት የለም። ሰዎችም ስለጉዳዩ ብዙ እውቀት የላቸውም" ይላል።

በሌላ በኩል 230 ሚሊየን የሚደርሱ ስልኮች በየዓመቱ አፍሪካ ውስጥ ይሸጣሉ።

ስልኮቹ አገልግሎት መስጠት ሲያቆሙ ደግሞ አንዳንዶቹ እንደ አርተር ባሉ ሰዎች የሚሰበሰቡ ሲሆን አብዛኛዎቹ ግን ይጣላሉ አልያም ቤት ውስጥ ይቀመጣሉ።

አንድ ዓለም አቀፍ ጥናት እንዳለመከተው አፍሪካ በአውሮፓውያኑ 2019 ብቻ 2.9 ሚሊየን ቶን ኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን አገልግሎት አይሰጡም ብላ ጥላለች።

ከዚህ ደግሞ 1 በመቶ ብቻ የሚሆነው ነው ተመልሶ ጥቅም ላይ የሚውለው።

"አፍሪካውያን ማንኛውም አይነት መገልገያዎችን እንዴት መልሰው ጥቅም ላይ ማዋል እንዳለባቸው በደንብ ያውቃሉ። ነገር ግን ተገቢ በሆነ መንገድና የተሻለ ገቢ በሚያስገኝ መልኩ እንዴት መልሰው መጠቀም እንደሚችሉ ብዙም እውቀቱ የላቸውም" ይላል ጁስት።

ጁስት በአንዳንድ የአፍሪካ አገራት አገር በቀል ድርጅቶች እንዲሁም መንግሥታት ኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን መልሰው ጥቅም ላይ ለማዋል እያደረጉት ያለው ጥረት የሚበረታታ ቢሆንም፤ ተገቢ እውቀት ሳይኖርና ቀጣይነቱን ማረጋገጥ ሳይቻል ወደሥራው መግባት ከባድ ነው ይላል።

ሲሞን አንደርሰን በኬንያዋ መዲና ናይሮቢ በተመሳሳይ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን መልሶ ጥቅም ላይ የሚያውል ድርጅት የንግድ ክፍል ኃላፊ ነች። ጁስት ያነሳውን ፈተናም ትክክል መሆኑን ተረጋራለች። ነገር ግን የሆነ ቦታ መጀመር አለበት ብላ ታምናለች።

"ብዙ ሰዎች በተለይ ኤሌክትሮኒክስ እቃዎች እንደሚባክኑ ያውቃሉ። ብዙዎችም አኗኗራቸውን መቀየር ይፈልጋሉ። እኛ ደግሞ የዚህ ለውጥ አካል መሆን ነው የምንፈልገው" ትላለች።

ሲሞን እንደምትለው ኬንያ ውስጥ ሁሉንም ሂደት ማካተት የሚችል ማቅለጫና መልሶ ጥቅም ላይ ማዋያ ድርጅት የመክፈት እቅድ አላቸው።

በጋና ኬፕ ኮስት የሚገኘው አርተር ደግሞ በጊዜ ብዛት የሰዎች አስተሳሰብ እየተቀየረ እንደሚመጣና ነገሮች እንደሚስተካከሉ ያምናል።

"የተሻለ ትምህርት መስጠት ከተቻለ ሰዎች ኤሌክትሮኒክስ እቃዎቻቸውን መልሰው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ እንዳለባቸው ይማራሉ ብዬ አስባለሁ" ይላል።