በኢትዮጵያ የገጠር ክፍል የነዋሪውን ኑሮ ለማሻሻል የሚጥሩት ሕንዳዊ መምህር

የፎቶው ባለመብት, Kannan Ambalam
ካናን አምባላም (ዶ/ር ) ይባላሉ። በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ አስተዳደርና የልማት አመራር ክፍል መምህር ሲሆኑ በወለጋ ዞኖች እና በምዕራብ ጉጂ ዞን በገጠር ከሚኖሩ የማኅበረሰብ አባላት ጋር በመሆን ከ70 በላይ ድልድዮችና ከ40 በላይ የንፁህ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታዎችን አከናውነዋል።
በሕንድ አገር ታሚል ናዱ ውስጥ ከምትገኘው ማንዱራይ ከተባለችው አነስተኛ መንደር የተገኙት ካናን፤ የዛሬ 13 ዓመት ገደማ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያውያን ፍቅር እወድቃለሁ ብለው አላሰቡም።
ካናን አሁን ላይ የአካባቢው ማኅበረሰብ እንደ አንድ የቤተሰብ አባል ነው የሚያየኝ ለማለት በቅተዋል።
ካናን በሕንድ መዲና ኒው ዴልሂ ከሚገኘው ጃዋሀርላል ኔህሩ ዩኒቨርሲቲ በሕዝብ አስተዳደር ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ያገኙ ሲሆን ለአንድ ዓመት ያክል ሕንድ ውስጥ ሥራ ሲያፈላልጉ ቆይተዋል።
የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ለመቀላቀል ያደረጉት ጥረት በአገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጠውን መመዘኛ ማለፍ ባለመቻላቸው ምክንያት ሊሳካላቸው አልቻለም።
ታዲያ የሥራ ፍለጋ ሙከራቸው በኦሮሚያ ክልል ከሚገኘው የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ጋር አገናኛቸው። በወለጋ ዩኒቨርሲቲ ሥራውን አግኝተው ወደ ኢትዮጵያ ለመሄድ እንዳሰቡ ለቤተሰቦቻቸው በሚናገሩበት ወቅት ግን አብዛኞቹ ሰዎች ወደማያውቁት አገር እንዳይሄዱ ነበር የመከሯቸው።
አንዳንዶቹም 'እንዴት ጦርነት ወደማይጠፋበት አፍሪካ ትሄዳለህ?' በማለት ስጋታቸውን ገልጸውላቸው ነበር። ካናን ግን ይህንን ዕድል እንደ ትልቅ አጋጣሚ እንደሚቆጥሩትና ወደ ኢትዮጵያ ሄደው ሥራ እንደሚጀምሩ ነግረዋቸው ጉዟቸውን ጀመሩ።
"ልክ እንደ ደረስኩኝ በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ አስተማሪዎችና ሌሎችም ጥሩ አቀባበል አደረጉልኝ። ሁሉም ሰው የምፈልገው ነገር እንዳለ ይጠይቀኛል። የአካባቢውም ማኅበረሰብም ቢሆን ወዲያው ነው የተቀበለኝ" ይላሉ።
አሁን ላይ በድፍረት የማኅበረሰቡ አንድ አካል ነኝ ለማለት እችላለሁ የሚሉት ካናን፤ መጀመሪያ አካባቢ ግን የማኅበረሰቡን ባህል፣ ቋንቋ፣ አመጋገብና አጠቃላይ የሕይወት ዘይቤ መልመድ ከብዷቸው እንደነበር አልካዱም።
ለምን ድልድይ ላይ አተኮሩ?
ካናን ያቀኑበት የአገሪቱ ክፍል በተፈጥሮ የታደለ ቢሆንም ንጹህ የመጠጥ ውሃ እና መሠረታዊ የሚባሉ ድልድዮች አለመኖር የማኅበረሰቡን ሕይወት እየፈተኑት ያሉ ችግሮች መሆናቸውን ለማስተዋል ጊዜ አልፈጀባቸውም ነበር።
"ወለጋ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ አስተዳደርና የልማት አመራር ክፍል በሁለተኛ ዲግሪ ደረጃ ትምህርት ለመስጠት ማሰቡን ተከትሎ ተማሪዎች በአካባቢው ተንቀሳቅሰው የሕዝቡን ችግር እንዲያጠኑ አደረግን። ከተማሪዎቹ ጋር ተጉዘን ማኅበረሰቡ በጣም የሚያሰስፈልጉት ነገሮች ምንድናቸው በሚለው ላይ መረጃ ሰበሰብን።"
በአንድ ወቅት ወደ ገጠራማው ክፍል ከተማሪዎቻቸው ጋር ባቀኑበት ጊዜ፣ በአነስተኛ ወንዝ አካባቢ የሚኖሩ አንዲት እናት ዕቃ ተሸክመው ለመሻገር ሲሞክሩ ተመለከቱ። ውሃው እየገፋቸውና ጭቃው እያዳለጣቸው በጣም ተቸግረው ወንዙን ተሻገሩ።

የፎቶው ባለመብት, Kannan Ambalam
ይህን ጊዜ "ወደተማሪዎቼ ዞር ብዬ ይሄ ችግር እኮ በቀላሉ መፈታት የሚቻል ነው አልኳቸው። እነሱ ግን በመጀመሪያ በጣም ከባድ ሊሆን እንደሚችልና ብዙ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ ነገሩኝ" በማለት ካናን መፍትሄ ለመስጠት ያሰቡትን ችግር እንዴት እንዳስተዋሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ካናን ግን ተማሪዎቹ በአካባቢው ለተጨማሪ ጊዜ እንዲቆዩና የቻሉትን ያህል እንጨትም ሆነ አጠና እንዲሰበስቡ ነገሯቸው። የተሰበሰውን እንጨት በመጠቀምም እዚያው አነስተኛ የሆነች ድልድይ መገንባት ቻሉ። የአካባቢውም ማኅበረሰብ ወጥቶ በሥራው አገዛቸው።
ካናን የመስክ ጉብኝታቸውን ጨርሰው ወደ ዩኒቨርሲቲው ሲመለሱ ከተማሪዎቻቸው ጋር ድልድዩን እንዴት ማሻሻል እንደሚችሉ ተነጋገሩ።
ተማሪዎቹም በአካባቢው በርካታ መሰል ድልድይ የሚያስፈልጋቸው መንደሮች መኖራችውን በማንሳት፣ የድልድዩን አሰራር ማሻሻል ስለሚቻልበትና ማኅበረሰቡን እንዴት ማሳተፍ እንደሚቻል በዝርዝር ተወያዩ።
ከዚህ በኋላም ካናን ከተማሪዎቻቸው ጋር በመሆን በወለጋ ዞኖች እና በምዕራብ ጉጂ ዞን ጉብኝት በማድረግ በርካታ ድልድዮችን መገንባት ችለዋል። በቅርቡ የሰሩትን ጨምሮ ከተማሪዎቻቸውና ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በመሆን 76 ድልድዯችን ገንብተዋል።
እንደ ቀልድ አንዲትን እናት ወንዝ ለመሻገር የገጠማቸውን ፈተና በመመልከት የተጀመረው የዚህ ሥራ ውጤት በርካታ ቦታዎችን ለማገናኘት በቅቷል። በተጨማሪም በተለያዩ ቦታዎች ያሉ ነዋሪ ድልድዮቹን እንዴት መስራት እንደሚችልና ሲበላሹም እንዴት መጠገን እንደሚችል ጭምር ለመስተማር ችለዋል።
መጀመሪያ አካባቢ ደግሞ የድልድዮቹን ጥቅም የተመለከቱ የሌላ መንደር ነዋሪዎች ዩኒቨርሲቲው ደጃፍ ድረስ በመምጣት ካናን ድልድዮቹን እንዲገነቡላቸውና አሰራሩንም እንዲያሳይዋቸው ይጠይቁ ነበር።
ድልድዮቹ በግምት እስከ 34 ሜትር እርዝማኔ ያላቸው ሲሆን ስፋታቸው ደግሞ እስከ 4 ሜትር የሚደርስ ነው።
እነዚህ ድልድዮች እንደ ቀላል ነገር ታይተውም ቢሆን አገልግሎት ላይ መዋል ከጀመሩ ወዲህ የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ተማሪ ልጆቻቸው ወደ ትምህርት ቤት በጊዜ መድረስ መቻላቸውንና ወደ ጤና ጣቢያዎች መሄድም ቢሆን ከሌላ ጊዜው መቅለሉን አስተዋሉ።

የፎቶው ባለመብት, Kannan Ambalam
በመጀመሪያ የተሰሩት ድልድዮች ከእንጨት ብቻ ነበር የተሰሩት። ነገር ግን ከጊዜ ብዛት በዝናብና በንፋስ መበለሻሸት ሲጀምሩ ለድለድዮቹ የተሻለ ድጋፍና ተጨማሪ ንጣፍ መገንባት ጀመሩ። ከዚያም ሲሚንቶ በመጠቀም ጠንካራ ድጋፎች እንዲኖራቸው በማድረግ ለረጅም ጊዜ እንዲያገለግሉ አደረጉ።
"ከመጀመሪያዎቹ ድልድዮች መካከል ጥቂቶቹ የመፍረስ አደጋ አጋጥሟቸው ነበር። ነገር ግን አሁን ላይ የተሻለ አሰራር ስለምንጠቀም ድልድዯቹ አይፈርሱም። ትንሽ ጉዳት ሲያጋጥማቸውም ቢሆን የአካባቢው ማኅበረሰብ እንዴት መጠገን እንዳለበት ስላስተማርነው እራሱ ሄዶ ይጠግናቸዋል" ይላሉ።
ድልድዮቹ በሚገነቡበት ጊዜ ሲሚንቶ እና የብረት ወይም የእንጨት ድጋፎች ብቻ ናቸው ከገበያ የሚገዙት። የተቀረው በሙሉ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በመተባበር የሚገኝ ነው። እንጨት፣ አሸዋ፣ ገመዶችና ዋነኛው የሰው ጉልበት የሚገኘው ከነዋሪው መሆኑ ወጪውን በእጅጉ ቀንሶላቸዋል።
ካናን የተሻሻሉትን ድልድዯች ለመገንባት የሚያስፈልገውን ሲሚንቶ ለመግዛት መጀመሪያ ላይ ከኪሳቸው ገንዘብ ማውጣት ነበረባቸው። ነገር ግን የአካባቢው መገናኛ ብዙኃን የሰሩትን ዘገባ ተከትሎ ድጋፍ የሚያደርጉ ሰዎች ቁጥር የጨመረ ሲሆን ዩኒቨርሲቲውም ቢሆን ተጨማሪ ድጋፍ ማድረግ ጀምሯል።
"በፕሮጀክታችን ሦስት ዋና ነገሮችን ማሳካታችንን እንከታተላለን። የመጀመሪያው በአካባቢው ያለ ማንኛውንም አይነት ሀብት በአግባቡ መጠቀም ነው። ሁለተኛው በጣም ቀላል ፈጠራ መሆን አለበት የሚለው ነው። ማኅበረሰቡ በቀላሉ ሊሰራው የሚችልና ወጣቶችን የሚያሳትፍ መሆን አለበት። ሦስተኛው ደግሞ በጣም አነስተኛ ወጪ የሚያስወጣ የሚለው ነው።"
ንጹህ የመጠጥ ውሃ
ካናን በአካባቢው ሲንቀሳቀሱ ያስተዋሉት የድልድይ ችግር ብቻ አልነበረም። ማኅበረሰቡ ንጹህ የመጠጥ ውሃ የሚያገኝበት ዕድል እንደሌለው ሲረዱ ይህንንም ችግር መፍታት የሚቻልበትን መንገድ ማሰላሰል ጀመሩ።
"ወደ ዩኒቨርሲቲው በምሄድበት መንገድ ላይ ሰዎች ግራና ቀኝ የሚፈሰውን ውሃ ሲቀዱ ተመለከትኩ። እንደውም ያንን ቆሻሻ ውሃ የሚጠጡ ሰዎችንም ተመለከትኩ። ቀረብ ብዬ ለምንድነው ቆሻሻውን ውሃ የምትጠጡት ስላቸው፤ ሌላ የንጹህ ውሃ ምንጭ እንደሌላቸው ነገሩኝ። ይሄን ካየሁ በኋላ ደግሞ አሁንም ከተማሪዎቼ ጋር በመሆን ለምን አነስተኛና ቀላል የውሃ ማጣሪያ አንሰራላቸውም ብዬ አሰብኩ።"
ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ ውሃውን የማጣራት ሥራው የአካባቢውን ማኅበረሰብ ኑሮ በጣም ቀላል ማድረግ ሲጀምር የሌላ መንደር ነዋሪዎችም ማጣሪያዎቹ እንዲሰሩላቸው መጠየቅና አስተምሩን ማለት ጀመሩ። አሸዋ፣ ጠጠር፣ ከሰልና ሌሎች በቀላሉ የሚገኙ ግብአቶችን በመጠቀም የሚሰሩት የውሃ ማጣሪያዎች ቁጥር አሁን ላይ 43 ድረሷል።

የፎቶው ባለመብት, Kannan Ambalam
ልክ በቀላሉ እንደሚሰሩት ድልድዮች ሁሉ የአካባቢው ማኅበረሰብ በሁሉም ሂደቶች ላይ ተሳትፏል። በዚህም ነዋሪው ውሃውን እንዴት አጣርቶ መጠጣት እንደሚችልና ማጣሪያዎቹ ቢበላሹ እንኳን መልሶ መጠገን የሚያስችል እውቀት አግኝቷል።
"ይሄ ትክከለኛ የልማትና ሕዝብ አስተዳደር ሥራ ማሳያ ነው" ይላሉ ካናን።
ካናን አምባላም (ዶ/ር) በወለጋ ዞኖች እና በምዕራብ ጉጂ ዞን በገጠር የሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ሕይወት ለመቀየር ባደረጉት ጥረት ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስቴር የወርቅ ሜዳሊያ ሽልማትና የእውቅና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።
ሚኒስቴሩ እሳቸውና ተማሪዎቻቸው እንዲሁም ማኅበረሰቡ በመቀናጀት ያከናወኑትን ሥራ እውቅና በመስጠት ሌሎች ፕሮጀችቶችን ለመደገፍ የሚውል 25 ሺህ ብር በሽልማት መልክ ሰጥቷል።
በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ አስተዳደርና የልማት አመራር ክፍል መምህር የሆኑት እኚህ ግለሰብ ምናልባት ከዚህ ቀደም የግንባታ አልያም የምህንድስና እውቀት ነበራቸው ወይ የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። እሳቸው ግን ከዚህ በፊት ምንም አይነት የግንባታ ልምድ እንዳልበራቸውና በጊዜ ብዛት የተማሩት እንደሆነ ይናገራሉ።

የፎቶው ባለመብት, Kannan Ambalam
"ሕንድ እያለሁ መሰል ሥራዎች ላይ በቀጥታ ባልሳተፍም በየመንደሩ የልማት ሥራዎች ሲሰሩ ተመልክቻለሁ። ወደ ወለጋ ከመጣሁ በኋላ ደግሞ ድልድይ እንዴት በቀላሉ መገንባት እንደሚቻል የራሴን ምርምር አድርጌያለሁ። በርካታ ተንቀሳቃሽ ምስሎችንም በመመልከት ነው ሀሳቡን ያመጣሁት።"
የአካባቢው ማኅበረሰብ ዳገትና ቁልቁለቱን በባዶ እግሩ ሲመላለስበት የተመለከቱት ካናን ለምን ጫማ አያደርጉም ብለው ይገረሙ ነበር። ነገር ግን የድልድዮቹን ግንባታ በሚያከናውኑበት ወቅት እርሳቸውም ጫማቸውን ማውለቅ ነበረባቸው።
"በደንብ ተመችቶኝ ሥራዬን ሰራሁ" ይላሉ ካናን። ከዚያ ጊዜ በኋላ ካናን ወደ መንደሮቹ ሲሄዱ ጫማቸውን አውልቀው ነው ወደ ሥራ የሚሰማሩት።
ይህ ደግሞ ከሰሩት አስመስጋኝ ተግባር ጋር ተደምሮ የአካበቢው ማኅበረሰብ ይበልጥ እንዲቀበላቸውና እንደ አንድ የቤተሰብ አባል እንዲያያቸው አድርጓል።












